የዘር ፖለቲካን የማስዋብ ፕሮጀክት

እናት እና አባቱን ለማያውቅ ሰው ያለው የማንነት ጥያቄ ለማንም ሚስጥር አይደለም። የሰው ልጅ ከማን ጋር እንደሚዛመድ፣ የዘር ግንዱ ከወዴት እንደሆነ ለማወቅ የሚፈልግበት ዋነኛው ምክንያት መከታና ዘብ ሚሆንለትን ለማግኘት፣ ከአዳም ወይ ከዝንጀሮ መጣህ ከሚለው ውጪ ትንሽ ለሱ ጠጋ ያለ ዘር ለማግኘትም ይሆናል። ከዝንጀሮ ወደ ሰው ተቀየርን የሚለው ሳይንስ በዋነኛነት የሰውን ልጅ ቆሞ መሄድ ምክንያት አድርጎ የሚያነሳው ዝንጀሮ ምድር ላይ ያለውን እህል ጨርሶ ከዛፍ ለማውረድ ሲታገል በዛው ቆሞ መሄድ ቻለ የሚል ነው። ስለዚህ አሁን ጎንበስ ብለን አርሰን መብላት ስንጀምር እንደው እንደ ድንገት ወደ ዝንጀሮ እንዳንመለስ ሲባል የሰው ዘር የሚባል ዘር መጠሪያችን አርገን መያዝ አለብን ባይ ነኝ። ከሰው ዘርነት ወረድ ብለን ስንዘረዝረው ደግሞ የአህጉር መከፋፈል፣ ቀጥሎም የሀገር መከፋፈል፣ ብሎም የክልል መከፋፈል እያልን እያልን ወደ ወረዳ እንዲሁም ወደ 1 ለ 5 አደረጃጀት ክፍፍል መድረስ እንችላለን። እውነት ነው አሁን ባለው ሁኔታ ከፋፍለህ ግዛ፣ ድሀውን ህዝብ የድሀ ደሀ እስከማስባል ተጠግቷል። ብቻ ከአብዛኛው የህዝብ ክፍፍሎች ውስጥ የዘር ክፍፍል አሁን ስሙ ከጦርነት ጋር ተያያዘ እና መልክ አጣ እንጂ ዘር ሲባል ቤተሰብ እንደማለት ውበት ያለው ስያሜ ነበረው። አሁን ዘሩን የሚወድ ሰው ዘረኛ በመባል ይፈረጅና “መውደድ” የሚለው ቃል ትርጉሙን ሲስት መመልከት ጀምረናል።

እንደ አብዛኛው ሰው አስተሳሰብ ዘረኝነት ከ30 አመት በፊት በመጣው የአስተዳደር ለውጥ፣ ህገ መንግስቱ እንደደነገገው ብሄር ብሄረሰቦች በመባል ስም ተሰጥቶት እንዲሁም ባንዲራችን ላይ ምልክት ይሆን ዘንድ ልዩነትን ተቀብሎ፣ እሱንም ልዩነት አቻችሎ ይኖር ዘንድ ያሳያል የተባለውን ምልክት ያሰፈርንበት ጊዜ የመጣ አይደለም። የዘር ክፍፍል በነገስታቱም ጊዜ ጭምር የነበረ፣ ያኔም ቢሆን ነገስታት እንዳሁኑ የፌደራል መንግስት እና የክልል መንግስታት ተብለው እንደተሰጣቸው መሰል የስልጣን ክፍፍል ነበር። በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ማን ስልጣን የመያዝ መብት አለው፣ ማን የሀገርን ሀብት የመጠቀም መብት አለው እንዲሁም ማን መብትና ግዴታን የማስቀመጥ መብት አለው የሚለውን ይወስናል። ችግሩ የሚፈጠረው አንዱ ዘር ትልቁን የመወሰን መብት ለብቻው ሲይዝና ሌላውን ዘር ከስልጣን የማራቅ ስራ ሲሰራ ነው። ይህም በሌላው ዘር ላይ ከፍተኛ ጥያቄን የሚያስነሳ ሲሆን፣ ስልጣኑን ሙሉ ለሙሉ በማለት ደረጃ የተቀራመተውን ዘር እና ከተነፈገው ዘር ጋር የእኩልነት አለመስፈን ስሜት ይሰፍናል። ይህ ደግሞ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ደግሞ የባህል እኩልነትን ጭምር ጥያቄ ውስጥ በመክተት አለመረጋጋትን ይፈጥራል።

የዛሬው የዚ ጽሁፍ አላማ የዘር ፖለቲካን መተንተን ሳይሆን፣ አሁን ባለንነት ወር የሚካሄደውን የአዊብ ሜይ ፎረም 2022 አስመልክቶ ፣ በእለቱ ከሚነሱት ሶስት ዋና ዋና ርእሶች የዘር ፖለቲካና አመራር(Ethnic Politics and Leadership Crisis)፣ በጥልቀት ማሰብና ማገናዘብ(critical thinking)፣ ራዕይ ያላቸው ሴቶች(Woman of vision) እንዴት ሶስቱን የተለያዩ ርእሶች ለአንድ አላማ እናውላቸው በሚል አሰብኩና እንዲ አስቀምጬዋለሁ።

ስለ ሴቶች እኩልነት ሲነሳ እንደው ሁሌ የምጨነቀው እኩል ለመሆን ሲባል ሴቶች ከወንዶች የሚበልጡባቸው ብዙ ብቃቶች እንዳይጨፈለቁ ነው። ሴት ልጅ ማንም የሚመሰክርላት የአስተዳደር ጥበብ አላት። ማስተዳደር ከመቻል ውስጥ ዋነኛው የሞተና የጠፋ የሚመስልን ነገር ነፍስ በመዝራትና ድምቀት የመሆን ጥበብን የተጎናፀፈች ናት ብል ማጋነን አይሆንም። በደስታም በሀዘንም፣ በህመምም በጤንነትም፣ በመረሳትም በመገኘትም ውስጥ ፊት አውራሪዋ ሴት ናት። እንደው አሁን በዘመናዊነቱ ንግርት ቡና አብሮ መጠጣት የሀሜት መድረክ ተባለና ሁሉም ቤቱን ዘግቶ መቀመጥ ጀመረ እንጂ፣ እናቶች ጎረቤቶቻቸውን አለን የሚሉበት፣ አንረሳሳም ችግራችንን አብረን እንፈታለን የሚል ጠንካራ ቃልኪዳን ያለበት መድረክ ነው። የዚህ ትልቅ መድረክ አዘጋጆች ደግሞ ውብ እናቶቻችን ናቸው። ቤተሰብን አስማት በሚመስል መልኩ ማስተዳደሩ ሳያንስ፣ ጎረቤትን ብሎም ሰፈርን የማስተዳደር ጥበብ ነው። እንደው እንደው ይህን ሀሳብ እንደሀገር እናስበውና፣ ለየሁሉም ቤት እናት ካልሆነም እናትን የምትተካ አንዲት ሴት እንዳለች ሁሉ፣ ለየሁሉም ዘር ወካይ የምትሆን አንድ እናት ብትኖር፣ ጉርብትናም እንዲሁም ኑ ቡና ጠጡ የምንባባለው የተለያየ ብሄር አባላት ጎረቤቶች፣ ለሀዘናቸው ምስር የሚለቅም እድር እንዳለ ሁሉ፣ አንዱ ብሄር ሀዘን ሲደርስበት አፈር ልብላ ብሎ ነጠላውን ይዞ የሚሮጥ የሌላ ብሄር ማህበር ቢኖር፣ ለሰርግ ሰንጋ ሲጣል፣ አረ ኩሉን ማን ኩሏታል የሚል ሙዚቃ ከኋላ ሲጫወት፣ በእድር ብር ከተከራዩት ዳስ ስር የሚንቦሎቦል ጭስ ያለበት፣ የክትፎ መጨለፍ ስራ ክፍፍል እንደተሰጣት እናት የጎረቤቷ ድግስ እንዲዳረስ ለልጇ አሳንሳ እንደምትሰጥ ሁሉ በዛ ልክ ለደስታው ሽር ጉድ የሚል ሌላ ብሄር ቢኖር፣

ባልና ሚስት ሲጣላ እግር ላይ ወድቀው የሚያስታርቁ ጎረቤቶች አይነት፣ የእርስ በርስ አለመስማማት ሊከፋፍል ሲነሳ እንደው በሞቴ ቤተሰባችን ነህ፣ አንተንም አንጣህ አንቺም አድቢ ብሎ ነገርን የሚያበርድ ብሄር ቢኖር፣ ስንቱ ተነግሮ ያልቅና! ከዚ በላይ ሀገርን የማስተዳደር ጥበብ ከእናቶች ወይም ከሴቶች በላይ፣ ፍቅር የማይገዛው እንደሌለ የሚያምን እና እሱን የማስመስከር ጥበብ ያለው ያለ አይመስለኝም።

ሴቶች ግን በዚ በወንድ መር አለም ላይ ተውጠው፣ ምህዋራቸውን ቤተሰብን በማስተዳደር ብቻ ያጠሩት ይመስለኛል። ይህንን ትልቅ ሀገርን አንድ የማረግ አላማ እና ራእይ ሴቶች ከልጅነታቸው ጀምሮ በማሰብ ራሳቸውን ሀገር ለመምራት ብቁ ማረግ አለባቸው። እንደኔ እንደኔ ሰው እንደህልሙ ስፋት ይኖራል። ሰው ባለው ራእይ ልክም ያብባል። ሴት ልጅ ሀገርን የመምራት ራእይ እስከሌላት ድረስ እንኪ ምሪ ብትባል አልፈልግም ብላ በሯን ዘግታ መቀመጧ አይቀርም። ታድያ በዚ ውስጥ ነው ክሪቲካል ቲንኪንግ የሚመጣው። Critical thinking ወቀሳ አይሁንብኝና ብዙውን ጊዜ እኛ ሀገር ላይ አይስተዋልም። አስተዳደጋችን ይሁን እንጃ፣ የሰውን ሀሳብ ተቀብሎ ለማገናዘብና ለመረዳት መሞከር ከሽንፈት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖረው አድርገናል። አብዛኛውም የዘር ፀብ የሚነሳው ካለመደማመጥና አንዱ የአንዱን እውነት አልሰማም አሻፈረኝ ግን አንተ የኔን እውነት መስማት አለብህ ከሚል መሰረት አልባ አስተሳሰብ ነው። ሴት መሪዎቻችን ይህንን ጉድለት በመሙላት፣ ነገሮችን ከስሩ በማጤን፣ አለመግባባት የተፈጠረባቸውን ሀሳቦች በመለየት፣ ለነሱም እልባት በመስጠት ችግሮችን ለመፍታት መሞከር አለባቸው። በስተመጨረሻም የሜይ ፎረም ጉባኤ የምትማሩበትና አንድ እርምጃ ከፍ የምትሉበት መድረክ እንዲሆንላችሁ እየተመኘሁ በቀጣይ ጽሁፍ እስክንገናኝ ሰላም ቆዩኝ።