ሜይ ፎረም ሕልሜን ፈታልኝ!

መቼስ ጥሩ ነገር ስናይ \”የእኔ በሆነ\” ብለን መመኘት ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ከእለታት በአንድ ወቅት በመ/ቤቴ አማካይነት ዓለም አቀፍ የሴቶች ስብሰባ ላይ ለመታደም እድል አግኝቼ ወደ አውስትራልያ ሄድኩኝ፡፡ ያንን ስብሰባ ለመሳተፍ ከ90 ሀገራት በላይ የተውጣጣን ከ1000 ያላነስን ተሰብሳቢዎች ተገኝተን ነበር፡፡ ስብሰባውን ካዘጋጁት እስከመሩት ድረስ ያሉት በሙሉ ሴቶች ነበሩ፡፡ በስብሰባው ቦታ እስክንደርስ የነበረው መጓጓዝ ሳይቀር የተቀነባበረው በእነዚሁ ሴቶች ነበር፡፡ ዝግጅቱ የተጀመረው በስብሰባው እለት ዋዜማ ላይ በተደረገ የእንኳን ደህና መጣችሁ ልዩ ዝግጅት ነበር፡፡ ዝግጅቱ ላይ ለመታደም ተሳታፊዎች ሁላችንም ከያረፍንበት ሆቴል የየሀገራችንን ባህላዊ አልባሳት ለብሰን ወደ ትልቁ አዳራሽ ግቢ ተመምን፡፡ በደረስን ጊዜ በመግቢያው ላይ የተደረደሩት አዘጋጆች በየስማችን የተዘጋጀ መለያ መታወቅያ እና በየሀገራችን ስም የታተመ አርማ አለበሱን፡፡ በሚገርም ፍጥነትና ቅልጥፍና እየተስተናገድን ወደ ዝግጅቱ ገባን፤ በማግስቱም ስብሰባ አዳራሹ ውስጥ ስንገባም ጠረጴዛችንን መለየት አልከበደንም፤ በየሀገራችን እና ስማችን ተሰይሞ ስለነበር፡፡ ስብሰባው ልክ በሰዓቱ ተጀመረ፤ የሻይ እና የምሳ እረፍቱም ሁሉ በሰዓቱ ነበር፤ ዝንፍ የለም፡፡ ይህ በአምስቱም ቀናት ቆይታችን ሆነ፡፡ በነገራችን ላይ ስብሰባው የዓለም አቀፍ የወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወሴክማ) በየአራት ዓመቱ የሚያደርገው ጉባኤ ነበር፡፡
በቃ ምድር ላይ ሳይሆን ሌላ ዓለም ላይ የቆየሁ እስኪመስለኝ ቆይታዬ በአግራሞት ተጠናቀቀ፡፡ ወደ ሀገሬ ስመጣ ያሳለፍኩትን እያውጠነጠንኩ ነበር \”እውን እንደዚህ ያለ ስብሰባ በእኔ እድሜ በሀገሬ ላይ እመለከት ይሆን?\” እያልኩ:: ከዚያ በኋላም የተለያዩ ስብሰባዎች በተሰበሰብኩ ቁጥር ያንን እሩቅ ሀገር ያየሁትን እያስታወስኩ ሀሳቤ መጠየቁን እኔም ሆኖ ማየት ማለሜን እና መመኘቴን አላቆምኩም፡፡
የመጀመርያውን የሜይ ፎረም የተካፈልኩ እለት ስካርን በእውኑ ባላውቀውም በደስታ መስከሬን አስታውሳለሁ፡፡ የተመኘሁት ያለምኩት እውን የሆነ ያህል ነበር የተሰማኝ፡፡ የኤውብ መስራቾቹ ናሁሰናይ እና ዶ/ር ሮማን በደገሱት የፎረም ድግስ ላይ ተፍ ተፍ እያሉ ያስተባብራሉ፤ በወቅቱ የነበሩት የቦርድ አባላትም እንዲሁ፡፡ በታሪኬ ለመጀመርያ ጊዜ በሀገሬ ምድር፣ በዩኤን ኢሲኤ የተንጣለለ አዳራሽ ውስጥ ከ500 የማያንሱ ሙያተኛ (ፕፌሽናል) ሴቶች ተሰብስበው አየሁ፡፡ መርሀ ግብሩም እጅግ የተቀነባበረ ነበር፡፡ በተለይ ናሁሰናይ በለበሰችው ፀአዳ ጉርድና ኮት ተመቻችታ ስትሯሯጥና በንፋስ የምትገፋ ይመስል ከሰው በማይጠበቅ ፍጥነት ጠረጴዛ ላይ ፈጥና በመውጣት እየቆመች ድምፅዋን ከፍ አድርጋ አንዳንድ መልእክቶችን ስታስተላልፍ መቼም ከአእምሮዬ አትጠፋም፡፡ ከቆምኩበት ጥግ ቀድሞ ወዳየሁት እና \”በሀገሬ ሆኖ አየው ይሆን?\” ወዳልኩት ስብሰባ በምናቤ ጭልጥ ነበር ያልኩት፡፡ ከምናቤ ስነቃ ፊቴ ላይ ኮለል ያሉ የእንባ ዘለላዎች ነበሩ፤ የደስታ ዘለላዎች፡፡ ነብሷን በገነት ያኑረውና ዘሚ ዩኑስ አውቃብኝ ኖሮ ጠየቀችኝ፡፡ ስሜቴን ነገርኳት፤ \”ይገርማል እያለቀሰ የሚስቅ ደማቅ ዓይን አለሽ!\” በማለት አሞካሸችኝ፡፡ ያቺ ቀን የማከብራትን እሷን በቅርበት ለመተዋወቅ ምክንያት ሆነች፡፡ የዚያን እለት ከዘሚ ሌላ በተለይ ዩኒቨርስቲ ስንማር የማውቃቸው ግን ከዚያ በፊት ለዓመታት የትም አይቻቸው የማላውቅ የነበሩ ሴቶችንም አግኝቻለሁ፤ ተደሳስተናልም፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ ሜይ ፎረም ሕልሜን ፈትቶልኛል! የእኛ ኤውብ መልስ ሰጥታኛለች፡፡
ውዬም አላደርኩም፤ ድጋሚም አላሰብኩም፤ ወድያው የዚያን እለት የአባልነት ክፍያዬን ከፍዬ አባል ሆንኩ፡፡ እነሆም እየተማርኩ፣ እያደግሁ፣ በቦርድ አባልነት እና በስትራተጂክ አመራርነት እየተሳተፍኩ፣ በማህበሬ ውስጥ ካገኘኋቸው እህቶቼ ጋር እየተደጋገፍኩ፣ እየተመካከርኩ፣ አብሬ ቢዝነስ እየሰራሁ እነሆ አስራ አንድ ዓመቴ፡፡ በሕይወቴ በጣም ደስተኛ ከሆንሽባቸው ቀናት ውስጥ ተብዬ ብጠየቅ የኤውብን ሜይ ፎረም በኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ማየቴ አንዱ ነው እላለሁ፡፡
ሁላችንም ሕልሞች አሉን፡፡ ሕልሞቻችን ሁሉ እውን ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ እውን የሆኑትን ግን ጠብቆ የማቆየት፣ የማሳደግና አብሮ የማደግ ኃላፊነት የእራሳችን ነው፡፡ ሙያተኛ ሴቶችን በአንድ ፎረም ወይም ማህበር የማየት ሕልሜ ተሳክቶልኛል፡፡ የሀገሬ ሴቶች እንደሚችሉ እነሱ የቻሉት ናሁ እና ሮማን አሳይተውኛል፤ እኔም እንደምችል የታመቀ ችሎታዬን አውጥተውልኛል፡፡ ጠብቆ ማቆየት እና ለቀጣዮች ማሳለፍ ደግሞ የእኔ እና የእኛ ኃላፊነት ነው፡፡ ለዚህም እተጋለሁ! አባልነቴን ማቋረጥ ኃላፊነትን ያለመወጣት ስለሆነ ባለእዳ መሆን አልሻም! እኔና ኤውብን የሚለየን ያው የማይቀረው ሞት ብቻ ነው፡፡ የእኔን ሕልም የምትጋሩ ብዙዎች ናችሁ! እንኳን ደስ አለን! እነሆ በኮቪድ ተቋርጦ የነበረው ሜይ ፎረም እየደረሰልን ነው! እዚያው እንገናኝ! ሜይ ፎረም ላይ!