መንጋና መንጋጋ (Mob & Molar)

መቼስ አማርኛ ቋንቋችን ድንቅ እና ሳይንሳዊ ነው፡፡ አንዳንድ ምንም የማይገናኙ ግን እንዲህ እንደ መንጋ እና መንጋጋ በአንድ ፊደል ብቻ የሚለያዩ ስያሜዎችን ስመራመርባቸው ለካ ሳይንሳዊ ግንኙነት አላቸው፡፡ ዛሬ ደግሞ ምኑን አመጣችብን አላችሁ አይደል!? ሳይንሳዊ ትንታኔውን ከማድረጌ በፊት የ”ሕይወቴ ቅኝት” በተሰኘው መጽሐፌ ላይ በድርበቡ የጠቀስኩትን እና በስራ ዘመኔ ያሳለፍኩትን የመንጋ ገጠመኝ ላውጋችሁ፡፡ ዛሬ ስላለፈ እየገረመኝ እና እያሳቀኝም የማወራው ይሁን እንጂ በወቅቱ ግን ሰው ሆኖ በተለይም ሴት ኃላፊ መሆን ከባድ እና መራራ የሆነብኝ ዘመን ነበር፡፡

ታሪኩ እነሆላችሁ፤ በአንድ እሰራበት በነበረ የአለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት ውስጥ የድርጅቱ የግዢ እና ሌሎች ንብረቶች የሚተዳደሩበት እና የሚንቀሳቀሱበት እንዲሁም የድርጅቱ የአጠቃላይ ደህንነት እንቅስቃሴ የስራ ክፍል ኃላፊ ነበርኩ፡፡ በጣም ከፍተኛ ኃላፊነት መሆኑ እና ለዚያ ብቁ ሆኖ መገኘቱ የሚያኮራ እና የሚያስደስት ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ የስራው ባህርይ ሰቀቀን የሞላው ነበር፡፡ አሁን ላይ ያንን ጊዜ ሳስታውሰው ልክ በልጅነታችን ሌባና ፖሊስ የሚባለውን ጨዋታ የሚመስል የአዋቂዎች አባሮሽ ያለበት ስለነበረ አስፈሪ የሚለው ይገልፀዋል፡፡ ድርጅቱ በቂ ልምድ እና ሙያ ያላቸው የጥበቃ ሰራተኞች እያሉት በጠራራ ፀሐይ የሰራተኞች ሞባይል፣ ገንዘብና ሌሎችም እቃዎች እንዲሁም በሌሊት ደግሞ የቢሮ ጣራ ተከፍቶ ላፕቶፖች፣ ከቆሙ መኪናዎች ደግሞ መለዋወጫዎች፣ እና ሌሎችም ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ንብረቶች ተዘረፉ ሲባል እንደ ኃላፊ በእኔ ቦታ ብትሆኑ ምን ታደርጋላችሁ!? የሌብነቱ ድርጊት ተደጋጋሚ ከመሆኑ የተነሳ እንደማረጋግያ ይነገረኝ የነበረው እኔ በድርጅቱ ከመቀጠሬ በፊትም የነበረ እና የቀጠለ መሆኑን ነበር፡፡ ለእኔ ግን እነሱ እነደተለማመዱት ጉድ ጉድ ተብሎ በዝምታ መታለፍ ስላልነበረበት በእኔ ዘመን ለውጥ ማየት እና ማሳየት ፈለግሁ፡፡ በአንዱ እና አስደንጋጭ በነበረው በአንዲት ሰራተኛ ኃላፊነት የተቀመጠ የድርጅቱ ሰራተኛ መዋጮ ገንዘብ ዝርፊያ መፈፀም ምክንያት ፖሊስ ጣብያ አመለከትኩና ፖሊሶች መጥተው አስፈላጊው ምርመራ እንዲደረግ አስደረግሁ፡፡ ሌቦች አሻራቸውን እንደማይተዉ ባውቅም የሕግ የበላይነትን ለማሳየት እና በድብቅ የሚዘርፉትን ለማስደንገጥ ያደረግኩት ነበር፡፡ አፍታም ሳይቆይ እኔኑ አስደነገጡኝ እንጂ፡፡

በዚያው ሳምንት ሰራተኞች ሰብስቤ አንዱ የሰጠሁት ትእዛዝ “ማናቸውም የጥገና ስራ ለመስራት ወደ ድርጅታችን የሚመጡ አገልግሎት ሰጪዎች ሲወጡ ፍተሸ ይደረግ፣ ለስራ ወይንም ሰራተኞችን ስም ጠርተው የሚመጡ እንግዶች ከመግባታቸው በፊት ሰራተኛው ተጠርቶ/ተጠርታ እንግዳቸውን ይቀበሉ፣ የሚገቡበትንም ቢሮ ተከታተሉና አስተናግዱ…ወዘተ” ሚል ነበር፡፡ ይሄ ትእዛዝ ለካ ያልተመቻቸው ሰራተኞች ነበሩ እና ተመካክረው መንጋ ፈጠሩ፡፡ አንዱን አገልግሎት ሰጪ በስብሰባ ላይ ስምህን ጠርታ ሌባ ብላሀለች በማለት ክስ እንዲመሰርትብኝ ያደርጉና ከ30 ተሰብሳቢዎች ሁለቱ ምስክር ሆነው ይቀርባሉ፡፡ በሕይወቴ ሰው በዚህ ልክ ይክዳል፣ ይዋሻል፣ ብዬ አስቤ ስለማላውቅ በድንጋጤ ታመምኩ፡፡ የገረመኝ ግን እራሴን አልሳትኩም፤ ጠንካራ ሴት መሆኔን ያወቅኩት የዚያን ቀን ነበር፡፡ ፖሊስ ቢሮዬ መጥቶ ጣብያ ስደርስ የሰደብኩት ሰው እንዳለ ስጠየቅ “በሕይወት ዘመኔ ሰው ተሳድቤ አላውቅም!” ብዬ የመለስኩት በልበሙሉነት ነበረና ፖሊሱ የምመጻደቅ መስሎት “ሳትሳደቢማ ተሳድበሻል ተብለሽ አትከሰሺም፣ ያን ያህል እንኳን አትመጻደቂ!?” ያለኝን ሳስታውሰው ከመንጋዎቼ ክስ በላይ የእሱ ሙያ የጎደለlው አስተያየት እስካሁን ያበሳጨኛል፡፡ እኔ ግን ተረጋግቼ ወድያው የድርጅቱን ኃላፊ እና ባለቤቴን ደውዬ ጠራሁ፡፡ ብቻ ላሳጥረውና ድርጊቱ የተጠነሰሰው በመንጋ ነበር፡፡ የድርጅቱን እና የሰራተኞችን ንብረት በቡድን ተደራጅተው ሲመዘብሩ የነበሩ መንጋዎች እኔን ከዚያ ኃላፊነት ለማስነሳት ብቻ ሳይሆን ከድርጅቱ ለማስወጣት ያደረጉት ሴራ ነበር፡፡ በፈጠሩት የውሸት ትርክት ለማሳሰር ባይችሉም እና የባሰ ጥንካሬዬን ቢያውቁም የእኔን በድረርጅቱ የመቆየት እድሜ ግን አሳጥረውታል፡፡ በቆይታዬ ለድርጅቱ ውጤት ካስመዘገቡ ኃላፊዎች አንዷ በመሆኔ ድርጅቱ እኔን ቢያጣም እንደድርጅት ግን ቀጥሏል፡፡ እኔ ግን እስከዛሬ መንጋ ሲባል በአእምሮዬ ጠባሳ ሆኖ ይኖራል፡፡ ስንቶች የመንጋ ሰለባ ሆነው ይሆን!? ድርጅታቸውን አይደለም ሀገራቸውንም ጥለው ተሰደዋል፡፡ ሕይወታቸውንም ያጡ ይኖራሉና መንጋ ክፉ ነው፡፡

መንጋ እና መንጋጋን ታድያ ምን አገናኘው ወደሚለው ልመልሳችሁ፡፡ መንጋ ማለት በድብቅ የሚንቀሳቀስ ቡድን ነው፡፡ የሆኑ ሰዎች ለአንድ አላማ ሕብረት ፈጥረው ድብቅ አላማቸውን ለማሳካት የሚመሰርቱት ነው፡፡ ተቧድነው ሆ ብለው እስኪነሱ በድብቅ ነው የሚያሴሩት፣ አላማቸው ግቡን እስኪመታ የሚበግራቸው የለም፤ ተማምለው የገቡበት እስኪመስል ሞቅ እያላቸው ነው የሚሄዱት፡፡ ምናልባትም በተናጠል ቢጠየቁ ከውስጣቸው የመንጋውን የመጨረሻ ግብ ያልተረዱ ወይም ያላመኑበት ሁሉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን መንጋ ቁጥሩ ብዙ ስለሆነ ከብዙሀኑ መነጠል ስለሚያስፈራቸው እና መገለላቸው የሚያስከትልባቸውን ጫና ፈርተውም የገቡበት ሊሆን ይችላል፡፡ መንጋ ኃይል አለው፡፡ በተለይ የመንጋው ጠንሳሾች ከኋላ ሆነው ሲጠነስስ አላማ ይዘው ስለሆነ የማሳመን እና የመግፋት አቅማቸው እስከሞት ድረስ ነው፡፡ አጥፍቶ ጠፊ አይነት ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ መንጋ ሁሉ  መጥፎ ላይሆን ይችላል፤ ለበጎ አላማም በመንጋ ማሰብና መፈፀም ለውጥ የሚያመጣበት ጊዜም እንዳለ ልብ ይሏል፡፡ ይህንን ምሳሌ ከመስጠቴ በፊት ስለመንጋጋ ተመሳሳይነት ትንሽ ልናገር፡፡

መንጋጋ የጥርሳችን የኋላ ክፍል ሲሆን ልክ እንደ መንጋ ስራውን የሚሰራው በድብቅ ወይንም ከኋላ ነው፡፡ የፊት ጥርስ ምግብ የሚነክሰው እየታየ ነው፣ የውሻ ክራንቻ የምንለውም የሚግጠው እየታየ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት የጥርስ አይነቶች የነከሱትን እና የጋጡትን አሳልፈው የሚሰጡት በድብቅ በሕብረት ለተሰደሩት ለመንጋጋ ጥርሶች ነው፡፡ የመንጋጋ ጥርሶች በቡድን ወይንም ሕብረት ይሆኑና የተላከላቸውን ምግብ አድቅቀው/አልመው ለጉሮሮ ያበቁታል፡፡ የመንጋጋ ጥርሶች በሕብረት በመስራታቸው ለሌሎቹ ጥርሶች ያልተቻለውን የመቻል አቅማቸው የትዬለሌ ነው፡፡ ሌላው መንጋጋ አቀመማመጡም እንደ ሴረኛው መንጋ በድብቅ ስለሆነ እንደፊት እና ጎን ጥርሶች ሲቆሽሽ እና ሲበላሽ ቶሎ አይታይም፤ ስለዚህም ችግሩ ስር ሰዶ ወደ ሕመም እና መነቀል ድረስ ይደርሳል፤ ልክ መንጋ ሲደረስበት እንደሚነቀለው ማለት ነው፡፡ አቤት መመሳሰል! አጃይብ እኮ ነው!

መቼስ የመንጋ እና የመንጋጋን ቃላታዊ እና ተግባራዊ ግንኙነት በዚህ መልኩ አስበነው አናውቅም ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔም ከአእምሮዬ የማይወጣው የመንጋ ጥላቻ አፈላሰፈኝ እንጂ መንጋጋ እግዚአብሔር የሰጠን እጅግ ጠቃሚ የሰውነታችን አካል ነው፡፡ መንጋጋ ባይኖር ኖሮ ጉንጫችን እንኳን እራሱ ወደ ውስጥ ሰርጉዶ መልከ ጥፉ እንሆን ነበር፡፡ መንጋጋችንን ይጠብቅልን! ለነገሩ ከላይ መንጋም ቢሆን በጎ ጎን አያጣውም ብያችሁ ነበር፡፡ አንድ ትዝታ ልንገራችሁ ከማጠቃለሌ በፊት፡፡ ዩኒቨርስቲ ስንማር ጥንስሱ ከየት እደሆነ የማናውቀው የመንጋ እንቅስቃሴ (mob movement) ይነሳል፡፡ በእኛ ጊዜ (በ1980ዎቹ) የሞቡ መነሻ በተለይ በምግብ አቅርቦቱ ላይ ነበር እንጀራው ኮመጠጠ፣ ወጡ የጤፍ ነው፤ ዳቦ ደረቀ ወዘተ፡፡ ከዚያ ያንን መንጋ (ሞብ) ተማሪው ሁሉ ሆ ብሎ ሲቀላቀል ድንገት የፖለቲካ መዝሙሮች  መዘመር ይጀምራሉ፡፡ ለካ መጀመርያም የሞቡ ጠንሳሾች መንግስትን ለመቃወም የጠነሰሱት ነበር፡፡ ያው ተማሪውን አስፈራርተው ደብድበውም ጭምር ቢበትኑትም እንጀራ እና ወጡ ግን የዚያን ሰሞን ይሻሻላል፡፡ የፖለቲካ ጥያቄው ምን እንደሚደርስ አላውቅም፤ የሚያውቁ እና የሚያስታውሱ ይኖራሉ፡፡ ታድያ መንጋ በዚህኛው ገጽታው ለምግቡ መሻሻል ጠቀመም አይደል! ሳጠቃልለው እንደ መንጋ እና መንጋጋ ተደብቆ በሕብረት ማሰብ የራስን ማንነት ከማሳጣቱም በላይ እድሜ ልክ የሚቆጨንን ውሳኔ እንድናስተላልፍ ስለሚያደርገን ብንጠነቀቅ እና ነገር ግን ከመንጋ እና ከመንጋጋ ሕብረትን በበጎ ጎኑ ወስደን እኛ ደግሞ ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትን እና አገልጋይነትን አክለንበት ለራሳችንም፣ ለወገናችንም ለሀገራችንም የሚጠቅም ስራ እንስራበት እላለሁ፤ ለዛሬ ጨርሻለሁ!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top