የአሥር ዓመታት የጓደኝነት ምስጢር

ባለፈው ቅዳሜ ፌብሩዋሪ 18 ቀን 2023 (እ.አ.አ.) ኤውብ “ጓደኝነትን ማክበር” በሚል ርእስ የእኔ እና የጓደኛዬን የነባት አባስን በኤውብ ቆይታችን ያካበትነውን የአሥር ዓመታት ጓደኝነት በማክበር እኛም ይህንኑ ምስጢር ለሌሎች እንድናጋራ እድል ተሰጥቶን ነበር፡፡ በቅድምያ መልካም ግንኙትን የምታበረታታው ብቻ ሳይሆን የምታከብረውን ማህበራችንን፣ በዋናነት ደግሞ ይህንን ሀሳብ ያፈለቀችውን የማህበራችን መሥራች ናሁን እኔና ጓደኛዬ እጅግ አናመሰግናታለን፡፡ ኤውብ እንደ ሙያ ማህበር ሙያተኛ ሴቶችን ለማስተሳሰር እያደረገች ያለችው ጥረት ተሳክቶላታል፡፡ ብዙዎች ጓደኛ ሆነዋል፣ ከዚያም ባለፈ የሥራ አጋር ሆነዋል፡፡ እስቲ ስለ እኔና ስለ ጓደኛዬ ነባት የኤውብ ጓደኝነት እና ምስጢራችን ቅዳሜ እለት ላልተገኛችሁትም ሆነ ኤውብን የበለጠ ለማወቅ ለምትሹ ላውጋችሁ፡፡

በእርግጥ መጀመርያ የተዋወቅነው በቶስትማስተርስ ክለብ አባልነታችን አማካይነት ነው፡፡ እዚያ ያለውም የጓደኝነት መንፈስ በጣም ደስ የሚል ነው፡፡ እኛን ግን የበለጠ ያቀራረበን በኤውብ አባልነት ዳግም ስንገናኝ ነው፡፡ እሷም ሆነች እኔ ኤውብን የተቀላቀልነው ከተለያዩ ሰዎች ባገኘነው መረጃ ነው፡፡ የአገባባችን ወቅቱ ተመሳሳይ ስለነበረ በማህበሩ መሥራች (ናሁ) የሚሰጠውን በእራስ የመተማመን (Self Confidence) ስልጠና በአባባስ ቪላ አረንጓዴ መስክ ተገኝተን አብረን ወሰድን፡፡ የስልጠናውን አንኳር ጥቅም ለማግኘት ግልጽነት ወሳኝ ነበር፡፡ ጭንብላችንን አውልቀን በውስጣችን ያለውን ስሜት ዝርግፍ አድርገን ማጋራት፡፡ ናሁ ጭንብል የምትለው በማህበረሰባችን እና በባህላችን ሸብቦ የያዘን ይሉኝታ፣ ድብቅነት…ወዘተ ሲሆኑ ያንን በቻልነው ልክ ካላወለቅን በእራስ መተማመናችንን ልንገነባ አንችልም ትላለች፡፡

መደማመጥ አንዱ የጭንብል ማውለቁ ግብአት ነበር እና ጥንድ እየሆንን በግልጽ እንድናወራ ጊዜ ተሰጠን፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እኔና ነባት ተጣነድን፡፡ በተሰጠን አንድ ሰዓት ለዓመታት እንደሚተዋወቅ የልብ ልባችንን አወራን፤ ተደወለ፤ እኛ አልሰማንም ቀጠልን፤ ሰዓት አልቋል በቃችሁ ተብለን የመጨረሻዎቹ ጥንዶች ሆነን ሰልጣኖችን ተቀላቀልን፡፡ ያቺ ድንቅ እለት ነበረች የእኔ እና የነባት የልብ ጓደኝነት የመሰረት ድንጋይ የተጣለባት ቀን!

ከጥቂት የአባልነት ዘመን ቆይታ በኋላ ሁለታችንም ለኤውብ ቦርድ አባልነት ተመለመልን፡፡ ይሄ ደግሞ ሌላ አጋጣሚ ፈጠረልን፡፡ የቦርድ አገልግሎታችን ሲያልቅ በስትራተጂክ መሪነት አዳዲስ የቦርድ አባላትን ሜንቶር ማድረግ ቀጠልን፡፡ በቶስትማስተርስም እንዲሁ መገልገላችንን እና ማገልገላችንን ቀጠልን፡፡ ሌላ ያልነገርኳችሁ ሁለታችንም የሰው ሀብት ማኔጅመንት አባል ስንሆን እሷም በቦርድነት አገልግላለች፣ እኔም እያገለገልኩ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ ስናደርግ ደግሞ በእየ ፊናችን እንጂ እየተነጋገርን እንዳልሆነ ይታወቅልን፡፡ ቁምነገሩ ወዲህ ነው፡፡ እኔን የሚስበኝ እሷንም የስባታል፤ እሷን የሚስባት እኔንም ይስበኛል፤ እዛው እንገናኛለን፡፡ እውነት የማይመስሉ ብዙ ሳንነጋገር ወይም ሳንጠራራ የተገኘንባቸው ስብሰባዎች፣ ኮንፈረንሶች እና ወርክሾፖች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ሁለታችንም በደመነፍስ ተመሳስለናል፤ ተሳስረናልም፡፡  

እኛ ሳናስበው እና ሳንቀጣጠርባቸው የሚያገናኙን ጉዳዮቻችን አብረን ብዙ ጊዜያትን እንድናሳልፍ እድል ሰጡን፡፡ ጊዜ ማሳለፍ በደንብ ያስተዋውቃል፡፡ ሳወራላት ስታዳምጠኝ፣ ስታወራልኝ ሳዳምጣት፣ በሌላ ቀን “ያ የነገርሽኝ ጉዳይሽ ምን ደረሰልሽ?” ስንባባል፣ ምክር ስንለዋወጥ፣ ምክሩ ሲጠቅመን ስንመሰጋገን፣ ምክሩ ሲያከሽፍብን ስንሳሳቅ…ወዘተ እነሆ እዚህ ደረስን፡፡

ከመመካከር፣ ከመደማመጥ እና ከመሳሳቅ ከፍ ስንል ደግሞ በሙያችን አብረን እየሠራን እንገኛለን፡፡ በሙያችን እሷ በሰው ሀብት ማኔጅመንት ስፔሻሊስት ስትሆን እኔ ደግሞ ከሰው ሀብት በተጨማሪ በቁስ ሀብት ማኔጅመንት(Resource Management)፣ በሥነ ጾታ እና በኢቬንት ማዘጋጀት ዘርፎች ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ የሁለታችንን ሙያዎች እና ልምዶች አቀላቅለን በጋራ ብዙ ሥራ ሠርተናል፤ እየሠራንም እንገኛለን፡፡ እግዚአብሔር (አላህ) እድሜና ጤና ይስጠን እንጂ ወደፊትም ብዙ እንሠራለን፡፡ ባሳለፍነው አሥራ ዓመታት ኮሽ ብሎብን አያውቅም፤ ይልቁንም የበለጠ እየተቀራረብን መጣን እንጂ፡፡

አንዳንድ ሰዎች ጓደኛ አይወጣልኝም፣ እኔ ማንንም አላምንም፣ ጓደኞቼ  ቤተሰቦቼ (እህት፣ ወንድም፣ እናት አባት፣ ባል፣ ልጅ) ብቻ ናቸው…ወዘተ ብለውኝ ያውቃሉ፡፡ እናንተም ወይ  እንደዚህ ብላችኋል፣ ወይንም እንደዚያ የሚሉ ሰዎች ገጥመዋችኋል፡፡ እኔ ደግሞ ብዙ ጓደኞች ካሏቸው መሀከል አንዷ ነኝ፡፡ በጫወታችን ላይ ቤተሰቦቻችንን ጓደኛ በማድረግ ከምንጠቀመው ጥቅም ባልተናነሰ ሌሎች ቤተሰቦችን (ጓደኞችን) በሕይወታችን ብናስገባ እናተርፍ ይሆናል እንጂ አንከስርም፡፡

እንግዲህ ኤውብም ጓደኝነታችንን አስተውላ ይህንን ቀን ሰጥታናለች፡፡ ለእኛ ትልቅ ኃላፊነት እና ባለ አደራነትም ጭምር ነው፡፡ እኛ ሴቶች በማህበረሰባችን እና በአኗኗራችን የተጫነብንን ጫና ማቅለል የምንችለው ጥሩ ጓደኝነት በመመስረት ነው፡፡ ስሜታችንን የሚጎዱ እና የሚሰብሩን ብዙ ነገሮች በዙርያችን አሉ፡፡ ጥሩ ጓደኝነት የሕይወት ወጌሻ ነው፡፡ ጓደኛ እንዲኖራችሁ እየፈለጋችሁ ያልተሳካላችሁ ወይንም ያልሞከራችሁ ለጓደኝነታችን የረዱንን ምስጢራት እኔ በገባኝ ልክ ላጋራችሁ እና የሚጠቅማችሁን መርጣችሁ ውሰዱ፡፡

መተማመን፡- ለማንኛውም ግንኙነት መተማመን መሠረት ነው፡፡ አንዳችን ሌላችንን ማመን አለብን፡፡ ጥርጣሬ ግንኙነት ያሻክራል፤ ብሎም ያጠፋል፡፡ ለምሳሌ ጓደኛሽ የሆነ ሀሳብ ስታመጣ ልትጠቅምሽ እንጂ ልትጎዳሽ እንዳልሆነ ማመን ይኖርብሻል፡፡  አንቺም ለጓደኛሽ የምትሰጫት ሀሳብ ትክክለኛ እና ያመንሽበትን መሆን ይኖርበታል፡፡ ከሀሳብም በዘለለ በማንኛውም የእለት ከእለት ግንኙነት ላይ መተማመን ወሳኝ ነው፡፡

መደማመጥ፡- ጓደኛሽ ከምንም በላይ መደመጥን ትፈልጋለች፤ አንቺን የመረጠችሽ እንድታዳምጫት ነው፡፡ አንዳንድ ጓደኞች እያወራችኋቸው አቋርጠው (ይቅርታ ሳይጠይቁ) የራሳቸውን ብቻ አውርተው ይጨርሳሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰው ከሆንሽ ማዳመጥን ተለማመጂ፡፡ ጓደኛሽ የማዳመጥ ችግር ካለባት ምከሪያት፡፡ ተመክራም የማትታረም ከሆነ ጓደኝነቱ እኩል (mutual) ስለማይሆን ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም፡፡ ይህ ችግር የአንቺ ከሆነ መታረም ይኖርብሻል፡፡

መደጋገፍ፡-  ጓደኝነት ካለ መደጋገፍ የግድ ነው፡፡ በሀሳብ፣ በሙያ፣ መረጃ በመቀባበል እና ሌሎችም መደጋገፍ የሚጠይቁ ነገሮች ከጓደኝነት ይጠበቃሉ፡፡ ጓደኛሽ ድጋፏን ስትፈልጊ የማትገኝ ከሆነ አንቺም የማትገኚላት ነገር ግን እንዲሁ ለደስታ እና ለመዝናናት ብቻ የምትፈላለጉ ከሆነ ሙሉ ጓደኝነት አይደለም፡፡

መረዳት፡– የጓደኛሽን ስሜት ሆነ ያለችበትን ሁኔታ መረዳት ይኖርብሻል፡፡ ለምሳሌ ሁኔታዎች ሳይመቻቹላት ቀርቶ ለረዥም ጊዜ በአካልም ሆነ በስልክ ብትጠፋብሽ መጀመርያ በሀሳብሽ መምጣት ያለበት ደህንነቷን ማወቅ ነው፡፡ ደህና ሆና ነገር ግን ሳይመቻት ቀርቶ ከሆነ ያለችበትን ሁኔታ መረዳት ይኖርብሻል፡፡ አንቺ ካልሆንሽ ያልተመቸሽ ማስረዳት ይኖርብሻል፡፡ ጊዜው ደርሶ ስትገናኙ በመወቃቀስ ሳይሆን መገናኘታችሁን ብቻ በማክበር ያን ጊዜ ካቆማችሁበት መቀጠል ይኖርባችኋል፡፡ ነገር ግን መወቃቀስ፣ ያለመረዳት የመሳሰሉት ሀሳቦችን የምታስተናግዱ ከሆናችሁ ጓደኝነቱ ዘላቂ አይሆንም፡፡

ገደብ አለማለፍ፡- በተለይ ሴቶች ጓደኛ ስንሆን የግል ሕይወታችንን እና ምስጢራችንን ዝክዝክ አድርገን እናጋራ እና እኛም በአፀፋው የጓደኛችንን ታሪክ ማወቅ እንፈልጋለን፡፡ ይህ ጤነኛ ግንኙነት አይደለም፡፡ በጓደኝነትም ሆነ በማንኛውም ከሰው ጋር በሚኖረን ግንኙነት ገደብ (Boundary) ያስፈልጋል፡፡

መከባበር፡- ጓደኛሽን ምንም ያህል ብትወጃት እና እንደ እራስሽ ብታያት በማንኛውም ጊዜ ማክበር ይኖርብሻል፤ ሌሎች እንዲያከብሩሽ እንደምትሺው ሁሉ እሷም መከበር ትሻለችና፡፡ ለምሳሌ እኔና ጓደኛዬ ሙስሊም እና ክርስትያን ነን፡፡ እሷ የእኔን ሀይማኖት ታከብራለች እኔም የእሷን አከብራለሁ፡፡

ግልጽነት፡- ብዙ ጊዜበማህበረሰባችን ግልጽነት የተለመደ አይደለም፡፡ ጓደኝነት ደግሞ አንዱ ጠንካራ የሚያደርገው ሀሳብን በግልጽ መለዋወጥ ነው፡፡ ቀመር የበዛበት ግንኙነት ዘለቄታ የለውም፡፡

እንግዲህ የተቀረውን እናንተ ሙሉበት፡፡ እኔና ጓደኛዬ አስር ዓመታት አብረን እንድንኖር ያደረጉን የጓደኝነታችን ምስጢር እነዚህ ናቸው፡፡ ልባችሁን ለመልካም ጓደኝነት ክፍት አድርጉት፡፡ ለዛሬ ጨርሻለሁ!

Fitsum Kidanemariam

Share on your socials!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *