ሲስተሙ (ክፍል ሁለት)

እንዲያው አጋነንሽ አትበሉኝ እና (ከፈለጋችሁም በሉኝ) አንዲት ሴት እና አንድ ወንድ ተመሳሳይ ገድል ቢሠሩ ቀድሞ የሚወደሰው ወንዱ ነው፡፡ ቀድሞ መወደስ ብቻ አይደለም ገዝፎ የሚወደሰውም እሱ ነው፡፡ ይሄንን ያልኩት በተለያዩ አጋጣሚዎች ስላስተዋልኩ ነው፡፡ “ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ ያምራል”  እንዲሉ ምሳሌ ልስጣችሁ፡፡ ሴት እና ወንድ አትሌቶቻችን ዓለም አቀፍ በተደረገ ውድድር ላይ እኩል ርቀት በእኩል ድል አሸንፈው ቢመጡ በቅድምያ የወንዱ ድል ይዘገብ እና በተመሳሳይ ተብሎ ደግሞ የሴቷ ይነገራል፤ የወንዱ ፎቶ ከፊት ገጭ ሲደረግ የሴቷ ፎቶ የዞረው ገጽ ላይ ይታተማል፡፡ በእርግጥ ቦታ ከበቃቸው አንድ ገጽ ላይ ከላይ የወንዱ ከታች የሴቷ ይለጠፋል፡፡ ለነገሩ እሷ ምን ጨነቃት ያሸነፈችበት ሀገር የሚገባትን እኩል ክብር እና ክፍያ ስለከፈላት በአቅም ደረጃ አትተናነስም፡፡ በቢሮ አመራር፣ በፖለቲካ ስልጣን፣ በቢዝነሱ፣ ብቻ ሴቷ በምትሳተፍበት ሁሉ ዋና ሳይሆን ተከታይ ተወዳሽ መሆኗ የምናየው ነው፡፡

ያለፈው ሳምንት የአድዋ ድል 127ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሁላችንም አክብረናል፡፡ ድሉ ሲነሳ የሀገሪቷ መሪ የነበሩት ጀግናው እምዬ (አጼ) ምኒሊክ በዋናነት ይዘከራሉ፡፡ ደስ ያሰኛል፡፡ የአድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦችን ታሪክ የቀየረ ነው፡፡ የጦርነቱ መንስሔ የሆነውን የውጫሌ ስምምነት አንቀጽ 17 የጣልያንኛውን ቅጅ አለቃ አጽመ ጊዮርጊስ ከተረጎሙ በኋላ የሀገር ሉአላዊነትን እንደሚጋፋ ምኒሊክ ሲረዱ እና አሻፈረኝ ያሉት በቅድምያ የእቴጌ ጣይቱ አማካሪነት ታክሎበት ነው ይባላል፡፡ እቴጌ ሚስት ብቻ አልነበሩም፤ ስትራተጂያዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች አማካሪም እንጂ፡፡ ቆይ እስቲ ስለ እሳቸው ብዙ ከማውራቴ በፊት የእምዬ ምኒሊክን ድንቅ ባልነት ላስታውስ፡፡ እቴጌን ሲያገቡ በአራት አመት እንደሚበልጧቸው ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ? በእድሜ ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ እውቀትም ይበልጧቸው ነበር ይባላል፡፡ ታድያ ብልሁ ምኒሊክ መበለጣቸውን እንደ ጥቅም ነበር የቆጠሩት፤ ከ127 ዓመታት በፊት ሲጋቡ፡፡ የምኒሊክ በእራስ መተማመን የትየለሌ ነበር ማለት እኮ ነው፡፡ የእኛ ዘመን ባሎች በእድሜ የመውለድ ክልል መሆኗን፣ በእውቀት ሞጋች ያልሆነችውን አጣርተው ሲያገቡ “አቤት የስልጣኔ ልዩነት” እላለሁ!

እና ጣልያን “ያዙኝ ልቀቁኝ፣ አንቀጹን ካልተቀበላችሁ እና በማንኛውም የውጭ ጉዳያችሁ ላይ ጣልቃ ካልገባሁ ጦሬን እመዛለሁ” ሲል እቴጌ ጣይቱ የባላቸውን ምላሽ እና ምክር እንኳን አልጠበቁም ይባላል፤ “ከፈለግህ ለምን የዛሬ ሣምንት አታደርገውም!” በማለት ምላሽ ሲሰጡ፡፡ ምኒሊክም በሚስታቸው ምላሽ ተደሰቱ እንጂ አልተደናገጡም፡፡ ይልቁንም የሀገሬውን ሰው “ቅያሜ እንኳን ቢኖርህ ወደጎን አስቀምጠህ ክተት” ነበር ያሉት፡፡ እቴጌም ባላቸው ወደ ጦር ሜዳ ሲሄዱ እንደ ንግስትነታቸው “በድል ይመልስህ” ብለው አልነበረም የሸኟቸው፤ እርሳቸውም 5000 ወታደሮች አስታጥቀው አብረው ዘመቱ እንጂ፡፡ በውግያ መርተዋል፣ ሴቶችን አሰልፈው ወታደሩን በመመገብ፣ የተለያዩ የማበረታቻ እና የማወደሻ ዜማዎችን እንዲያዜሙ በማድረግ አብሮነታቸውን አስመስክረዋል፣ የጦር ቁስለኛ ወታደሮች እና ሰላማዊ ሰዎችን ሕክምና እና እንክብካቤ እንዲያገኙ አድርገዋል፤ ያውም ጣልያን ጉዳተኞችን ጭምር፡፡ በተለይ ደግሞ ለድላችን ዋነኛ ምክንያት ነው የሚባለውን ስልት ነድፈዋል፡፡ ይህም ጣልያኖች የመጠጥ ውሀ አጥተው እንዲዳከሙ በማድረግ መስመር አዘግተውባቸዋል፡፡ ድሉ ለኢትዮጵያ ከሆነስ በኋላ!?

በጦርነቱ እና በስደቱ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡትን ልጆች በመጠለያ በማሰባሰብ እናት ሆነዋቸዋል፤ በዘመኑ የነበረውን የዲቁና እና ቅስና ትምህርት እንዲማሩ በማድረግ በቤተ ክርስቲያናት እንዲያገለግሉ አድርገዋቸዋል፤ አዲስ አበባን የቆረቆሩት እሳቸው ናቸው፤ የመጀመርያውን ዘመናዊ እና በስማቸው የሚጠራውን እቴጌ ጣይቱ ሆቴልን መስርተዋል፤ ከቱርክ እና ከህንድ ነጋዴዎች ጋር በመዋዋል የሱፍ ምርት የሚመረትበት የመጀመርያውን የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ ለኢትዮጵያ በቅርሳቅርስ ጥበቃ እና ፊደላት ምስረታ ቀደምት የሆነችውን የኦርቶዶክስ ቤተ እምነት በማስፋፋት ረገድም የእንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያንን መስርተዋል፡፡ የመጀመርያው የሻማ ፋብሪካም የተቋቋመው በእሳቸው አማካይነት ነው ይባላል፡፡

እንግዲህ እቴጌ ከአድዋ ጦርነት በፊት፣ በጦርነቱ ጊዜ እና ከጦርነቱ በኋላ ከፈጸሟቸው ገድሎች ካነበብኩት በጥቂቱ ነው የነገርኳችሁ፡፡ ታድያ እቴጌ በሰሩት ገድል ልክ ተወድሰዋል ትላላችሁ? እኔ በበኩሌ አልተወደሱም ነው የምለው፡፡ ለስማቸው መጠርያ እንኳን አንድ ሐውልት አልተሠራላቸውም፡፡  ምክንያቱ ደግሞ እንደ እኔ አስተያየት ሴት የማወደስ ባህላችን ብዙ ይቀረዋል የሚል ነው፡፡ እስቲ ከእሳቸው በፊትም ሆነ በኋላ ለሀገር ውለታ የዋሉ ሴት መሪዎች እና ንግስታት አሉ፡፡ እነ ንግስት ሳባ፣ ንግስት ፉራ(የሲዳሞዋ) እና ሌሎችም ብዙ ሀገራዊ ገድል የተጋደሉ ሴቶች መሪዎች እንዲሁ ብዙ ሲነገርላቸው አይሰማም፡፡ እነዚህ የሴት መሪዎች አልፈዋል፡፡ ነገር ግን ሥራቸው ለዘለዓለም ይኖራል፡፡ ትውልዱ ግን ብዙም አያውቋቸውም፡፡ ምክንያቱም አልጠየቁም፡፡ የቀደሙትም አልተናገሩም፡፡ እኔ ይህንን መልእክት የማስተላልፈው ለአሁኑ ትውልድ ነው፡፡ የሀገራችሁን ታሪክ አንብባችሁ እና ጠይቃችሁ እወቁ፡፡ ግድለኛ ወንዶችም ሴቶችም ያሏት ድንቅ ሀገር አለቻችሁ፡፡ የጾታ ልዩነት ሳታደርጉ ሁሉንም መርምራችሁ እወቁ፤ የሚደነቁትን አድንቁ፣ አርአያ የሚሆኗችሁን ተከተሉ፡፡ ለዛሬ በድጋሚ እንኳን ለ127ኛ የአድዋ ድል አደረሰን፣ ለነጻነታችን ዋልታ የሆኑት የአጼ ምኒሊክ እና የእቴጌ ጣይቱ የሀገር ወዳድነት እና አርአያነት ይጋባብን! ሴቷ መሪ ትወደስ! ጨርሻለሁ!

by Fitsum Kidanemariam

Share on your socials!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *