ብዙ ጊዜ በስኬታማነታቸው የሚወደሱ ወንዶች ሲገጥሙን \”ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጀርባ ብርቱ ሴት\” አለች ይባላል፡፡ እውነትም ደግሞ ስኬታማው ሰው ምስክርነቱን የመስጠት እድል ሲሰጠው ከእናቱ ይጀምራል፤ ትዳር ውስጥ ከሆነ ደግሞ ሚስቱን ያወድሳል፡፡ አንዳንዴም እንደ እናት ሆና ያሳደገችኝ ታላቅ እህቴ በማለት የሴቷን በሕይወቱ ውስጥ ያደረገችውን አስተዋጾ ይናገራል፤ ያመሰግናል፡፡ ልክ ይህንን እየጻፍኩ ማን ትዝ እንዳለኝ ታውቃላችሁ? የአሜሪካው የመጀመርያው ጥቁር ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ፤ አቤት ስለሚስቱ ስለ ሚሸል ሲናገር የነበረ ደስታ፣ የእንባ መራጨት፣ የሴት ልጃቸው ስሜት በአጠቃላይ ድባቡ ከአእምሮዬ አይጠፋም፡፡ ለነገሩ እዚያ ድረስ ምን አስኬደኝ እናንተዬ! የእኛ ጠቅላይ ምኒስትር  ዶ/ር አብይ አህመድ ስለ እናታቸው እና ስለሚስታቸው የተናገሩት ምናልባትም ባህለ ሲመት ሲደረግ በጠቅላይ ሚኒስትር ከተደረጉ የቤት ውስጥ ደጋፊ ሴቶችን አክባሪ ንግግሮች የመጀመርያው ሳይሆን አይቀርም፤ ከተሰሳትኩ ለመታረም ዝግጁ ነኝ!

እኛ ኤውቦች ደግሞ ከእያንዳንዷ ስኬታማ ሴት ጀርባ ብርቱ ወንድ እንዳለ በተለያዩ አጋጣሚዎች በተለይ ደግሞ የላቁ ሴቶች በሚሸለሙበት ወቅት የምንሰማው ሐቅ ነው፡፡ በኤውብ የላቁ ሴቶች በዓመት አንዴ እንደሚከበሩትና እንደሚሸለሙት በየወሩ አርአያ የመሆን አቅም ያለው የሕይወት ጉዞ ያላቸው ሴቶች ትውልድ እንዲያነበው ኤውብ ድህረ-ገጽ Spotlight በሚለው ገጽ ላይ ይከተባል፡፡ ትኩረት (Focus) የሚለውም ለየት ባለ መልኩ የሴቷ ድንቅ ሥራ የሚወጣበት ገጽ ነው፡፡ ታድያ በአብዛኛው ሴቶች እንደ ወንዶቹ ሁሉ ከእናታቸው እና ከታላላቅ እሕቶቻቸው ወይንም ሴት አለቆቻቸው በተጨማሪ አባቶቻቸውን፣ ባሎቻቸውን እና ወንድሞቻቸውን በዋና ደጋፊነት እና አበረታችነት ይጠቅሷቸዋል፡፡

በኤውብ እንደዚህ ደጋፊ የሆኑ ወንዶች \”ምኒልክሽ\” ይባላሉ፡፡ እንግዲህ የአጠራሩ ስርወ ቃል ግልጽ ቢሆንም ትንሽ ማብራርያ ላክልበት፡፡ አጼ ምኒሊክ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ቀንበር ነጻ በማድረግ ትውልድ ሁሉ ሲዘምርላቸው የሚኖሩ የኢትዮጵያ ንጉስ ነበሩ፡፡ ከጀብንነታቸው ጋር አብሮ መወሳት ያለበት ቀደም ሲል በነበሩት ነገስታት ባልተለመደ መልኩ ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ብጡልን ስትራተጂክ በሆኑ ጉዳዮች ያሳትፏቸው ነበር፤ በመሆኑም ለአድዋ ድል ትልቅ አስተዋጾ ማበርከት ችለዋል፡፡ እቴጌ ጣይቱ ከዘመናቸው የቀደሙ ነበሩ ይባላል፤ አማርኛ መጻፍና ማንበብ፣ ግእዝ መናገር፣ በገና መጫወት እና ግጥምም መጻፍ ይችሉ እንደነበረ ይነገርላቸዋል፡፡ አዋቂነታቸው ከዚያም በላይ ሆኖ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ሚና ይጫወቱ ነበር፡፡ ለምሳሌ የአጼ ምኒልክን አስተዳደር ለማስፋት ተቀናቃኝ ሊሆኑ ይችላሉ የሚሏቸውን መሪዎች እያነፈነፉ በጋብቻ መዛመድ አንዱ መሣርያቸው ነበር፡፡ እንግዲህ ከጣልያን ጋር በተደረገው ፍልምያም የራሳቸው ጦር ይዘው ከመዝመት ጀምሮ በመጨረሻ ለድሉ ወሳኝ ሚና ነበር የተባለለትን የታልያን ጦረኞችን ውሀ የማስጠማት እና ከምሽጋቸው አስወጥቶ የማስደምሰስ ስልታዊ ምክር የእሳቸው ነበር፡፡

ታድያ ይህንን ሁሉ የእቴጌ ብጡል እምቅ ችሎታ አጼ ምኒልክ  እንደዘመናቸው ሁሉ ሽፍንፍን አድርገው እንደብዙዎች ባሎች (በዘመናችንም ሞልተዋል) በጓዳ ቢያስቀሩት ኖሮ የዛሬ የኢትዮጵያ ገጽታ ምን እንደሚመስል መገመት ይቻል ይሆን? በጭራሽ! አጼ ምኒልክ ባለቤታቸውን ያከብሩ ነበር፤ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሳትፉ ነበር፤ ያማክሯቸው ነበር፤ ያበረከቱትን አስተዋጾ አጉልተው ያወጡም ነበር፡፡ ለምን ይሆን እንደዚህ ያሉ ባሎች ያልበዙልን? አይይ የእኔ ነገር ወደ ሌላ ጣብያ (ወደ ብሶት አደባባይ) ገባሁ!

እንግዲህ ከላይ ወደ ተነሳሁበት ሀሳብ ስመለስ ኤውብ ሚስቶቻቸውን፣ ልጆቻቸውን፣ እህቶቻቸውን፣  የሥራ አጋሮቻቸውን እና በሌላም የሕይወት አጋጣሚ የሚያውቋቸውን ሴቶች የሚያግዙ፣ የሚያበረታቱ እና የሚያነቃቁ ወንዶችን ምኒልክሽ ትላቸዋለች፡፡ መድረክ እያዘጋጀችም እንዲሳተፉ ማለትም የሆኑትን የሆኑበትን ምክንያት፣ መልካምነታቸውን፣ ጥንካሬያቸውን…ወዘተ እንዲያጋሩ ታደርጋለች፡፡

ሕይወት ስኬታማ የሚሆነው በግል በሚደረግ ጥረት ብቻ አይደለም፤ በመደጋገፍ እንጂ፡፡ በተለይ ደግሞ ወንድ ልጅ ስኬታማ ይሆን ዘንድ ለብቻው አይቻለውም፤ ለሴቷም እንዲሁ፡፡ ፈጣሪ ሁለታችንን ወደ እዚች ምድር ያመጣን አንዳችን የሌላችን ጎዶሏችን ሞልተን በሙሉአችን አሸናፊዎች እንድንሆን ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የግል አስተዳደጋችን፣ ባህላችን ወይንም ተምእሮአችን የአንዳችንን ለሌላችን ያለንን ጠቃሚነት፣ አስፈላጊነት፣ ደጋፊና ተደጋጋፊነት ከማጉላት ይልቅ እንድንጨፈልቀው ይጫነናል፤ አለመታደል!

በዚህ ዙርያ ብዙ ገጠመኝ አለኝ፡፡ የአንዱን የባልና ሚስት ገጠመኜን ለምሳሌነት ላጋራችሁ፡፡ እኔ የማውቀው ባልየውን ስለነበረ ገጠመኙ ከእራሱ የተነገረኝ ነው፡፡ ሚስቱ በጣም ብልህ ሴት እንደነበረችም እኔም አውቃለሁ፤  በተለምዶ አጠራር የቤት እመቤት ነበረች፤ ግን ደግሞ ኑሯቸውን በኢኮኖሚ ለመደጎም በንግዱ እየተሯሯጠች ለኑሯቸው ጥሩ ገንዘብ ታስገኝ ነበር፡፡ የአቅም ችግር አልነበረባትም፡፡ እሱ ቢሮ ስለሚውልና የቢሮ ፕሮቶኮል ስለሚጠብቅ ሁልጊዜ የተስተካከለ አለባበስ ነበረው፡፡ እሷ ደግሞ እቤት ሥራዋን ሠርታ ከዚያ ደግሞ ተሯሩጣ ሠርታ ስለምትገባ አለባበሷ ለእሷ እንዲመቻት ሆኖ እንደነገሩ ነበር፡፡ እንደ አጋጣሚ በለስ ቀንቷቸው አብረው ሲሄዱ ለሚያያቸው ባልና ሚስት ናቸው ብሎ መገመት ያስቸግር ነበር፡፡ በጋራ ተመካክረው ማድረግ ያለባቸውን ነገሮች በግሉ ይወስን ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዚያት እንዲነጋገሩ ሀሳብ ብታቀርብም ለውይይት በር አይከፍትም ነበር፤ ይልቁንም ይሸሻል እንጂ፡፡ ታድያ ያቺ ሴት ሲበዛባት ትምህርት ሲዘጋ ጠብቃ በቤተሰቦቿ ጋባዝነት ለልጇ እና ለእሷ ለጉዞ የሚያስፈልጋቸውን አሟልታ አሜሪካ ከሄደች በኋላ እንደማትመለስ ከዚያው አበሰረችው፤ በጥቂት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እዚያው ትዳር መሰረተች፤ ደስ ብሏትም እየኖረች ትገኛለች፡፡ አባወራው በፀፀት እና በቁጭት ኑሮውን በአሳር እየገፋ ይገኛል፡፡  የዚህ ዓይነት ወንዶች ብዙ ናቸው፡፡ መቼስ በየፊናችን ሌሎችንም ብዙ እናውቃለን፡፡

እንግዲህ የዛሬ መልእክቴ የስኬታማ ሴት አጋር የሆኑትን እነ ምንልክሽን ከማስተዋወቅ በተጨማሪ እኛ ሰዎች አፈጣጠራችን አንዳችን የሌላችንን (የተቃራኒ ጾታን) ጎደሎ ወይንም ክፍተት ለመሙላት ነውና በሕይወታችን ወሳኝ አስተዋጾ ያደረጉትን እና እያደረጉ ያሉትን  ወንዶች ማመስገን ይልመድብን የሚል ነው፡፡ ልምዱ ካለን ይዝለቅብን ለማለት ነው፡፡ ኤውብ ታመሰግናለች፡፡

ፍፁም አጥናፍወርቅ ኪ/ማርያም