እኩልነት ለምኔ!

የማርች ወር መቼስ ሴቶች በአንድ ጣራ ስር በብዛት የምንታደምበት ወር ነው፡፡ ደስ ያሰኛል! ቢያንስ በአመት እንዲህ አምሮብን፣ ተሳክቶልን፤ በጀት ተበጅቶልን (ውሳኔ ሰጪው በአብዛኛው ያኛው ጾታ ነው ብዬ ነው) የልብ የልባችንን ማውራት ቀላል ነገር እንዳይመስላችሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ አቅልላችሁ ለተመለከታችሁት ወንድሞች እና እህቶች ይቅር በሉኝና ተሳስታችኋል የምል ነኝ (ስለይቅርታችሁ አመሰግናለሁ!)፡፡ አንዳንዶችማ “በየአመቱ ተመሳሳይ ነገር ለማውራት ቢሰበሰቡት ምን ዋጋ አለው፣ ከስብሰባ ያለፈ ተግባር አናይም፣ ለይስሙላ ነው፣ ወዘተ” በሚል መንፈስ ድከም ብሏቸው ሌላውንም ሰው ያዳክማሉ፡፡ ለነገሩ የሚዳከምላቸው ተላሎች ካገኙ ነው፡፡ እንደ እኔ አንድ ነገር በተደጋጋሚ (በአመት አንዴም ቢሆን) ሲዘከር ቀላል አይደለም፡፡ ውሳኔ ሰጪዎችን በየሚዲያው ወረፍ ስናደርጋቸው ማለቴ ስናስታውሳቸው እኮ መነቃቃታቸው አይቀርም፡፡ አለን ማለትም ቀላል አይደለምኮ! ፎ!

አንዳንድ አግራሞቶቼን እስቲ ላጋራችሁ፡፡ አሉላችሁ ንቅት ያሉ የሚመስሉ ግን ትንሽ የሚጎላቸው ሴቶች (በእኔ አስተያየት ነው ትንሽ ማለቴ) “ሴት ከወንድ እኩል ልትሆን አትችልም፣ እኔ ፌሚኒስት አይደለሁም…ወዘተ” እያሉ በማህበራዊ ሚዲያዎች የአቋም መግለጫ የሚመስል ነገር የሚጽፉ እና የሚያወሩ፡፡ ቆይ እኩልነት የሚለው ነገር በተክለ ቁመና፣ በአስተሳሰብ፣ በአፈጣጠር ነው እንዴ? ያንንማ እኛም እናውቀው የለ እንዴ! ፈጣሪም ሲፈጥረን እኩል እንዳንሆን ያስቀመጠልን መስፈርያ እኮ በእኛም ዘንድ ግልጽ ነው፡፡ ለምሳሌ እኛ ሴቶች የዘር ፍሬ አልተሰጠንም በቃ ልክ እነሱ ወንዶቹ ደግሞ ማህፀን እንዳልተሰጣቸው ሁሉ፡፡ ግን እኩል እንድናዋጣ አስቦ አንዳችን ከሌላችን ተጣምረን ምድሪቷን ሞላናት፤ እኩል አስፈላጊነታችንን ሲያረጋግጥ፡፡ በተፈጥሮ ቅርጽ እኩል የማንሆንባቸውን መስፈርያዎች ደግሞ አስቀምጦልናል፤ ነገር ግን አንዳችን ለሌላችን አስፈላጊ ነን አራት ነጥብ! ይሄኛው በፈጣሪ ቀመር ስለሆነ ወደጎን ትተን እኛ የምናወራውን የእኩልነት ኃሳብ ምንጩን ወይንም ታሪካዊ አመጣጡን አውቀን ብንቃወም አይሻልም!? እኩልነት የምንጠይቀው በዘር ፍሬ እና በጡንቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን ትምህርት በማግኘት፣ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ በአጠቃላይ ምድራዊ በሆኑ ሀብቶች ድርሻ ነው፡፡ ፈጣሪም ቢሆን እኮ ሴት ልጅ ከወንድ ልጅ እኩል ያለመማር፣ ምድር ላይ ያለውን ሀብት እኩል አለመጋራት፣የቤት ውስጥ ስራን ሙሉ በሙሉ መሸከም (አስባችሁታል በተለይ ውጪ ለምትሰራው ሴት ያለውን ድርብርብ ጫና)፣ በማህበረሰቡ ዝቅተኛ ሆና መቆጠር፣ መደፈር፣ መጠቃት የሚሉትን በገአዱ አለም የምናየውን ሰቆቃ ሁሉ መሸከም አለባት ብሎ አላሰመረላትም፡፡ ታድያ ለምን ይሆን ሳይገባን እየተቃወምን ያለነው!?

ቆይ ግን ወንዶችዬ እና አንዳንድ የክርክሩ አባሪ የሆናችሁ ሴቶችዬ ልጠይቃችሁ እስቲ፤ እኩልነት በጣም ነው እንዴ የምትፈሩት? ሴቶችዬስ ፌሚኒዝም በደንብ ገብቷችሁ ነው “እኔ ፌሚኒስት አይደለሁም!” የምትሉት? አንዷ በጣም የተማረች የምላት ሴት ጭራሽ “ምናምኒዝም (ism)” ያለበት ነገር አይመቸኝም አላለችኝም መሰላችሁ!? ታድያ እሷ እንደዚያ ካለችኝ በኋላ ትርጉሙን ፈልጌ በእንግሊዝኛ እንዲህ ተቀምጦ አገኘሁት፤

Historically, “ism” has evolved from the Greek suffix “-ismos,” which was used to form nouns indicating a state or condition. A word ending in ‘ism’ usually denotes a set of ideas about ‘big picture’ issues such as the nation-nationalism.

አና ጫፍ ይዞ መቃወም ግን በእኛ ደረጃ አልኩና ልሞግታት ብዬ ተውኩት፡፡ ሌላዋ ደግሞ የፌሚኒዝም ተቃዋሚ ነኝ የሚለውን ሀሳቧን ለማሳለጥ “እኔ እኮ እስከ አሁን የባሌን እግር የማጥብ ሴት ነኝ!” አላለችም!? “እንዴ ቆይ ምን አገናኘው?” ብዬ ልጠይቃት አልኩና ከአፌ መለስኩት፡፡ በትዳር ውስጥ እኮ አንዳችን የሌላችንን እግር ማጠብ ማለት የበታችነት ሳይሆን የመከባበር ምልክት ነው፤ ፌሚኒስት መሆን ደግሞ አለመከባበር ማለት አይደለም እኮ ወገኖች፡፡ እንግዲህ እግር ማጠብን እኩል ያለመሆንን (የበታችነት) ከሆነ በትዳር ውስጥ እኩል መብት የለኝም፣ ዝቅተኛ ነኝ እንደማለት እና ፌሚኒስት መሆን ይህን ይቃወማል የሚል ግንዛቤ ከሆነ ያለን “ምጽም!” ከማለት ውጭ ምንም የምለው የለኝም፡፡ ብቻ ያልገባን ነገር ብዛቱኮ! ወንዶችዬ ደግሞ (እኩልነትን የምትፈሩትን) አይዟችሁ፤ እንኳን እኛ ሀገር ይቅርና በታላቋ አሜሪካ እንኳን “የሴቶች እኩልነት ይረጋገጥ ዘንድ 100 ዓመት ይቀረናል” ብለዋል፡፡ እኛ ታድያ ከፈጠንን አንድ ዜሮ መጨመር ብቻ ነው፡፡ ግን እንኳን ደስ ያላችሁ አልላችሁም፤ ለእናተም እኩልነት ያልሰፈነበት አለም ሰላም አይሆንማ! ለዚህ ደግሞ እሩቅ አትሂዱ፤ያው የደከማችሁባቸውን የአብራካችሁን ክፋይ ሴት ልጆቻችሁን አለም ማሰብ ብቻ በቂ ነውና፡፡

እንግዲህ የስነ ጾታ እኩልነት አስፈላጊ ነው የምንለው እና እኩልነት ለምኔ የምንለው ሴቶች እራሳችን መሳ ለመሳ ስለሆንን ማርች 8 ታስቦ እና ተከብሮ ከመዋል ባለፈ ፋይዳ እንደማይኖረው አልጠራጠርም፡፡ ቆይ ግን በጆሮሽ ልጠይቅሽማ! ሴቷ ልጅሽ ተምራ ምን እንድትሆንልሽ ነው የምትፈልጊው? ለነገሩ ተምረው ጥሩ ስራ እየሰሩ በኢኮኖሚ ቤታቸውን ቀጥ አድርገው ከያዙት ሴቶች ይልቅ ሙሉ ጊዜአቸውን ለልጆቻቸው የሰጡትን እናቶች ጀግና እያልን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ለእኔ ሁለቱም በየምርጫቸው ጀግና ናቸው፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም ቀጥ አድርጋ በመያዝ ለቤተሰቡ የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም እና አሪፍ እናትነትንም አሳልጣ የያዘችው ሴት የበለጠ ሚዛን ትደፋብኛለች፡፡ የተሰጣትን 24 ሰዓት ያመጣጠነችበት መንገድ ያስደምመኛል፡፡ ነገ በትዳሩ ላይ እንከን ቢፈጠር (አያድርገው እና) ልጆቿን የማታስርብ ሰርታ ጥሪት የያዘች ሴት ትገዝፍብኛለች፡፡ ለማንኛውም ሁሉም የምርጫ ጉዳይ ነውና የሁሉንም ምርጫ የማከብር ሴት ነኝ፡፡

የተነሳሁት እኩልነት መጠየቅ ትክክል አይደለም ለሚሉ እንዲሁም ፌሚኒስት በመሆን ወንዶች ያገልሉኛል ብለው ለሚፈሩ ሴቶች ትንሽ ሀሳብ ለማጋራት ነበር፤ብዙ አወራሁ መሰለኝ፡፡ ለማንኛውም በቃ አንብቡና እወቁ! የስነ ጾታ እኩልነት ማለት ምን ማለት ነው፣ እኩል መሆን ማለት ምን ድረስ ነው፣ እኩልነት ለምን አስፈለገ፣ ፌሚኒዝም ማለትስ ምን ማለት ነው…ወዘተ የሚሉትን በደንብ አንብቡ እና ተረዱ፡፡ ከዚያ ደግሞ የእራሳችሁን ኑሮ ከሌሎች ሴት መሪዎች የአኗኗር ዘይቤ ጋር አወዳድሩት እና የት ድረስ መሄድ እንደምትችሉ ከቻላችሁ አስቡ አለበለዝያ ተወያዩ፡፡ ወገኖቼ የስነ ጾታ እኩልነት ማለት ለሴቶች መብት መቆም ብቻ ማለትም እኮ አይደለም፡፡ እንዴ ሴቷ የወሊድ ፈቃድ እንደሚያስፈልጋት ወንዱም የአስወላጅ ፈቃድ (paternity leave) ይጨመርለት ብለን እየታገልንለት እኮ ነው፤ ሌላም ልቀጥል!?

ለማንኛውም በዚህ ላብቃ እና ማርች ወርን በጥሩ ጥሩ መድረክ ያሳለፍን እህቶችም ወንድሞችም በተግባር ልናያቸው የምንፈልጋቸው የእኩልነት ጥርጊያ መንገዶች ላይ በጋራ እንስራ! በየዓመቱ ተሰባስበን መወያየታችን ከእለታት አንድ ቀን እኩልነታችንን ስለሚያረጋግጥልን ለዘላለም ይኑርልን! ለቀጣይ ዓመት ማርች ወር በሰላም ያድርሰን በሚል መልካም ምኞት ለዛሬ ጨርሻለሁ!

የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Share to your circles!

2 thoughts on “እኩልነት ለምኔ!”

  1. በጣም አስተማሪ ጦማር ነው…ፍፁም አመሰግናለሁ 🙏ፈጣሪ ማህፀንን ለሴት ዘርን ለ ወንድ ስሰጥ በምክንያት ነው :: ሁለቱም ማድረግ ያለባቸው ነገር አለ…. በሕይወት እስካሉ በሚያደርጉት ነገር ሁሉ ላይ የዉሳኔ ነፃነት እና ምክክር አስፈላጊ ነው… እኔ በበኩሌ….. ቤተሰቦቼ ያሳደጉኝ.. ያስተማሩኝ… እኔ ደግሞ ትምህርቴን Masters.. Postgraduate.. እያልኩ የቀጠልኩት አንድ መሆን.. ማድረግ ምፈልገው ማንነት ስላለኝ ነው.. Somebody’s ሚስት ብቻ ሆኘ ማለፍ አልፈልግም :: thanks.

  2. ሙሉጌታ ፀጋዬ

    ፍፄ ልክ ብለሻል አሁን እኮ ችግሩ ነገሮችን ከአዉድ ዉጪ የምንረዳበት መንገድ ነዉ በመሰለኝ የምንሄድበት መንገድ የት እንደሚያደርሰን አይታወቅም መዳረሻዉ የማይታወቅ መንገድ ደግሞ መጨረሻዉ የከፋ ነዉ ስለ እኩልነት ስታወሪ ስለተፈጥሮ ያወሩሻል በተፈጥሮ ደግሞ ቀድሞ የተፈጠረዉ ወንድ ነዉ ወንድም ለብቻዉ ምንም ማድረግ እንደማይችል እና ግማሽ ጎዶሎ ሰዉ በመሆኑ ሙሉ የታደርገዉን ግማሽ አካሉን ሴትን ፈጠረለት ሁለቱ አንድ ላይ ሲሆኑ ነዉ ሙሉ ሰዉ የሆኑት አብዛኛዉ ያገራችን ፌሜኒስቶች አረዳዳቸዉ እና አካሄዳቸዉ ተፈጥሮንም ለመጋፋት ነዉ የሚመስለዉ አንቺም በፁፍሽ እንደገለፅሺዉ ሴት ልጅ የባሏን የወንድሟን የአባቷን እግር ስታጥብ የበታችነት በደል አለመሰልጠን ተደርጎ ይታሰባል ይህንኑ ነገር ደግሞ ወንዱ ሲያደርገዉ መከባበር መተናነስን ፍቅርን ይገልፃል ታድያ እንዴት እንግባባ አንድ ተመሳሳይ ነገር በተመሳሳይ ሰአት ወንድ እና ሴት ሲሰሩት የተለያየ ትርጉም እየተሰጠዉ ሌላዉ ደግሞ ያገራችን ፌሚኒስትነን ባዮች የነሱ ፌሜኒስትነት መገለጫዋ ቤት ዉስጥም ይሁን ከቤት ዉጪ ተፈጥሮን የሚቃረኑ ነገሮችን ሲደርጉ ነዉ የሚታዩት በተፈጥሮ ለወንድ የተሰጠዉን እኛ ካላደረግነዉ ሲሉ ይስተዋላል

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top