ሲስተሙ (ክፍል ሁለት)

Image source: https://www.istockphoto.com/vector/cartoon-woman-saying-no-gm541136698-96757881

ይሄ ቃል በሕጻናት አንደበት ሲባል ልክ ከአፋቸው ማር ጠብ የሚል ነው የሚመስለው፡፡ እምቢ አንዳንዴም ሳብ ብሎ ወደ እምቢየው! ይለጠጣል፡፡ እኛም እነሱ ሲሉት አንከፋም፡፡ እንደውም ስሜታቸውን በትክክል የመግለጻቸውን ነጻነት ነው የሚያሳየን፡፡  እምቢ የማይፈልጉትን “አልፈልግም” የሚሉበት ቀላል እና ግልጽ ቃላቸው ነው፡፡  መቼስ በምድር ላይ  ድጋሚ የማይገኝ ነገር ቢኖር ሕጻንነት ነው፡፡ ስለማናገኘው “እንደ ሕጻናት” በሆንን ብለን እንመኛለን፡፡ ለነገሩ መጽሐፍ ቅዱስም ሁኑ የሚለን እንደእነሱ ነው፤ መሆን ስለማንችል ሕጻን ሁኑ አላለንም፡፡ ታድያ ይሄም ሆኖ እንደ ሕጻናት እምቢ ማለትስ ይቻል ይሆን! ነጻነቱ አለን ይሆን?

ዛሬ ይህንን ርእስ ይዤ የመጣሁት በምክንያት ነው፡፡ በሀገራችን ብዙ ጥሩ ልማዶች እንዳሉን ሁሉ ብዙ መጥፎ ልማዶችም አሉን፡፡ ስለጥሩዎቹ ሳልነካካቸው አርፈው ይቀመጡ፡፡ ጥሩ ያልሆኑትን  ግን በቻልኩት ልክ ላውራቸው እና ከተሳሳትኩ ታርሙኛላችሁ፤ ልክ ከሆንኩ ትጋሩኛላችሁ፡፡

አንደኛው ጥሩ ያልሆነ ልማድ የማንፈልገው ነገር ሲሰጠን “እምቢ” ያለማለት ነው፡፡ እምቢ እኮ በተለያየ ግን ደግሞ ቀለል ባለ መንገድ ይባላል፡፡ ለምሳሌ ምግብ እየበላን መጎራረስ ባህል ስለሆነ ብቻ ከአቅም በላይ የሆነ ጉርሻ ሲሰጠን እምቢ ለማለት ይሉኝታ ስለሚይዘን እንጎርሳለን፡፡ ጉርሻ ደግሞ ክፋቱ ትልቅነቱ እና በአንድ ያለመቆሙ ነው፡፡ ሁለት ትላልቅ ጉርሻ ያለፍላጎት መጉረስ ማለት ከዚያ በኋላ የሚመጣውን መጨናነቅ አስቡት፡፡ እኔ ጉርሻ ስለማልወድ ነው ይህንን ምሳሌ ያመጣሁላችሁ እንጂ ብዙ ሳንፈልግ የምንቀበላው ነገሮች አሉ፡፡

ሁለተኛው ጥሩ ያልሆነ ልማድ ወደ ሥራ ቦታችን ያመጣናል፡፡ የሥራ ኃላፊያችንን እምቢ ማለት እያቃተን ያላመንንበትን ሥራ ተቀብለን እንሠራለን፡፡ ለምሳሌ የስራ ኃላፊያችን የእኛ መደበኛ ያልሆነ ሥራ በአስቸኳይ እንድንሠራላቸው ቀነ-ገደብ ወይንም ሰዓተ-ገደብ አበጅተው ይሰጡናል፡፡  በእርግጥ በሥራ ቦታ የኃላፊ ትህዛዝ ከሆነ አይመለከተኝም የሚባል ሥራ የለም፡፡ ነገር ግን ቅደም ተከተል የሚባል ነገር ግን በእኛ ቁጥጥር ሥር መሆን አለበት፡፡ በእጃችን ላይ ያለው ሥራ ቀነ-ገደቡ ደርሶ የግድ ማለቅ  ያለበት ከሆነ ኃላፊያችን ያመጡልንን ተጨማሪ ሥራ በግልጽ ወይንም ቃል በቃል እምቢ ማለት ባይኖርብንም ቅሉ ሁኔታውን በማሳወቅ የቀደመውን ሠርተን ስንጨርስ እንደምንሠራው የማሳወቅ ልምድም ሆነ ጥበብ የለንም፡፡ እናም በተደራረበ ሥራ ተወጥረን እየተበሳጨን፣ እየተነጫነጭን እና እየታመምን እንሠራለን፡፡ እንደዚህ የተሠራ ሥራ ደግሞ ስህተት ሊኖረው ይችላል እና ከምስጋና ወቀሳ እናስተናግድ ይሆናል፡፡ በሥራ ቦታ ተመሳሳይ እምቢ የሚሹ ግን የማንላቸው ልማዶች ብዙ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ሦስተኛው ጥሩ ያልሆነ እና እምቢ መባል ያለበት ልማድ ሳንፈልግ የምንሄድባቸው ቦታዎች ናቸው፤ ሌሎችን ተከትሎ መሄድ፡፡  ማህበራዊ ሕይወት ከባድ ነው፡፡ ከሰው ጋር ለመኖር እና ላለመለየት ሲባል በጭራሽ የማንፈልግበት ቦታ ሄደን እንገኛለን፡፡ እዚህ ጋር አንድ የሥራ ባልደረባዬን በምሳሌ ላስታውሰው፡፡ እሱ ከሥራ በኋላ ወደ ቤት በቀጥታ መግባት አይመቸውም ነበር፡፡ ስለዚህም ከጓደኞቹ ጋር ካፌ አካባቢ ካልሆነም አየር እየወሰዱ ዞር ዞር ብሎ አመሻሽቶ መግባትን ይመርጥ ነበር፡፡ ጓደኞቹ ደግሞ “በባዶ አየር መሳብ ምን ይጠቅማል ባይሆን አንድ አንድ እንበል!” በሚል መጠጥ ቀማምሰው መግባትን ያደንቁ ነበር፡፡ እናም ይሄ ጓደኛዬ በሀሳቡ ባይስማማም ከጓደኞቹ ላለመለየት ወይንም እምቢ ላለማለት አብሮ እየጠጣ ማመሻሸቱን ያዘወትር ነበር፡፡ ታድያ በየቀኑ በሥራችን ላይ አረፍ እያልን ስንጨዋወት ምሬቱን ያወራልኝ ነበር፡፡ ሁለት ነገር ነበር የመረረው፤ ባልፈለገበት ቦታ ማምሸቱ እና በኢኮኖሚው መዛባት ምክንያት ወር ከመድረሱ በፊት በግለሰቦች ብድር ጠያቂነት እጅ መውደቁ ነበር፡፡ ሁለቱም የከፉ ጉዳዮች ስለነበሩ ለምን እምቢ አትላቸውም ብዬ ምክረ ሀሳብ ሳቀርብለት “አንቺ የደላሽ ነሽ፤ እምቢ ብዬ ከማን ጋር ልኖር ነው? ወይንስ ሴት ይመስል በጊዜ እየገባሁ…” ያው አልጨርሰው፡፡  ዋናው ችግሩ እምቢ የማለት ሆኖ ሳለ አማራጭ አለማሰብም ሌላ ችግሩ ነበር፡፡ ብዙ እንደዚህ ያሉ ሰዎች አሉ፡፡ በእኛ በሴቶችም ከሌሎች ላለመለየት በሚል ግር ብሎ ያለፕሮግራም ተከታትሎ መሄድ የተለመደ ነገር ነው፡፡ ጎጂ ባህል ብለው ይቀለኛል፡፡

 አራተኛው ጥሩ ያልሆነ እና እምቢ የሚያስፈልገው ልማድ ሳንፈልግ የምንገዛቸው ነገሮች ናቸው፡፡ ሻጭ የሆነ ሰው መቼስ ማግባባት፣ ማዋደድ፣ ከቻለም ማስገደድ እንጀራው ነው፡፡ የሚያስፈልገንን እና የማያስፈልገንን ማወቅ ደግሞ የእኛ የገዢዎች ነው፡፡ በዋጋው ይሁን በጥራቱ ካልተስማማን እምቢ ማለት መብትም ጭምር ነው፡፡ አንዳንድ ሰው ግን ይሉኝታ ይሁን ወይንም ቋጣሪ (ስስታም) ላለመባል ብቻ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት የማይፈልገውን ነገር ይገዛል፡፡  ይሄ በተለይ እኛን ሴቶችን የሚያጠቃ ልማድ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የታዘብኩት በተለይ ሱፐር ማርኬት አንድ ነገር ፈልገን ገብተን አሳፍሮን ያልፈለግነውን ወይንም ፕሮግራማችን ውስጥ የሌለውን ነገር የገዛንበትን ቀናት እናስታውስ፡፡ እዚህ ጋር ታይታ የእራሱ ድርሻ አለው፡፡ ታይታንም እኮ እምቢ ማለት ይገባል!  

እንግዲህ እምቢ መባል ስላለባቸው ልማዶች ሌሎችም ብዙ ምሳሌ እና እውነታዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እምቢ ማለት ሰዎችን ሊያስከፋ እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ መቼስ እንደ ሕጻናት እንደወረደ  እምቢ ብንል ትክክል አይመጣም፤ ለእነሱ የተሰጠ ነውና፡፡ ነገር ግን እምቢታችንን ዲፕሎማሲ ከጨመርንበት እና የሌሎችን ስሜት በማይጎዳ መልኩ ብንለማመደው እራሳችንንም ሌሎችንም ከጎጂ ባህል እና ከአላስፈላጊ ልማድ እንታደጋለን ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ በበኩሌ እምቢዬን ብዙ ተጠቅሜበታለሁ፡፡ በእርግጠኝነት የምመሰክረው እራሴን ከመጥቀም ውጪ ሌሎችን እንዳልጎዳሁም አረጋግጫለሁ፡፡ ለእራስ መመስከር ይቻል የለ!

ይህንን ጽሑፍ ለምታነቡ በድጋሚ ላስታውሳችሁ፤ እስቲ ወደ ልማዳችሁ ተመለሱ  እና “እምቢ” የሚያስፈልጋቸውን ልማዶቻችሁን አስቡ! እርግጠኛ ነኝ አንድም፣ ሁለትም ከዚያም በላይ አግኝታችኋል፡፡ እናም በሀሳቡ ከተስማማችሁ ልምምዳችሁን ከዛሬው ጀምሩ፡፡ መልካም ጅምር! እምቢ ካላችሁም መብታችሁ ነው! ለዛሬ ጨረስኩ!

Written by: Fitsum Atnafework K/Mariam

Share on your socials!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *