የሴት እድርተኞች


ማህበራዊ ኑሮ አስፈላጊ ነው ከሚሉ መሀከል አይደለሁም፤ አልፎም እጅግ ከሚያደንቁ እንጂ፡፡ ምናልባትም የሰውን መድሀኒትነት ስላየሁት ይሆናል፡፡ ማህበረሰባችን ከተዋቀረበት ማህበራዊ ተቋም አንዱ  ደግሞ እድር ነው፡፡ እድርም ያው እንደምናውቀው የሴት እድር እና የወንድ እድር ተብሎ ለሁለት የተከፈለ ነው፡፡  የሴት እድር ለማጀት ስራ የወንድ እድር ደግሞ ለአደባባይ ስራ የተዋቀረ ነው፡፡ \”ደግሞ በእድር ማጀትና አደባባይ ምንድነው?\” ለምትሉ እና ወደ እድር ላልተቀላቀላችሁ ከእኔ በቅርቡ ከተቀላቀልኩት የሴት እድርተኛ ማብራርያ ልስጣችሁ፡፡ ኢትዮጵያዊ ሆና ወይም ሆኖ \”እድር ደግሞ ምድነው?\” የሚለኝ ስለሌለ የማንነቱን ዝርዝር ባልፈውም ያው ጠቅለል ሲል ግን በሞት ጊዜ ለመረዳዳት የተቋቋመ ማህበር ነው፡፡

ማጀቱ እና አደባባዩን አልረሳሁም፡፡ የእድር የአደባባይ ስራ በሞት ጊዜ ድንኳን መትከል፣ ወንበር መደርደር፣ የእድር እቃዎችን ማውጣት ከዚያም ሟችን መቅበር ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ የለቅሶው ስርዓት ሲያበቃ ድንኳኑን አፍርሶ ወንበሮቹን እና እቃዎቹን ሁሉ መመላለስ ነው፡፡ አንዳንድ ሰፈር በተለይ የቀብር እለት በአሳላፊነት ሲሳተፉም ይታያሉ፡፡ ድሮ ድሮ እንደውም አስከሬን እየተቀባበሉና እየተጋገዙ እስከ ግብአተ መሬት ማድረስም  የወንድ እድርተኞች ኃላፊነት ነበር፤ አሁን አሁን ግን አስቀባሪ ድርጅቶች ሸክሙን ተረክበው ሥራቸውን አቅልለውላቸዋል፡፡

የማጀቱ ደግሞ ያው የእኛን የሴቶቹ እድር ማለቴ ነው፤ ቀጥታ ወደ ሀዘኑ ቤት ጓዳ በመግባት፣ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በመገዛዛት፣ ቤት በማስተካከል፣ ወደ ኩሽና ገብቶ ምግቡን፣ ቡናውን ብቻ ለእንግዳ መስተንግዶ የሚያስፈልገውን ሁሉ ማዘጋጀት፣ ከቀብር መልስ ቆሞ ማስተናገድ፣ ከማስተናገድ ቀጥሎ እቃ አጣጥቦ ማስገባት፣ ከዚያ ለእራት መዘጋጀት፣ ከዚያ ማስተናገድ፣ ከዚያ ነገም ተመልሶ በመሄድ ያንኑ ዙር እስከ ሶስት ቀን ደጋግሞ መስራት፣ ማስተናገድ…ወዘተ፡፡ ታድያ በዚህ መሀከል የቤቱ ማጀት እንዳይጎድል ደግሞ መለስ ቀለስ ማለትም እንዳለ ነው፡፡

ከመነሻዬ እንደጠቀስኩት ማህበራዊ ኑሮ አደንቃለሁ፤ በዚህ በለቅሶ ስርዓትም መተጋገዛችንን ወይም በእድር እና በጉርብትና የሚደረገውን ባህላችንን አከብራለሁ፡፡ ነገር  ግን ደግሞ በይበልጥ ስለ እድር በተለይ ስለሴት እድር ባወቅኩ ቁጥር ጥያቄዎች ይመላለሱብኝ ያዙ፡፡ በዋናነት የሴቶች ሕይወት የባሰ አታካች ሆነብኝ፡፡ መቼስ መከራ ወይንም ሞት በየጊዜው የሚመጣ ነገር ባይሆንም በአንድ መከራ የሴት እድርተኞች መከራው የደረሰባትን ሴት ጨምሮ (እራሷ ሟች ካልሆነች) እጅግ በጣም ይደክማሉ፡፡  ሌላው ያስተዋልኩት  የእድርተኞች አቻ ያለመሆን የሚኖረው ክፍተት ነው፡፡  በቤት ሥራ ያሉት ሴቶች የእራሳቸው አለቆች ስለሆኑ በሰዓታቸው ተገኝተው ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፤ የውጭ ሥራ የሚሰሩት በተለይ በሥራ ቦታቸው ፍቃድ መጠየቅና ማግኘት የማይችሉ ከሆኑ ጭንቅ ነው፡፡ በእድሩ አንዷ ሌላዋን የመረዳት መንፈስ አይስተዋልም፡፡  ይልቁንም የጎንዮሽ ወይም የኋልዮሽ ውይይት (gossip) በጣም አለ፡፡ \”እሷ ከማን በልጣ ነው ቀን መጥታ የማትሰራው? እኛ የሰራነውን ማታ መጥቶ ለማስተናገድማ ማን ብሏት! ከፈለገች ሰራተኛዋን ትላክና ታሰራ…ወዘተ\”፡፡ መድከማቸው ሳያንሳቸው አንደበታቸው ግን ያሸማቅቃል፡፡ እድርና ጉርብትና እንደጓደኝነት በምርጫ ስላይደለ የአስፈላጊነቱን ያህል በጣም ጥንቃቄ የሚሻው ግንኙነት መሆኑን ከገባሁበት በኋላ ነው የተረዳሁት፡፡

\”እና ምን ይሁን እያልሽ ነው!? ይሄማ የምናውቀው ባህላችን አይደለም ወይ? ያውም ድንቅ እሴታችን\” እያላችሁኝ እደሆነ ተሰማኝ፡፡ እኔ ይህንን ሀሳብ በጽሑፌ ሳመጣው መነሻ ሀሳቤ ያልተመለሰልኝን እና የሚያብከነክነኝን ነገር ለመጠየቅ ነው፡፡

መከራ ወይም ሀዘን የደረሰበት ሰው ድግስ (በክርስትና ሀይማኖት ጸበል ጸዲቅ) የሚያደርገው እና ያንን ሁሉ ቀባሪ የሚያስተናግደው ለምንድነው? እሺ ምናልባት የመጀመርያውና ከቀብር መልስ ያለውን ቀን ባህል አዋቂዎች \”ፍራጅ ነው፤ ነብስ ይማር ነው፣ ግዴታ ነው…ወዘተ\” ብለው አስረድተውኛል ያው ሙሉ በሙሉ ባይገባኝም ቀብር አድካሚ ስለሆነ የደከሙ ሰዎች ቢስተናገዱ ክፋት የለውም፡፡ ነገር ግን ሀዘንተኞችን በማያስጨንቅ መልኩ ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ በተለይ በማስታመም ያለ የሌለ ሀብት ንብረታቸውንና ጉልበታቸውን ሙጥጥ አድርገው መጨረሻ የማይቀረው ሞት መጥቶ ያሳዘናቸው ቤተሰቦች ድካማቸውና ሀዘናቸው ሳያንስ ለመስተንግዶ በርበሬ አነሰ፣ ዘይት ይጨመር፣ ሽንኩርት፣ እንጀራ…ወዘተ ጥያቄዎች ለምንድነው ጭንቀታቸው እንዲሆን የተፈረደባቸው!?

ከሁሉም  የሚገርመው ወይም የሚያሳዝነው ደግሞ ሞልቶ ተትረፍርፎልን የምንኖር ዜጎች ያለመሆናችን ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱና ጡዘቱ እየበዛ ሲሄድ እኛ ደግሞ ሞታችንም፣ ሰርጋችንም፣ ቤቢ ሻወራችንም (በቅርብ የተጀመረ ሌላ ጎጂ ባህል)፣ ልደታችንም በአጠቃላይ ድግሶቻችን ከሚገባው በላይ እየጦዙ መጥተዋል፡፡ እንዲያው የተጠና ነገር ባላገኝም (ፈልጌ ነበር) የለቅሶ እና የሰርግ ፉክክር እና ከፍተኛ ወጪ ያላቸው ሀገራት ቢጠኑ የእኛ ሀገር ከፊት ከሚሰለፉት ሁሉ ፊት እንደምትሆን እገምታለሁ፡፡

ወደተነሳሁበት የሴት እድር ስመጣ ደግሞ ብዙዎቻችን አሰራሩን ከማዘመን ይልቅ እየሸሸነውም ነው፡፡ የሴት እድርን እና ጉርብትናን ላለመቀላቀል \”ሀዘንና መከራ ሲመጣብኝ ወይንም የሚያስደግስ ደስታ ሲኖረኝ  እንደአመጣጡ በጊዜው እወጣዋለሁ\” በማለት በየቤታችን ክትት ብለን መኖርን መርጠናል፡፡ ታድያ ማህበራዊ ኑሮ ጠል ሆነን ይሆንን? እኔ አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም መዘዙን እና መንዛዛቱን ጠልተን እንጂ፡፡  ከስራው በላይ ሀሜት እና ማሽሟጠጡ አስፈርቶንም ጭምር! ወደድንም ጠላንም የማይቀር ከሆነ  የሴት እድራችን እድሳት ያስፈልገዋል! እድሳቱ ግን የእኛን አእምሮ ይመለከታል፡፡

እኔ በአጠቃላይ የለቅሶ ላይ መስተንግዶ ባሀላችን ጎጂ ባሀል ነውና መቀየር አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ሰልጥነናል የምንል ከሆነ ከሰለጠኑት ሀገሮች ተሞክሮ መውሰድ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ምን አልባት \”ቤቢ ሻወር ከሰለጠኑት ያየነውም አይደል!?\” እንዳትሉኝ ደግሞ፡፡ እኛም ሀገር \”ገንፎ ቅመሱልኝ\” የሚባል ባህል እንዳለን አስታውሱ፡፡ እና እስቲ እባካችን ከጊዜያችን ጋር እንሰልጥን! ቢያንስ የለቅሶ ቤት ድግሳችንን በመቀነስ እንጀምር! የሴት እድርተኛም ከሆንን የሰለጠንን እድርተኞች እንሁን!