ጆሮም እንደ ዓይን መዝጊያ ቢኖረው?!

የሰውነት አካላችን በቅንጅት የሚሰራው ስራ እኛን እኛ ያደርገዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለነገሮች ተጋላጭ የሚያደርገን ፈልገን ሳይሆን ሳንፈልግ ወይንም ከአቅም በላይ በሆነ ክስተት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ቦታ ሄደን ለተከሰተው ክስተት እግራችን ፈቅዶ ባይሄድ ላናይ ላንሰማ እንችል ነበር፡፡ በሄድንበት ቦታ ዓይናችን “ይሄን ማየት አልፈልግም” ብሎ ከጨፈነ ያንን ክስተት ባለማየት እንተርፋለን ማለት ነው፡፡ እጃችንም ከመንካት ከታቀበ ታቀበ ነው፡፡ ብቻ በአብዛኛው የሰውነታችን ክፍል እምቢ የማለት መብት እስኪኖረው ድረስ ነው የተሰደረው፡፡ አፍንጫ እንኳን እድሜ ለኮቪድ አይባልም እንጂ ልብስ ተሰፍቶለታል፡፡ እኔ የሚያሳዝነኝ ጆሯችን ነው፡፡ አሰራሩ እራሱ እንደ ዲሽ ግራ እና ቀኝ በስፋት ተለጥፎ እና በስፋት ተከፍቶ ነው፡፡ ወደደም ጠላ የመስማት ወይም የማዳመጥ ግዴታ አለበት፡፡ የምር ጆሮ በጣም ተበድሏል! ችግሩ እራሱን ችሎ አይበደልም፡፡ ተሸካሚው ፍጡሮች (እኛ) የግዴታ ጆሮ የሚያመጣልንን ጥሩም ይሁን አርቲ ቡርቲ (መጥፎ) የማዳመጥ እና የማቀበል ውለታ ልበለው ግዴታ ተጥሎብናል፤ በጆሮ የተነሳ፡፡ እንደሌሎቹ የሰውነት ክፍሎቻችን ልንዘጋው አንችልም፡፡ ለነገሩማ ጥቅሙ ስለሚያመዝን ተመስገን እንኳንም ኖረልን! እንዲያው ለመምረጥ ይችል ዘንድ አድልዎ ተደርጎበታል፤ ፊት ለፊት ይታይ ዘንድ እንዳይችል በጎን ተለጥፎ መገለልም ጭምር ስለደረሰበት አሳዝኖኝ እንጂ፡፡

ዛሬ ስለጆሮ ያወራሁላችሁ በምክንያት ነው፡፡ ከጆሮ ጋር ተያያዥ ገጠመኞቼ የእናንተም ጭምር ስለሆኑ ላጋራችሁ እና አብረን የአቋም መግለጫ እናወጣለን፡፡

ገጠመኝ አንድ፡- አንድ ቢሮ ለስራ ሄድኩ እና በመረጃ ክፍሎች አማካይነት ጉዳዬ ወዳለበት ቢሮ ተመራሁ፡፡ ወደቢሮው ስገባ ሦስቱ ሰራተኞች ቢሮውስጥ ነበሩ፤ ሁለት ሴቶች እና አንድ ወንድ፡፡ የእኔ ጉዳይ የተመራላት ፊትለፊት የተቀመጠችው ወጣት ሴት በሞባይሏ ላይ ክፉኛ ተጠምዳለች፡፡ ቀና ብላ አይታኝ ስታበቃ ምንም ዓይነት የይቅርታ ፊት ሳታሳየኝ የስልክ ጭውውቷን ቀጠለች፡፡ እኔም ደክሞኝ ስለነበረ ቁጭ በይ ብላ ባልጋበዘችኝ የእንግዳ ወንበር ላይ ተቀመጥኩ፡፡ ለ12 ደቂቃዎች ታግሼ ቁጭ በማለቴ ተስተናገድኩ፡፡ ይህም ተመስገን ነው! ቅጥል ያደረገኝ ግን 12 ደቂቃ ያለምክንያት መቀመጤ ብቻ አልነበረም፡፡ ሻይ ልትጠጣ ወጥታ ወይንም አለቃ ቢሮ ገብታ ቢሆንስ መጠበቄ ይቀራል? አይቀርም፡፡ እኔን ያበሳጨኝ ያንን ሁሉ ደቂቃዎች ስታወራ የነበረውን ልቅም አድርጌ ማዳመጤ ነው፤ እኔ ብቻ ሳልሆን የስራ ባልደረቦቿም ጭምር፡፡ ከወድያ በኩል ያለው ሰው ወንድ መሆኑን በየመሀሉ “ሂድዛ! አልቀረብህም፣ ሞዛዛ፣ እና፣ በል ባክህ…ኪኪኪ” ከሚሉት ጣፋጭ ቃላቶቿ (ያው ቢጣፍጠው ነው ብዬ ነው!) ተረድቻለሁ፡፡ በዚያ ላይ ያስቃታል፤ ጮክ ብላ ትስቃለች፡፡

እኔ የምለው በእኛ ዘመንኮ ከተቃራኒ ጾታ ጋር እንደዚህ በአደባባይ አይወራም! መፎረሽ ሲመጣ ማን ይሳቀቃል! በዚያ ላይ ባህል የሚባል ድባብ ያለው ነገር ነበር (ዋሸሁ እንዴ እናንተ ከ40 በላይ የሆናችሁ የእኛ ዘመን ጓደኞቼ?)፡፡ ደግሞ ሌላ የስራ ባልደረባ የሆነ ወንድ ቢሯችን ካለ ጭራሽ ዚፕ ነው በእኛ ጊዜ!

እናላችሁ ቁጭ ብዬ ሳስብ የነበረው በቀን ስንት ሰዓቶች በእንደዚህ ያሉ ስልክ ምልልሶችእንደሚባክኑ፣ ደንበኛ መቼ በቅጡ እንደሚከበር፣ ሚስጥር የአደባይ መሆኑ መቼ እንደሚቀር፣ በአጠቃላይ ስነስርዓት ናፈቀኝ፡፡ ምክንያቱም ይሄ የመጀመርያ ጊዜዬ አይደለማ! በየቢሮው፣ በየንግድ ቦታው ይህ የሚያጋጥመኝ ጉዳይ ነው፤ በሴት ገጠመኜን አጋራኋችሁ እንጂ በወንዶችም ሰራተኞች አለ፡፡ እናንተን አስቀምጠው የኳስ ግጥምያ፣ የጥሬ ስጋ፣ የቤት ኪራይ እና መሰል ከኑሮና መዝናናት የሚያጣቅሱ ወጎችን ያስከሰክሷችኋል፡፡

ገጠመኝ ሁለት፡- ሰፈሬ አትክልት እና ፍራፍሬ ነጋዴዎች አሉ፡፡ ጭነታቸው የሚገባው ከእኩለ ሌሊት በኋላ ነው፡፡ ያ ሰዓት ደግሞ ለእኛ ለቀን ሰራተኞች የማረፍያ ወይም ድብን ያለ የእንቅልፍ ሰዓታችን ነው፡፡ ታድያ ነጋዴዎቹ ጎረቤቶቻችን ይሄ የእነሱ ጣጣ አይደለም፡፡ የጫነውን መኪና የት ደረስክ ለማለት ስልኩን ትተው እራሱ በድምጽ ቢጠይቁት ዘልቆ ሊሰማው በሚችል ጩኸት ያወራሉ፡፡ ከዚያ ጭነቱን እያራገፉ ሌሎች ነጋዴዎች ጋር ይደውላሉ፤ እየጮሑ ያወራሉ፡፡ እኛም በደንብ ነቅተን እናዳምጣለን፤ ወደን ሳይሆን ተገደን፡፡ ይባስ ብለው ሙዚቃም ይከፍታሉ፤ የሰራ አእምሯቸውን ዘና ለማድረግ በውድቅት ሌሊት፤ የእኛ ጆሮ እሱንም እኛ ሳንፈልግ ሰምቶ ያቀብለናል፡፡

በአጠቃላይ የስልክ አጠቃቀም ስርዓት አንዱ የፕሮፌሽናሊዝም (Professionalism) ሚዛን መጠበቅያ ነው፡፡ በቢሮ ወይንም በማንኛውም በተሰማራንበት የስራ መስክ ሞባይል ሆነ ማንኛውም ስልክ በምናወራበት ጊዜ ስነስርዓት ከሌለን ኪሳራ ላይ መሆናችንን እንወቅ! ስለዚህም የሚከተሉትን የአቋም መግለጫዎች እንለማመዳቸው፡-

1ኛ፡- ሰላምታም ሆነ ጭውውት አሳጥሮ ቁምነገር በማውራት የማውሪያ ሰዓት መቀነስ፤ ደዋይ ከሆናችሁ ስራ በማይበዛባችሁ ሰዓት ብቻ ደውሉ፤ የሌሊት ሰራተኞችም ለቀን ሰራተኞች እዘኑ፡፡

2ኛ. ቢሮ ወይም የስራ ቦታችሁ ሌሎች ሰዎች ካሉ እና ስልኩን መመለስ ካለባችሁ ወደ ኮሪደር ወይንም ከስራ ባልደረቦቻችሁ ራቅ ብላችሁ አውሩ፡፡ ከወንበራችሁ መነሳት የማይቻል ከሆነ ይቅርታ ስልኩን ከመመለሳችሁ በፊት በማይዘጋው ጆሯቸው መስማታቸው ስለማይቀር ይቅርታ ጠይቋቸው!

3ኛ. ድምጻችሁ እንደ እኔ ትልቅ ከሆነ ቀንሶ ማውራት ተለማመዱ፡፡ አለበለዝያ ሌሎች ሰዎች አእምሯቸው እንዲሰረቅ ታደርጋላችሁ! ማውራትም ሆነ ማንኛውም ስሜት ለመግለጽ (ድንገታዊ ካልሆነ በስተቀር) ድምጽን ዝቅ ማድረግ አግባብ ነው፡፡

4ኛ. ቢቻል የሞባይላችሁን የጥሪ ድምጽ ቫይብሬት ወይም ሳይለንት አድርጉት፤ ካልሆነ ትንሽ ድምጽ አድርጉት

5ኛ. የግል የሆኑ ነገሮችን ወይም በጣም ስሜታዊ የሆኑ ነገሮችን የስራ ጓደኞቻችሁ ወይንም ባለጉዳዮች (customers) ፊት አታውሩ፡፡ ገመና የሚባል ነገር አለኮ! እኛኮ ስለቦይፍሬንድ ገርልፍሬንድ፣ ስለቤተሰብ፣ ስላየነው ኳስ፣ ስለሰራተኛችን ስለልጆቻችን ምግብ…ወዘተ ቢሮ ውስጥ በስልክ ማውራት ምንም የማያሳፍረን ጉዶች ነን፡፡ በእርግጥ በሻይ ሰዓት ወይንም ቢዚ ባልሆነ ሰዓት ማህበራዊ ነገሮቻችንን መጋራት ከለመድን ክፋት አይደለም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰው እንደኛ ነወይ? ማውራት እና ማዳመጥ ይፈልጋል ወይ? ስለዚህ ተመራርጠን ለምን በራሳችን ጊዜ አናወራም? በተለይ በስልክ ሲሆን ደግሞ ሌሎችን የማያሳትፍ ስለሆነ በጣም የሚረብሽ (destructive) ነው እና እንታቀብ፡፡

5ኛ. የስራ ስልክ ከሆነ ደግሞ ጥሩ መግቢያ እና መውጫ ያለው ቃላት ተጠቀሙ፡፡ ሰላምታ ለመግቢያ፣ አመሰግናለሁ ለመውጫ እንዴት አሪፍ መሰላችሁ! አንዳንዶች አንስታችሁ እኮ “እ” ትላላችሁ! ዋሸሁ እንዴ!

6ኛ. ማስቲካ ወይንም የሚላመጥ ነገር እያኘካችሁ ስልክ አታውሩ! ጓደኛ ወይንም ቤተሰብ ከሆነ እንደፈለጋችሁ ሪላክስ ማድረግ ትችሉ ይሆናል፡፡ የስራ ስልክ ግን በባዶ አፍ (በቃላት ብቻ)!

 እንግዲህ ጆሮ መዝጊያ የለውም እና እኛም ምርጫ የለንም እና እርስ በእርሳችን እየተዛዘንን፡፡ ልብ እንበል፤ ፕሮፌሽናሊዝም የግድ ቢሮ ለሚውሉ ሰዎች ብቻ አይደለም፡፡ በማንኛውም መስክ ለተሰማራን ሰዎች አስፈላጊ ነው፡፡  ለዛሬ ጨርሻለሁ!  

የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top