
አብዛኛውን ጊዜ አለም የምትሰጠን የሰጠናትን ቆጥራ ነው፡፡ በእርግጥ ይሄ ሁልጊዜ ላይገጣጠም ይችላል፤ አብላጫውን ማለቴ ነው፡፡ ይህንን ጽሑፍ የምትጽፈው ኮንፈረንስ ለመካፈል ከተሻገርኩበት ባር ማዶ ሰማይ ስር ነው፤ በአሜሪካ ላስ ቬጋስ የሚካሄደውን የሰው ሀብት ማኔጅመንት አለም አቀፍ ኮንፈረንስ ለመሳተፍ፡፡ የኮንፈረንሱ ቀን ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ቀደም ብዬ ስለመጣሁ በጓደኛ እና ቤተዘመድ እንክብካቤ ውስጥ ነኝ በዲሲ እና አካባቢው፡፡ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ሀገራትን የማየት እድል ቢገጥመኝም ይቺን (አልኩ እነዴ ማለቴ እነዚህን) አሜሪካ ስረግጥ ግን የመጀመርያዬ ነው፡፡ እናም በጣም ለማየት የማያ አካሎቼን ከፍትፍት አድርጊያለሁ፡፡ ቆይታዬ አዲስ ስለሆነ ያየሁትን እያየሁ ምንም እንኳን ለአንዳንዶቻችሁ አዲስ ባይሆንም ለእኔና ከዚህ ቀደም ላላያችሁ አዲስ የሆነውን ግን የምንሰማውን በአየሁት ልክ ላጋራችሁ ወደድሁ፡፡ በእርግጥ የአሁኑ ጉዞዬ ለአሜሪካ አዲስ ይሁን እንጂ ከአስር ያላነሱ ሀገራትን በተለያዩ ጊዚያት ስላየሁ እይታዬ የድምር ውጤት ሆኖ ይቆጠርልኝ፡፡ ትኩረቴም ስራ እና ስራ ነው፡፡
እኛ ሀገር አባባል በሽበሽ ነው፤ ለምሳሌ ስራ ክቡር ነው፤ ስራ ያስከብራል፡፡ የሚለውን አባባል ከልጅነታችን እስከ እውቀታችን (አዋቂነታችን ዘመን ለማለት ነው) ስንሰማው አድገናል፡፡ እኛ ግን በአንጻራዊነት ክብር ያለመፈለጋችንን በደንብ ያመንኩበት አጋጣሚ ነው ያገኘሁት፡፡ እኛ ወደ መንግስት ይሁን መንግስታዊ ያልሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ስንሄድ ከቤታችን ስንወጣ “ጉዳዬን ላስፈጽም” ብለን ሳይሆን በስጋት በታጀበ ሀሳብ ተውጠን ነው፤ “ባልጠመሙብኝ፣ በቀናኝ፣ ባገኘኋቸው፣ ስብሰባ ላይ ባልሆኑ፣ በጎን ክፍያ ወይንም ሙስና ባልጠየቁኝ፣ ወረፋ ባልሆነ…ወዘተ”፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አገልግሎት ሰጪዎቻችን ስራቸውን እየሰሩ ስላይደለ መሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ ተጠያቂነት ስለሌለ እና ሰሩም አልሰሩም ደመወዛቸው ስለማይቆረጥ ወይንም ከስራቸው ላይ የሚያነሳቸው አካል ስለሌለ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ደጅ አፍ ተኮልኩሎ የሚውለው ሰው በሀገራችን ሁልጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ ወይንም የሆነ የንግስ በዓል ያለ ያስመስለዋል፤ ደስተኛ ከሚሆነው ሰው ይልቅ አማራሪ ይበዛል፤ ጠቅለል ሲደረግ “የማያልፍላት ሀገር!” እንላታለን፡፡
ግን ደግሞ ሁላችንም የዘራነውን እያጨድን አይመስላችሁም!? ብዙዎቻችን በየአገልግሎት ሰጪዎቻችን የምናገኘውን ምሬት እኛም በተሰማራንበት ስራ ላይ እያማረርን እንደሆነ ልብ ብላችኋል?! ምክንያቱም ሁላችንም የእኛው ማህበረሰብ እና ባህል አባላት ነን፡፡ እያንዳንዳችን የምናደርገው አስተዋጽዎ ነው መልሶ እኛኑ እያማረረን ያለው፡፡ እኔ በዚች በጥቂት ቀናት ከአውሮፕላኑ ወርጄ እስከ ቆየሁባቸው ጥቂት ቀናት ያስቀኑኝን ነገሮች ልንገራችሁ፡፡ እዚህ በስራ ላይ ያሉ ሰዎች ሰው ላይ አያፈጡም፤ አይደለም ማፍጠጥ ቀና ብለው አያዩም፤ ለዚያ የሚያባክኑት ሰዓት የላቸውም፤ ወይንም ያንን ቢያደርጉ የሚመለከታቸው እና የሚቀጣቸው ሲስተም ወይንም አካል አለ፡፡ ስለዚህ ዋና ትኩረታቸው ስራቸው ላይ ብቻ ነው፡፡
እኛ ጋር ሲስተሙ የሚባለው አካል አልደረሰም፤ ወይንም እንዳይደርስ በሩ ተዘጋግቶበታል፡፡ ይህንን የእነሱን ትኩረት ወደ እኛ ስንመነዝረውስ? እየሰራን ጸጉረ ልውጥ ሰው ስናይ በስነ ስርዓቱ ስራችንን አቁመን ያውም በማፍጠጥ እና በመገረም እናያለን፤ አይተንም በእንግዳ ተቀባዩ መንፈሳችን “ይሄ/ይህች ደግሞ ከየት የመጣ/ች ነው/ናት?” ብለን ስለላዊ እና ጉጉታዊ ጥያቄ ወይ ለእራሳችን አልያም አካባቢያችን ለሚገኝ ሰው እናቀርባለን፤ ቢመለከተንም ባይመለከተንም ይህንን ከማድረግ የሚያግደን የለም፡፡ እነዚሁ ሰዎች ለጉዳይ ወደቢሯችን ሲመጡ በተጠራጣሪነት መንፈስ ስለምንቀበላቸው ችግራቸውን ከመፍታት ይልቅ ተጨማሪ ችግር እንሆንባቸዋለን፡፡ ምክንያቱም የፈለገንን ብናደርግ የሚጠይቀን ሲስተም የለማ! እናም ይኸው እየተማረርን እና ሌሎችንም እንዲመራመሩብን ምክንያት እንደሆንን አለን፤ ወደፊትም እንኖራለን፡፡
እነሱ ብዙ ጉዳያቸውን በስልክ ወይንም በጽሑፍ መልእክት ይጨርሳሉ፡፡ ስለዚህ ሲስተሙን እንጂ ሰዉን አያውቁትም፡፡ የሚመሰጋገኑትም በስልክ ነው፤ የሚወቃቀሱት ካለም እንደዚያው፡፡ ይህ ደግሞ በብዛታቸው ልክ ጎዳና ላይ እንዳይፈሱ አድርጓቸዋል፤ ሕይወታቸውንም አቅልሎላቸዋል፡፡ አሁንማ ስራቸውን ከቤታቸው መስራት እያዘወተሩ ነው፡፡ እድሜ ለኮቪድ ባይባልም፡፡ እኛ ደግሞ አሁንም መንገድ ላይ ነን፡፡ ለእያንዳንዱ ጉዳያችን ከቤታችን መውጣት አለብን፤ በጠዋት ተነስተን ከያለንበት እንተማለን፤ እንገፋፋለን፤ እንሻማለን፡፡ ይሄ ደግሞ ከጥቃቅን እና አነስተኛ አንስቶ እስከ ከፍተኛ ጸብ ይዳርገናል፡፡ በትራንስፖርቱ ጸብ፣ በሰልፉ ጸብ…ወዘተ፡፡ ምክንያቱም እኛ ጋር ሲስተሙ የለም፤ ወይንም ከሲስተም ጋር አንተዋወቅም፤ እዚያ ለመድረስ ገና ብዙ መጓዝ ይኖርብናል፤ ቢያንስ የስራ ባህል ሊኖረን ይገባል፡፡ ይህ ባልሆነበት ከቤት ስሩ ብንባል ከስራው ሳይሆን ከእራሳችንም እንጠፋለን የሚል ስጋት አለኝ፡፡ እነሱ እኮ ድሮም ከቤት የመስራት ሲስተም ቢኖራቸውም በተለይ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት አጠናክረውታል፡፡ እኛ ደግሞ ጭራሽ በኮቪድ 19 ምክንያት ከነበረን ትንሽ የስራ ተነሳሽነት ላይ ተቀናንሶብን ወደ የማንሰራበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ እንደዚያም ከቤታቸው እየሰሩ መሰላቸትን አያውቁት እንደሆነ እንጃ ጎዳና ላይ ብዙም አይታዩም፤ ኸረ ትንሽም አይታዩም፡፡ ምናልባትም ከታዩ ውሾቻቻን በቄንጠኛ ቀበቶ አስረው ሲያንሸራሽሩ ነው፡፡ እያንሸራሸሩ ውሻቸው ሲጸዳዳ የያዙትን የኪስ ላስቲክ መዥረጥ አድርገው ሲያጸዱ ነው፤ አቤት ስነ ስርዓት! ማለቴ ሲስተሙ ደስ ሲል! እኛ ሰፈር እንኳን የውሻ ቆሻሻ የራሳችንን ቆሻሻ የምናስወግድበትን ለቅጽበት አስታውሼ “እውነት ተመሳሳይ ምድር ላይ ነው ያለነውን! እውነት ሀገራችንን ስለምንወዳት ይሆን እንደዚህ የምናቆሽሻት? እንደዚህ ቆንጥረን በሚጢጢ የምንሰራላት? ነው ወይንስ ይሄ ሲስተሙ የሚባለው ነገር እኛ ስለሌለን ነው?” ሲከነክነኝ ውሎ አደረብኝ፡፡ መከንከን ብቻ እንዳይመስላችሁ፤ ቅናቱንም አልቻልኩትም፡፡ ቶሎ ኮንፈረንሴን ተሳትፌ የምመልበት ቀን እንዴት እንደናፈቀኝ ልነግራችሁ አልችልም፡፡ እንዴ ቅናት መጥፎ ነዋ! ሲስተሜን ማለቴ ሀገሬን ቢያስክደኝስ?
ስራን ማክበር እንደሚያስከብር በደንብ ያየሁበት ሀገር ስለመጣሁ ደስ ብሎኛል! ይመቻቸው! ይገባቸዋል! ስራም፣ ገንዘብም፣ ሲስተምም፣ ብቻ ለዚህ ዓለም ጠቃሚ ነገሮች አክባሪያቸውን ያከብራሉ፡፡ ሲስተሙን ወደ እኛ የሚያመጣልን ጀግና እስክናገኝ በዚያም ታግዘን ስራችንን አክብረን የምንከበርበት ዘመን እስኪመጣ ሲስተማቸውን እያደነቅን እንኖራለን፡፡ ዳግም የማየውን አይቼ እስክመለስ እስቲ የስራ ባህላችንን እና ሲስተማችንን እንዴት እንለውጠው የሚለው ላይ እያሰብንበት የየግላችንን ጥረት እንቀጥል፤ እስከምንጣመር እና ሲስተም እስኪኖረን! ለዛሬ ብቻ ጨርሻለሁ! በሚቀጥለው አስክመለስ ቸር ያገናኘን!