ምድር ትናወጣለች

ታህሣስ እና መጋቢት ወራት ሲመጡ ብዙ ገመናዎች ይወጣሉ፤ እናም ግርም ይለኛል፡፡ ታህሣስ ወር የስነ ፆታ ጥቃት ይቁም በሚል የሚደረገው የ16 ቀን ንቅናቄ ሲሆን መጋቢት ደግሞ በማርች ስምንት አከባበር ላይ የሚተላለፉ መልእክቶች ናቸው፡፡ በተለይ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ውስጥ በደንብ ቦታ ተሰጥቷቸው ይከበራሉ፡፡ አሁን አሁን አንዳድን መንግስታዊ ድርጅቶች እና የግል ተቋማትም ማክበር ወይም ጊዜ መስጠት ጀምረዋል፡፡

ገመና ያልኳችሁ በቅጥር ዘመኔ አብረውኝ የሚሰሩ ብዙዎች የወንድ የሥራ ጓደኞቼን እና አንዳንድ የሴት ጓደኞቼን አስታውሼ ነው፡፡ በግብረ ሰናይ ድርጅት ሥራ ላይ መሰማራት ከመደበኛ ሥራችን ውጪ ብዙ ዓለማቀፋዊ ንቅናቄዎችን እንድናውቅ እድል ይሰጠናል፤ በእድሉ ከተጠቀምን፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በተቃራኒው እይታችን ቅርብ ነው (Short sighted) እንደማለት፡፡ እናም ሴት ስትባል የሚታየን ቢሮ ውስጥ አብራን የምትሠራውን፣ ትምህርት ቤት አብራን የተማረችውን አልያም በየቤታችን በወላጆች እቅፍ ያለችውን ነው፡፡ ከላይ በጠቀስኳቸው ወራት መ/ቤታችን ውስጥ ለማክበር ደፋ ቀና ስንል በተለይ ባለቅርብ እይታዎቹ ወንዶቹ የማይሉን የለም፤ እስቲ እናንተ ምናችሁ ተነካ፣ ከእዚህ በላይ የምን እኩልነት ነው የምትፈልጉት፣ ሴት ልጅ ተለከፍኩ ብላ ጉራ ከረዩ (ይሄ ነገር ግን አማርኛ ነው?) የምትለው በልቧ ደስ እያላት ስታስመስልና የውሸቷን ነው…ወዘተ ይሉን ነበር፡፡ ባለቅርብ እይታዎቹ ሴቶች ደግሞ \”እኔ ሴቶች ምናምን ሲባል ይደብረኛል\” የሚሉት አባባል አላቸው፡፡ በነገራችን ላይ ሴቶች የሚለው ቃል ከተነሳ \”ምናምን\” የሚለው ቃል እንደ አባት ሥም በወንዶች ብቻ ሳይሆን በሴቶችም ጥቅም ላይ እየዋለ መጥቷል፡፡ በቅርቡ እራሱ አንድ ስልጠና ቦታ ባለሙያ ሴቶች ተዋውቄ ስለኤውብ ሳወራላቸው \”ይሄ የሴቶች ምናምን በየወሩ እንኳን ሂልተን የሚካሄደው?\” ሲሉኝ ጠላታችሁ ክው ይበልና ክው ነው ያልኩት፡፡ ምናምን ያለችውን ሴት የበለጠ እንድታብራራልኝ ጠይቂያት መልስ አልነበራትም፡፡ ወንዶች እንኳን መቼስ ገና ለለውጥ ዝግጅት ላይ ናቸው እንበል፡፡ እኛ ሴቶቹ እራሳችን ካልተለወጥን፣ የሚገባንን ካላወቅን ታድያ ማን መጥቶ መብታችንን ሊያስከብርልን ነው? ቢያንስ ሴቶች ብለን ምናምኑን ላላመኑብን ብንተወው!?

\”የስነ ፆታ ጥቃት ይቁም\” ብለን ድምጽ ማሰማት የጀመርነው ከዓለም በኋላ ነው፡፡ ያደጉት ሀገራትም ቀድመው ጀምረው አሁንም ገና እየታገሉ ነው፡፡ ቢያንስ ግን ብዙ ለውጥ ለራሳቸውም ለሀገራቸውም እያመጡ ስለሆነ ድምጻቸው አይታፈንም፡፡ እኛም እንዲያው ለነገሩ ዛሬ ይታፈን እንጂ ልጆቻችን ወይንም የልጅ ልጆቻችን አልያም የእነሱ የልጅ ልጆች ለውጡ ላይ ይደርሱበት ይሆናል፡፡ በተለይ ደግሞ የገጠሯ እናት ልጆቿ ሲማሩ እና ሰብአዊ መብት ምን እንደሆነ ሲያውቁ ከዚያም የስነ ጾታ ጥቃትን አስከፊነት ተገንዝበው እራሳቸውን መከላከል ሲጀምሩ ያን ጊዜ የእኛ ምድር ትናወጣለች፡፡ ይህቺኛዋ አለም፤ በሴቶች የሚያላግጡ፣. ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ፣ ሴቶችን እንደ መገልገያ የሚያዩ፣ ሴቶችን አቅመ ቢስ አድርገው የሚቆጥ፣ ሴት የሚለውን ቃል እራሱ ለስድብ የሚጠቀሙ፣ እናትህን/ሽን እንዲህ ላድርጋት (ልድፈራት) ብለው የሚሳደቡ ሰዎች ያሏት ምድራችን ትናወጣለች፡፡

በነገራችን ላይ የስነ ጾታ ጥቃት (Gender Based Violence) ይቁም! የሚለው ንቅናቄ በዋናነት ተጠቂዎቹ ሴቶች ስለሆኑ የሴቶች ጩኸት ቢመስልም ቅሉ ጥቅልሉ ሲፈታ ግን በማንኛውም ጾታ ውስጥ ያሉ ሰዎች ጥቃት እንዳይደርስባቸው እና በሰላም የመኖር መብታቸው እንዲከበር ነው፡፡ ለምሳሌ ነርስ የሴት ሥራ ነው ብሎ ነርሲንግ ያጠናውን ወንድ ለጾታህ የማይመጥን ሙያ ነው ብንለው ሳይኮሎጂካል ጥቃት እያደረስንበት መሆኑን ላስታውሳችሁ፡፡ ሴቷን ዶክተር \”ዶክተሩን ጥሪልን\” እንደማለት ማለት ነው፡፡ የስነ ጾታ ጥቃት ሲባል አስገድዶ መድፈር ብቻ የሚመስለን ብዙዎች ነን፡፡ እስቲ ሀሳቡን ከመቃወማችን እና በንቅናቄው የሚሳተፉ (የምንሳተፍ) ሴቶች የተለየ ስያሜ ከመስጠታችን በፊት ስለ ሀሳቡ እና ንቅናቄው በደንብ እንረዳ? እስከመቼ ነው ባልተረዳነው ነገር ተቃዋሚዎች ብቻ ሆነንስ የምንቀረው? መቼ ልንረዳ እና ልንረዳዳ ነው!? እኔ አሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ስልጠና ለመስጠት አይደለም፤ መች ጠየቃችሁኝና! ግን እንዲሁ የተሰማኝን እና ያየሁትን ለመተንፈስ ነው፡፡ በእነዚህ ወቅቶች መ/ቤቶቼ ውስጥ የነበሩትን ተመሳሳይ አመለካከቶች እና ጉምጉምታዎች አስቤ እንዲያው ውስጤ ይዤው ከምቀር ላፈንዳው ብዬ ነው፡፡ እመኑኝ ሀገር የምታድገው የስነ ጾታ እኩልነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው አራት ነጥብ!

የሴቷጉዳይ ወንዱን የወንዱ ጉዳይ ሴቷን ካልቆረቆረን፤ ለችግራችን መፍትሔ እየሰጠን ካልሄድን ወደፊት መጓዝ አንችልም፡፡ እንዴት ነው ሴት ስለሆንሽ አንቺ አይመችሽም እሱ ይሥራው የምትባል ሴት ወደመሪነት የምትመጣው? እንዴት ነው ሴት ይመስል ጓዳ ትርመጠመጣለህ የሚባል ወንድ መልካም አባወራነቱን የሚቀጥለው? እንዴትስ ነው የሴት አለቃ አትመቸኝም በሚባልበት የሥራ ኃላፊ የሆኑ ሴቶች ማውጣት የሚቻለው? እንዴት ነው ባልማ ትንሽ ገጨት ካላደረገ ምኑን ወንድ ሆነ እየተባለ ያደገ ወንድ ሚስቱን እንደሚስት የሚያከብረው? ልቀጥል? ምን በወጣችሁ! ቢዘረዝሩት ያማል፡፡

ምድራችን ትናወጥ እስቲ ይውጣላት! ያልደፈረሰ አይጠራም ያሉት ቀደምቶቻችን በምክንያት ነው፡፡ እስቲ ሁላችንም ዝም ብለን በጭፍን ከመቃወማችን በፊት በደንብ በጥልቀት እንመርምር፤ እንማር፡፡ ይህንን ስናደርግ ከድርጊታችንም እንታቀባለን እና በሰበቡ መፍትሔም እየሆንን እንጓዛለን ማለት ነው፡፡ እናንተ ደግሞ በየቢሮው ያላችሁ የገባችሁ ሳትሆኑ ጥቂቶቹ ያልገባችሁ ሴቶች ከቅርብ እይታ ተላቀቁ፡፡ አርቃችሁ ተመልከቱ! እናንተን እና ቤታችሁን ከማየት አልፋችሁ 80% የሚሆኑት የሀገራችን ገጠራማ ክፍሎች የሚኖሩትን ያልተማሩ፣ በጨቅላነታቸው ተድረው መአት ልጆች እየወለዱ የሚያሳድጉ፤ ያልተጫሙ፣ ያሊያጌጡ፣ እያረሱ ያልቃሙ፣ ውሀ ለመቅዳት እንደእናንተ የጓሮ ቧንቧ የማይከፍቱ፣ ማገዶ ለማምጣት ከጅብ የሚታገሉ፣ ለመውለድ በአልጋ ሳይሆን በቃሬዛ የሚጫኑ ብቻ እየኖሩ ሳይሆን እያኗኗሩ ያሉትን ሴቶች አስቡ፡፡ ዳሩ እንደእነዚህ ያሉ ሴቶች በከተማችንም ሞልተውናል፡፡ እና አርቀን እንይ! ገመናችንን እንሸፍን! የስነ ጾታ ጉዳይ የሴቷም የወንዱም ጉዳይ ሳይሆን የሁላችንም ጉዳይ ነው፡፡ እውቀታችንን ለበጎነት እንጠቀምበት፣ የማናውቀውን ለማወቅ እንትጋ፣ ሳናውቅ አንቃወም! ዘመናዊ እንሁን! ለዛሬ ጨርሻለሁ!

ፍፁም አጥናፍወርቅ ኪ/ማርያም