ሲስተሙ (ክፍል ሁለት)

በሥራ ላይ በቆየሁባቸው በርካታ ዓመታት ብዙ እውቀት አግኝቻለሁ፤ በሥራም፣ በስልጠናም፡፡ አንዳንዶቹ እውቀቶች ግን እውነተኛ እውቀቶች አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ተግባራዊ ሲሆኑ አይታዩማ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በዓመት አንድ ጊዜ ወይንም ሁለት ጊዜ (እንደ መ/ቤቶቹ ይለያያል) የሚከናወነው የሥራ አፈጻጸም ምዘና ወይንም ግምገማ (Performance Appraisal) ነው፡፡ የሚያሳዝነኝ ደግሞ አንዳንድ መ/ቤቶች ብዙ በጀት በጅተው ለሠራተኞቻቸው እና ለኃላፊዎች ስልጠና እንዲያገኙ ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን በበኩሌ ውጤቱን ብዙም አይቼው አላውቅም፡፡ ለምን ይሆን? እንደ መገመት ቀላል ነገር የለም አይደል? እኔ ግምቶቼን ከልምዴ በመነሳት እዚህ ጽሑፍ ላይ ላስፍር እና እናንተ ተወያዩበት፡፡ እንደ ባለሙያ አንድ ነገር ግን አምናለሁ፡፡ የሥራ አፈጻጸም ምዘና አስፈላጊ ነው፡፡

የሥራ አፈጻጸም ምዘና ወይንም ግምገማ ማለት  ሠራተኞች በተሰጣቸው የሥራ ዝርዝር እና በተቀመላቸው ግብ ልክ ወይንም ከዚያ በላይ፣ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ሠርተው ማጠናቀቃቸውን፣ ሥራውን በሚያከናውኑበት ወቅት ምን ጠንካራ ጎን ነበራቸው፣ ምንስ ደካማ ጎን አላቸው፣ ከሌሎች ጋር ተግባብተው የመሥራት ችሎታቸው…ወዘተ የሚገመገምበት ነው፡፡ እያንዳንዱ ሠራተኛ በግሉ/ሏ ውጤት ተኮር በሆነ ሚዛን ይገመገማል/ትገመገማለች፡፡ ኃላፊዎችም ኃላፊዎቻቸው ይገመግሟቸዋል፡፡ የማይገመገም የለም፡፡ ሁሉንም በደረጃው ያዳርሳል፡፡ የግል ድርጅት ከሆነ የመ/ቤቱ ዋናው ኃላፊ በሥራው አይገመገምም፡፡ ምክንያቱም የድርጅቱ ባለቤት ነው፡፡ የመንግስት ድርጅት ከሆነ ደግሞ በአብዛኛው ሹመቱ ፖለቲካዊ ስለሚሆን የእሱ/ሷ መመዘኛ የፖለቲካ ብቃት እና ታማኝነት ነው፡፡ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ከሆነ ደግሞ ብሩን የሚለግሱት ለጋሾች የግምገማው የበላይ አካል ናቸው፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን  የአተገባበር ወጥነት የሌለው፤ ውጤትን ያላገናዘበ፣ በየዓመቱ አልያም በየስድስት ወሩ መደረግ ስላለበት ብቻ  “በግብር ይውጣ”  መንፈስ የሚደረግ እንደሆነ ብዙዎቻችን እናውቀዋለን፡፡እውነተኛ እውቀት አይደለም ለማለት ያበቁኝን ምክንያቶች ግን ብዙ ናቸው፡፡

አንደኛው ምክንያት ኃላፊዎች የሥራ አፈጻጸም ምዘና ወይም ግምገማ ማድረግ እንዳለባቸው የሚያስታውሱት ከሰው ሀብት የሥራ ክፍል ማስታወሻ ሲደርሳቸው ነው፡፡ ይህ ማለት ዓመቱን ሙሉ ምንም ዓይነት ሪከርድ የላቸውም ማለት ነው፡፡ ሪከርድ ማለቴ ለምሳሌ አንድ ኃላፊ በስሩ/ሯ አንድም፣ ሁለትም፣ አስርም፣ መቶም…ወዘተ ሠራተኞች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እለት ከእለት እንደ እሳት አጥፊ ከመሯሯጥ ውጪ ወይንም ድምጽ አጥፍቶ ከመሥራት ውጪ ዞር ዞር ብለው ያልተከታተሏቸውን ሠራተኞች በምን መነሻ ነው የሚገመግሙት? እኔ የእራሴን ልምድ ለምን አልነግራችሁም፡፡ ገምጋሚም ተገምጋሚም ሆኛለሁ፡፡ የግምገማ ሰሞን ሠራተኞች ባህርያቸው ይቀየራል፡፡ በማርፈድ እና በመቅረት እንዲሁም ሪፖርት በማዘግየት ናላችሁን ሲያዞሩ የነበሩ ሠራተኞች የዚያን ሰሞን ሽር ብትን ይላሉ፡፡ ይሄ ደግሞ የሆነው ሁኔታዎችን ገምተው ነው፤ አይፈረድባቸውም፡፡ ብዙ ኃላፊዎች የቅርብ ተመልካቾች (Short sighted) ሆነው ስላስተዋሉ ነው፡፡ እኔማ ምን ያስታውሰኛል መሰላችሁ፡፡ ካፌ ገብታችሁ የተለያየ ማክያቶ (ነጭ፣ ጠቆር ያለ፣ መካከለኛ፣ ያለ ስኳር…ወዘተ) ብላችሁ ካዘዛችሁ በኋላ አንድ ዓይነት ማክያቶ አቅርበው በግዳጅ እየተነጫነጫችሁ ካስጠጧችሁ በኋላ ሂሳብ ልትከፍሉ ስትሉ ጉርሻ (ቲፕ) ላለማጣት የሌለ ትህትና የሚያሳዩትን አስተናጋጆች፡፡ ብዙ ጊዜ የቢሮ ሠራተኞችም ባህርይ እንደዚያው ነው፡፡ ሥራቸውን ጽድት አድርገው የሚሠሩ ሠራተኞች በዚህ ሂደት ይዘነጋሉ፡፡ እስቲ የዓመት ወይንም የስድስት ወር ሪከርድ ወይንም መዝገብ ያላችሁ ኃላፊዎች እነማን ናችሁ? የሠራተኞቻችሁን የሥራ ዝርዝር እያያችሁ፣ በየጊዜው ክትትል እያደረጋችሁ በበረቱበት እያደነቃችሁ በደከሙበት እየደገፋችሁ ሙሉ ክትትል የምታደርጉ ኃላፊዎች እነማን ናችሁ?

ሁለተኛው ምክንያት ከሥራ አፈጻጸም ውጤት ይልቅ ግንኙነት ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ኃላፊዎች ይበዛሉ፡፡ በዚህም የተነሳ አንዳንድ ሠራተኞች የሥራ ውጤታቸው ላይ ከማተኮር ይልቅ ኃላፊዎቻቸውን ማስደሰት ላይ ያተኩራሉ፡፡ በእርግጥ ኃላፊዎች ሁሉ በሥራ ውጤት ይደሰታሉ፡፡ ምክንያቱም የእነሱ ብቃት የሚለካው እያንዳንዱ ሠራተኛ ባመጣው የሥራ አፈጻጸም ውጤት ነውና፡፡ ነገር ግን ይህ ሁልጊዜ እውነት አይደለም፡፡ አንዳንድ ኃላፊዎች ጸጥ ለጥ ብላችሁ ሥራው ላይ ከተቀመጣችሁ አልፎ አልፎም የግል ጉዳያቸውን ከፈጸማችሁ ለእነሱ በቂ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ጥቁሩን ነጭ ሲሉ ልክ ነው፣ ነጩን አረንጓዴ ሲሉም ልክ ነው የምትሉ ከሆናችሁማ ሌላ መሥሪያ ቤት ደርባችሁ ብትሠሩ እንኳን ዞር ብለው አያይዋችሁም፡፡ የእነሱን ትኩረት የሚስቡት የሚሞግቷቸው ሠራተኞች ናቸው፡፡

ሦስተኛው ይሉኝታ ነው፡፡ በሀገራችን ይሉኝታ እንደ ትህትና ከመቆጠሩ የተነሳ ብዙዎችን አቅመ ቢስ ያደረገ ድምጽ አልባ መሣርያ ነው፡፡ ኃላፊዎች የማይሠራን ሠራተኛ በትክክል ድክመቱን በመንገር፣ ማሻሻል የማይችል ከሆነ በማሰልጠን ከዚያም ካለፈ በተለይ ያልተገራ ባህርይ ካለው በመግራት እና በመቅጣት አስተካክላለሁ በማለት ቁርጠኛ ከሆነ አለቀለት፡፡ ሴት ኃላፉ ከሆነችማ ወየውላት፡፡ ስለዚህ ተቀባይነት ለማግኘት ወይንም በኃላፊነት ላይ ለመቆየት ያለው አማራጭ እያዩ እንዳላዩ መሆን ነው፡፡ እናም የሥራ አፈጻጸም ምዘናው ወቅት ዝቅተኛ ውጤት ላስመዘገቡት ሠራተኞች ሳይቀር የማለፍያ ነጥብ ማለትም ዓመታዊ ጭማሪ ካለ የማያስከለክል፣ እድገት ቢመጣ ከውድድር የማያስወጣ እና በዋናነት ቂም የማያመጣ የምዘና ውጤት መስጠት የተለመደ አሠራር ነው፡፡ አንዳንድ መ/ቤቶች ምዘናውን ለማዘመን እና አሳታፊ ለማድረግ 360 ድግሪ የሚባለውን ያክሉበታል፡፡ ጥሩ ጅማሮ ሆኖ ነገር ግን ማንም የሥራ ባልደረባ ደፍሮ ትክክለኛ አስተያየት አይሰጥም፡፡ ሁልጊዜ ልክ ሰዎች ሲሞቱ በስርዓተ ቀብራቸው ላይ እንደሚነበበው አማላይ ታሪካቸው 360 ድግሪም መልካምነትን፣ በሥራ ተባባሪነትን፣ መፍትሔ አምጪነትን…ወዘተ ያትታል፡፡  ጥቂቶች እውነት ይናገሩ ይሆናል፡፡ እሱንም በቀጣይ ግንኙነታቸው ላይ ፈርደው ነው፡፡ እውነት ታጋጫለቻ! ታስጠምዳለችም፡፡

አራተኛው የእውቀት ማነስ ነው፡፡ ሁሉም ኃላፊዎች እና ሠራተኞች የሥራ አፈጻጸም ምዘና እውቀት አላቸው ብዬ አላምንም፡፡ ይህንን ከልምዴ አይቼዋለሁ፡፡ መመዘኛው አንድ ወጥ ከመሆኑ የተነሳ ሁሉንም የሥራ መደቦች በአንድ ዐይን ከማየቱም በተጨማሪ ኃላፊዎች ለእየራሳቸው የሥራ ክፍል በሚመጥን መልኩ ተርጉመው መጠቀም የተለመደ አይደለም፡፡ የፎርሙ አዘገጃጀትም ክፍተት አለበት፤ ተጨባጭ ከመሆን  ይልቅ ግምታዊ መለኪያዎች ይበዙበታል፡፡ ይህን ጊዜ እውቀት ያለው ኃላፊ ለሥራው በሚመጥን መልኩ በያዘው መረጃ ወይንም መዝገብ (ሪከርድ) መሠረት የሠራተኞቹን ሥራ መመዘን ያስችለው ነበር፡፡ ግን ማንም ቁብ አይለውም፡፡

በአጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ወይንም ምዘና ወግ ነው ያልኩትም ለዚሁ ነው፡፡ ይልቁንም በትክክል ሥራ ላይ ቢውል ሁሉም ሠራተኛ እንደየደረጃው እውቀት ኖሮት ሥራ ላይ ቢውል፤ አጠቃቀሙም በተመሳሳይ ፎርም ሁሉንም በአንድ ዓይነት ከመገምገም እንደየሥራ መደቡ ቢቀረጽና ቢተገበር ለሠራተኞችም፣ ለኃላፊዎችም እንዲሁም ለድርጅትም ጠቃሚ የሆነ የማኔጅመንት አሠራር ስልት ነበር፡፡ ለውጥ እዚህ ላይ ነው! ለዛሬ ጨረስኩ!!

By Fitsum Kidanemariam

Share on your socials!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *