ዶሮ ፊት ፈንግል ካልተወራ ልጆች ፊትስ?!

Image source: https://images.mid-day.com/images/images/2023/oct/wmhdpgfive.jpg
መቼስ አባቶቻችን ተረት ሲያውቁ እኮ! ቆይ ግን ይቅርታ አባቶቻችን ብቻ ነበሩ እንዴ የሚተርቱት? ጀመረኝ ደግሞ ዋና ሀሳቤን ገና ሳልዳስስ የተረት እና ምሳሌ ታሪካዊ አመጣጥ የአባቶች ወይንስ የእናቶች ወደሚለው ዥው ብዬ ገባሁ፡፡ ብቻ የድሮ ተረቶች አስተማሪዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ በርእሱ ያነሳሁት “ዶሮ ፊት ፈንግል አይወራም” የሚለው መቼስ ዶሮዎች ጆሮ ስላላቸው አይደለም፤ ሰውኛ አባባል ሆኖ እንጂ እኛን ለማስተማር፡፡ የዚህ አባባል አንዱ ግጣሙ ልጅ ፊት የማይወሩ ነገሮችን እንዳናወራ የሚያስታውስ ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው ታማሚ ፊትም ስለሞት አይወራም፡፡
ወደዚህ ርእስ ያመጣኝ አንድ አብሮ አደጌን ከብዙ ዓመታት በኋላ በድንገት አግኝቼው የተገናኘንበት የእኔም የእሱም የተለያየ ጉዳያችን ወረፋ ስለሚያስጠብቀን በሰጠን በቂ ጊዜ ቡና እየጠጣን ያወጋነው ወግ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አብሮ አደግ ስላችሁ እንግዲህ በእኛ ዘመን ቀበሌ የሚባል ነበር፤ አሁን ሰብሰብ ተደርጎ ወደ ወረዳ ያደገው አሰፋፈር ወይንም አሰያየም፡፡ እና የቀበሌአችን ልጅ ስለሆነ እንጂ አብረን ተጫውተን አላደግንም፡፡ እሱ ሜዳ ነክ ጫወታዎች ላይ ብዙም ተሳትፎ አልነበረውም፡፡ ለምን ካላችሁ በኋላ እነግራችኋለሁ፡፡ መቼስ ልጅነቴን ሳስታውስ ከሚያስገርመኝ ነገር አንዱ የአካባቢ ዳሰሳ ብቃታችን ነው፡፡ ከአንድ ሺህ በላይ አባወራ የሰፈረበትን መንደር ወላጆችንም ልጆችንም ጥንቅቅ አድርገን እናውቃቸው ነበር፡፡ ይሄ መቼስ የአሁን ልጆች ከማይኖራቸው ተሰጥኦዎች አንዱ ይመስለኛል፤ በአብዛኛው ተቆልፎባቸው ስለሚውሉ፡፡ በልዩነት የሚታወቁት ደግሞ ከአካባቢው በኑሮ ደረጃ ከፍ ያሉት፣ በባህርይ ለየት ያሉት (ስካርን ያስታውሷል) እና ሌላም ሌላም መለያ ያላቸው ናቸው፡፡ ታድያ ይሄ አብሮ አደጌ ያልኳችሁ ልጅ ቤተሰቦቹ በኑሮ ደረጃ ከአካባቢው ነዋሪ ትንሽ ከፍ ያሉና አባትየው ደግሞ መሽቀርቀር የሚያዘወትሩ ነበሩ፡፡ ሌላ ሌላም ከሌሎች አባቶች የሚለዩበት ከሌሎች ልጆቻቸው በተለየ ይሄኛውን ልጃቸውን ከስራ ውጪ በሚሄዱበት ሁሉ እንደ ሳምሶናይት ቦርሳቸው (ያኔ እሳቸው ይሄ ቦርሳ ነበራቸው) ከእጃቸው አይለዩትም ነበር፡፡ ከላይ ሜዳ ነክ ጨዋታዎች ያልተሳተፈበትን ምክንያት አሁን አገኛችሁት አይደል!
እናላችሁ ይሄ ሰውዬ (አብሮ አደጌን ይሄ ልጅ ማለት ግፍ ነው መቼስ!) አሁን በንግድ ስራ ተሰማርቶ የሚኖር በኢኮኖሚ ዘርፍ ጥሩ ደረጃ ላይ ያለ ነው፡፡ ግን በሕይወቱ ሌላኛው ገጽ አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ነው ያለው፡፡ እንግዲህ አባትየው የትም ሲሄዱ ከእጃቸው አይለዩትም ነበር ብያችኋለሁ (ዛሬ ይለዩትና! በሕይወት ስለሌሉ)፡፡ ያን ጊዜ ከሚያዘወትሯቸው ስታዲየም፣ እድር ቤት፣ ካርታ ቤት (በጨዋ መልክ ብቻ ሳይሆን ሲቆምሩም ጭምር)፣ ግሮሰሪ (ለሱ ለስላሳ ቢገዛለትም ድባቡን ያውቀዋል) እና ከሁሉ የከፋው ግን ሰውየው በሚስታቸው ላይ ይሄዱ ስለነበር ሚስቶቻቸው (አበስኩ ገበርኩ አይባልም) ሴቶቻቸው ጋር (ውሽሞች ላለማለት ብዬ እኮ ነው!) ጋር ሲሄዱም ይዘውት ይሄዱ ነበር፡፡ ይሄ ጉብል ታድያ ያንን ሁሉ እያየ የአባቱ ምስጢረኛ ሆኖ አደገ፤ በተለይ ከፍ እያለ ድርጊቱ ነውር እንደሆነ እስኪገባው ድረስ ያየውን አይቷል፡፡ እንዲያውም አንድ ኑሮዋን በውጭ ያደረገች የዚያ ቀበሌ ሳይሆን ከፍ ሲል ደግሞ ከፍተኛ የሚባል ነበር እና የከፍተኛችን የዘመኑ ሽቅርቅር ወጣት እንደማስታውሳት ጠየቀኝና አዎንታዬን ስገልጽለት ጀርመን ሀገር የላኳት አባቱ መሆናቸውን ሁሉ አጫወተኝ፡፡ የላኳት ደግሞ እሷንም ያውቋት (በጨዋ አገላለጽ) ነበረና “በወጣትነቴ ተጫውተሀልና ውጭ ሀገር የማትልከኝ ከሆነ ምስጢሩን አውጥቼ ትዳርህን እበትነዋለሁ!” ብላ አስፈራርታቸው ነው፤ ያልተበተነ የምትበትን መስሏት ምጽም፡፡ ለነገሩ እናቶቻችን እኮ የዋሆች ነበሩ፤ አንድም ብዙ አይመራመሩም እንደዚህ ያለ ሸፍጥ እንደሚሰራባቸው ሲያውቁም ከጥቂቶች በስተቀር ብዙዎቹ አንጀታቸውን ቆልፈው ቻል ያደርጉት ነበር፡፡ ማን ያውቃል ምስጢር እያለ የሚነግረኝን እናትየው በዘመኑ አውቀውት በቁጭት እና በፀፀት ያሳለፉት ይሆናል፡፡
ይሄን ሁሉ ወግ ያወጋኝ መነሻው አሁን ያለንበትን የኑሮ እና የቤተሰብ ሁኔታ ስንጠያየቅ ነው፡፡ ሰውየው ቤተሰብ አልመሰረተም፡፡ ያልመሰረተበት ምክንያት ደግሞ ውሀ አጣጭ ስለአጣ ሳይሆን ስላልፈለገ ነው፡፡ ያልፈለገበት ምክንያት በሁለት ምክንያት እንዲህ ያስቀምጠዋል፡፡ አንደኛው በልጅነቱ አባቱ በእናቱ ላይ ሲያደርጉት የነበረው ድፍረት እና ሸፍጥ የተሞላበት ውስልትና እሱም አባቱ በሚያደርጉለት መደለያ ለእናቱ ሳይተነፍስ መቅረቱ አባሪ በደለኛነት ስሜት እንዲሰማው ስላደረገው ቀሪ ዘመኑን እናቱን እየጦረ አብሯቸው ለመኖር መወሰኑ ነው፡፡ እኔ ግን “እናትህ እኮ ያለፈውን ታሪክ ባለማወቃቸው ምናልባትም ለበጎ ይሆናል፡፡ ያን ጊዜ ቢያውቁ ኖሮ ትዳሩ ሲፈርስ አባትህ ሴቶቻቸው ጋር ይሄዳሉ፤ እናትህ ግን ገቢ ስለማይኖራቸው እናንተን ይዘው ይቸገሩ ነበር” አልኩት “በእኔ የደረሰ ቢሆንስ?” የሚለውን አካታችነት ያላማከለ ምክሬን ገፋ አድርጌ፡፡ ሁለተኛው ምክንያቱ ደግሞ ከአባቱ ጋር ሲወሰልቱ ከነበሩት ውስጥ ባለትዳር የነበሩ ሴቶችም ስለነበሩበት ለትዳር ያለው አመለካከት ዘጭ ያለ ሆነ፡፡ ለዚህም አልኩት “ሁሉም ባለትዳሮች ወስላቶች አይደሉም፤ በዚያ ላይ እናትህም አብረሀቸው ከምታረጅ አግብተህ ቤተሰብ ብትመሰርትላቸው ደስታቸው ነው” አልኩት “ምክር እና ቡጢ ለሰጪው ይቀላል” እንዲሉ፡፡ ግን ደግሞም ልክ እኮ ነኝ አይደል? መሰለኝ!
መቼስ ይሄን ሁሉ ያስወራኝ በርእሱ ላይ እንደጠቀስኩት ዶሮ ፊት ፈንግል አይወራም ብሎ ሲተርት የኖረ ማህበረሰብ ልጆች ፊትስ የሚወራ እና የሚደረገውን መለየት ያቅተዋልን!? የሚል ጥያቄ መጥቶብኝ ነው፡፡ ብዙ ወላጆች ጠንቃቆች እንደሆኑ አምናለሁ፤ ግን ሁላችንም አይደለንም፡፡ አስቡት ይሄ ሰው በልጅነቱ የአባቱ ልዩ ልጅ ነበር፡፡ በእርግጥ ልጆችን ከልጆች ማበላለጡም ሌላ ዋጋ የሚያስከፍል ነገር ነው፡፡ የዚህኛው ግን ተወዳጅነቱ ለከፋ ነገር አጋለጠው፡፡ ልጅ የማይውልበት እንዲውል ከመደረጉም በላይ የከፋው የአባቱን የብልግና ጥግ (ይቅር በሉኝ!) እያየ እንዲያድግ መደረጉ ነው፡፡ አሁን በዚህ ሰው አእምሮ ውስጥ ያለውን የስሜት ቀውስ (trauma) ማነው የሚነቅልለት? በነገራችን ላይ “እንዲህ ያለ በልጅነት የተፈጠረ የስሜት ቀውስ ይታከማል ለምን ባለሙያዎች አታማክርም” ብዬ ስጠቁመው “ደግሞ ይህንን ችግር ነው ብዬ ጊዜዬን እና ገንዘቤን ላባክን ነው!?” ነበር ያለኝ፡፡ እንግዲህ “በሽታውን የደበቀ መድሀኒት አያገኝም” እንዲሉ አበው/እመው ከማዘን በስተቀር ምንም አቅምም ሆነ አቋም የለኝም፡፡ ማለት የምችለው ወላጆች ወይንም አሳዳጊዎች በተቻለን መጠን ልጆቻችን ፊት የሚደረግ እና የማይደረግ፣ የሚወራ እና የማይወራ ለይተን እንወቅ፡፡ ከማጠቃለሌ በፊት ግን አንድ ትዝብት አለኝ፡፡ እኛ ሀገር በአብዛኛው ወላጅነት “አቦ ሰጡኝ” ነው የሚመስለኝ፡፡ አቦ ሰጡኝ ማለት ምን እንደሆነ ለማታውቁ እንደሎተሪ እድል የሆነ ነገር ማለት ነው፡፡ ከምር የታዘብኩት ነው፡፡ ከቀድሞ ወላጆች እኛ ሰልጥነናል የምንለው እንኳን ወላጅነትን በእውቀት አንደግፈውም፤ በልምድ እንጂ፡፡ እንደ እኔ ወላጅነት ኮሌጅ ወይንም የስልጠና ማእከል የሚያስፈልገው ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ወላጅ ከመሆናችን በፊት መሰረታዊ ስልጠናዎችን መውሰድ ነበረብን፡፡ ቆይ ይቺ ሀሳብ ግን ቢዝነስ ትሁን እንዴ! ትውልድ የማዳን ቢዝነስ! እናስብበት እስቲ!? በሉ ለዛሬ ጨርሻለሁ!
የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም
Share to your circles!