ለውጥ ነውጥ አይደለም!

የዛሬ ጽሑፌን መነሻ ሀሳብ ያገኘሁት ከዓመታት በፊት የሥራ ባልደረባዬ የነበረች ሴት በአንድ ገበያ መሀከል አግኝቼ ከነበረኝ ወግ ነው፡፡ መቼስ እኛ ሴቶች በመጀመርያ ከሰላምታችን ቀጥሎ  መገማመት የተለመደ ነው፤ ውይ ምነው ያን የመሰለ ቅጥነትሽ የት ገባ? ምንም አልተለወጥሽም ምንድነው ነገሩ? አምሮብሻል ጥሩ ደመወዝ እየበላሽ መሆን አለበት? አገባሽ? ወለድሽ? ውይ ምነው?…ማቆምያ ስላሌለው ላቁም እና ወደ ጭብጥ ወጉ ልምጣ፡፡ ይቺ ሴት አሁንም ቀድሞ የምንሠራበት መ/ቤት እንደምትሠራ ነገረችኝ፡፡ የድሮዋ ባልደረባዬ ከሰላምታ ውጭ ያን ያህል የምንቀራረብ ዓይነት አልነበረችም፡፡ ስለዚህ ከሰላምታችን ቀጥሎ በዚያ ግርግር ቆሜ ረዥም ወግ ለመያዝ ይሉኝታ አልነበረብኝም፡፡ እናም “ስላገኘሁሽ ደስ ብሎኛል” ብዬ በማሳጠር ለስንብት ስንደረደር እሷ እቴ ልትለቀኝ አልፈቀደችም፡፡

ለወግ ማጣፈጫ “አንዳንዴ በሚዲያ ላይ አይሻለሁ” በማለት አድናቆት የሚመስል አስተያየት ሰጠችኝ እና “ደግሞ በጣም ብዙ መ/ቤቶች እንደሸሚዝ ለውጠሻል፤ ምንድነው ነገሩ?” በማለት አድናቆቷ ወድያው ተቀይሮ ኮስተር በማለት ምላሼን በጉጉት መጠበቅ ያዘች፡፡ እኔ ምክንያቱማ ብዬ ከማብራራቴ በፊት ጥያቄዋን በጥያቄ መለስኩላት፡፡ “አንቺ አሁን ድረስ እዚያ መ/ቤት እንዴት ቆየሽ?” ከማለቴ ጥፋት እንደሠራ ሰው “ወዴት ወዴት! የእኔን ጥያቄ መልሽልኝ እንጂ!?” አለችኝ ግዴታ ያለብኝ ይመስል፡፡ “መልሱ እኮ ያለው አንቺ ጋር ነው ብዬ ነው፤ ካልሽ እሺ” ብዬ ላስረዳት ስዘጋጅ አቋረጠችኝ እና “እንዴ እኔ ምን አውቄ ነው መልሱ ከእኔ የሚሆነው፣ እኔ እኮ ተደላድዬ አንድ መ/ቤት ቁጭ ብያለሁ፤ የምትሽከረከሪው አንቺ!” አለችኝ የድሮ ወላጆች ቁጣ በሚመስል ቋንቋ፡፡

ከዚህ ቀደም ብዙም አግባብ ካልነበራችሁ ሰው ጋር እንዴት እንደምታወሩ ሁሉ ይጨንቃልም አይደል! ትንሽ አሰብ አደረግኩ እና “ተደላድለሽ የተቀመጥሽው ስለተመቸሽ ነው አይደል? እኔ ደግሞ ተደላድሎ የሚያስቀምጠኝ ምቾት ስላላገኘሁ ነው!” አልኳት፡፡ የገባት አትመስልም ነበር፡፡ ወጋችንን  ላሳጥረው እና እሷ ከዚያ መ/ቤት የማትወጣው ሌላ መ/ቤት መለወጥ የማትፈልገው ሌላ ቦታ መልመድ እና መሥራት የምትችል ስለማይመስላት እንጂ በመ/ቤቱ ውስጥ ያላት ቆይታ ስልችት እና ድክም እንዳላት አጫወተችኝ፡፡ ይህ ነው እውነታው፡፡ አንድ መ/ቤት እየደከመን፣ እየሰለቸን፣ መሄጃ ያለን ስለማይመስለን፣ እምቅ ችሎታችን ምን እንደሆነ ስላላወቅን…ወዘተ ለውጥ እንፈራለን፡፡

ለውጥ ነውጥ አይደለም፡፡ ለውጥ የማይቀር ሂደት ነው፡፡ እኛ አንድ መ/ቤት ውስጥ በመቆየታችን ያልተለወጥን ቢመስለንም እንኳን በመ/ቤቱ ግን የስትራተጂ እቅድ ይለወጣል፣ አሠራር ይለወጣል፣ ፕሮጀክቶች ይለወጣሉ፣ ሰዎች ይለዋወጣሉ፣ ኃላፊዎች ይለዋወጣሉ፣ ፖለቲካው ይለዋወጣል…ወዘተ፡፡ እንደውም ብዙ ነገር ከመለዋወጡ የተነሳ እኛ እዚያው መ/ቤት ቁጭ ብለን “መ/ቤቱ እኮ እንደድሮ አይደለም፣ ተለውጧል፣ እንዲያውም ተበለሻሽቷል፣ ሠራተኛ ድሮ ቀረ፣ ኃላፊ ድሮ ቀረ፣ ጉርሻ እና እድገት ድሮ ቀረ…ወዘተ” እንላለን፡፡ ለውጥ ለአንድ ድርጅትም ይሁን ግለሰብ በጣም ጥሩ የሆነ ሂደት እንጂ ነውጥ ወይንም ክፉ አጋጣሚ አይደለም፡፡

ብዙዎቻችን ለውጥ የምንፈራው ከምቾት ቀጠናችን ስለሚያስወጣን ነው፡፡ በእርግጥ ለውጥ ሁልጊዜ መልካም ነገር ይዞ አይመጣም፡፡ ሂደቱ ነውጥ ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን ይዞ የሚመጣውን ለማወቅ መሞከሩ ቢያንስ በእኩል እጅ (50%) ሊገጥመን የሚችለውን መልካም አጋጣሚ ፈልጎ ለማግኘት እድላችንን እናሰፋበታለን፡፡ መልካም ለውጥ ለማግኘት ጥረትም ይጠይቃል፡፡ በእራሳችን ላይ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ብዙ ሴቶች እውቀት እና ልምድ የሚገኘው ኮሌጅ ገብቶ መደበኛ ትምህርት በመማር ብቻ ስለሚመስላቸው የተለያዩ ምክንያቶችን ከፊታቸው በመደርደር በእራሳቸው ላይ መሥራትን ችላ ይሉታል፡፡ አንዳንዴም “እኔ መቼ ደላኝ ልጆቼን እያስተማርኩ ነው!” ሲሉ ይደመጣሉ፤ ልጆችን የለውጥ እና የእድገት ተጋፊ ለማድረግ፡፡  በአጠቃላይ ዋነኛ ምክንያታቸው የለውጥ ሽሽት ወይንም ፍራቻ ነው፡፡

ዛሬ ዘመኑ ድሮ አይደለም፡፡ እውቀት በቤት ይመጣል፡፡ ቴክኖሎጂውን ከተጠቀምንበት ሜዳው የእኛ ነው፡፡ ሕይወት ቀያሪ የሆኑ አጫጭር ኮርሶች እና ስልጠናዎች ሞልተዋል፡፡ የሙያ ማህበራት (እንደ ኤውብ ያሉ) በመጠነኛ የአባልነት ክፍያ ያጎለብታሉ፡፡ ያም ሆኖ ግን እድሉን አንጠቀምበትም፡፡ ምክንያቱም ለውጥ እንፈራለን፤ ከሥራ ወጥተን ቀጥታ ወደ ቤታችን መሄድ የለመድን ሰዎች የሙያ ማህበራት  እናስተምራችሁ፣ እናጎልብታችሁ ብለው ያለ ምንም ክፍያ ቢጋብዙንም እንኳን አንሳተፍም፡፡

ከመግቢያዬ የገበያ ወግ ካወጋኋት ሴት ጋር በነበረኝ የደቂቃዎች ቆይታ የተረዳሁት ይኸው ነበር፡፡ በትምህርት ከመጀመርያ ድግሪዋ በላይ አልገፋችም፣ ለረዥም ዓመታት የሠራችበት መ/ቤት ውስጥ ከያዘችው ሙያ በእርከን እንጂ በእድገት ብዙም አልገፋችም፣ ደስተኛ አይደለችም፣ ጡረታዋን ብቻ ተስፋ አድርጋለች፡፡ ይሄ ደግሞ የእሷ ብቻ ሳይሆን የብዙ ሴቶች ሕይወት ነው፡፡

ከማጠቃለሌ በፊት ከሠራሁባቸው በአንዱ መ/ቤቴ በየዓመቱ በሚደረገው የዓመቱ መዝጊያ ስብሰባ ላይ ነባር ሰራተኞች እየተቀባበሉ ኃላፊያችንን ጠጣር ጥያቄ ጠየቁት ይህም “እኛ የመ/ቤቱ አንጋፋ ሠራተኞች ሆነን እያገለገልን ከእኛ ይልቅ አዳዲስ ሠራተኞች በእኛ ደረጃ ሲቀጠሩ በከፍተኛ ደመወዝ ይቀጠራሉ፤ እኛ ተበድለናል!” ብለው አቤቱታቸውን ሲያቀርቡ ዋና ኃላፊው ጠቅለል አድርጎ እንዲህ ሲል አስደንጋጭ መልስ መለሰላቸው፤ “ልክ ብላችኋል እናንተ አንጋፋ ናችሁ፤ ነገር ግን መ/ቤቱ አዲስ ጉልበት፣ አዲስ ተሞክሮ እና አዲስ እውቀት ያስፈልገዋል፤ ስለዚህም ያንን ለማግኘት መ/ቤቱ ዋጋ መክፈል ነበረበት፡፡” በወቅቱ በጣም ተበሳጭተው ነበር፡፡ እውነት ስላላቸው እኔም አብሬ ተበሳጭቼ ነበር፡፡ መ/ቤት ውስጥ የቆዩ ሰዎች የመረጃ ቋት የሆኑ፣ የእኔነት ስሜት ያላቸው ናቸውና፡፡ ግን ደግሞ ኃላፊውም እውነት ነበረው፤ አዲስ ሰዎች አዲስ ልምድ፣ አሠራር፣ ባህል፣ እውቀት ይዘው ይመጣሉ፡፡ ሁሉም በእራሳቸው እውነት ነበራቸው፡፡

በነገራችን ላይ ለውጥ ስንል የግድ መ/ቤት መቀየር አይጠበቅብንም፡፡ እዚያው መ/ቤት ውስጥ እየሠራን እራሳችንን በእውቀት እና በልምድ እያበቃን በውስጥ በሚደረጉ እድገቶች ተጠቃሚ መሆን መቻልም ለውጥ ነው፡፡ ኃላፊነት እየጨመሩ እያደጉ መሄድ ለውጥ ነው፡፡ ስለዚህ ለውጥ ነውጥ ስላይደለ እንፈልገው እላለሁ፡፡ ለዛሬ ጨረስኩ!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *