ድምጽ አልባው ጦርነት

ይሄ ማህበራዊ ሚዲያ በጣም ብዙ ጥቅም ያለውን ያህል ጎጂነቱም ቀላል እንዳይመስላችሁ፡፡ እኔ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ እንደመሆኔ መጠን አንዳንዴ የፈለግኩትን ብቻ እያጣራሁ እና እያጠለልኩ ሳይሆን ከነድፍድፉ የምጋፈጥበት ሁኔታ አሌ አይባልም፤ ምክንያቱም አልጎሪዝሙ ክሊክ አድርጌ የምመርጠውን ብቻ ሳይሆን ያልመረጥኩትን ጭምር ስለሚያቀርብልኝ ነው፡፡ ደግሞ ሰዎች አይደለን እንጓጓለን፤ “ካመጣው ለምን አላይ አልሰማ!?” ብለን፡፡ ከዚያም በተጨማሪ “ምን አዲስ ነገር አለ!?” የሚል እንቅልፍ የሚነሳ የመረጃ ማነፍነፍ አባዜ አለ አይደል! እናላችሁ ሰሞኑን በፌሚኒስቶች እና በተቃዋሚዎች (ፀረ-ፌሚኒስቶች) መሀከል የሚደረገው አስደንጋጭ የቃላት ልውውጥ በቃ ድምጽ እልባ ጦርነት በሉት፡፡ ለነገሩ ድምጽ አልባ ያልኩት ተኩስ አለመማዘዛቸው እንጂ የሰሞኑ ዋነኛ የሚዲያው ሁካታ እሱ ብቻ ነው፤ከድምጽም በላይ የሆነ ሁካታ! በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ከማህበራዊ ሚዲያው አልፎ ዋና ሚዲያዎችን (mainstream media) መቆጣጠሩ አይቀርም፤ ለነገሩ እኮ ዋና ሚዲያዎች እራሱ መረጃቸውን ለማግኘት በእነዚህ ማህበራዊ ሚዲያ ቁጥጥር ስር ከዋሉ ውለው አድረዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ከረር ያለ ይሆንና ስጋት እንደሚሆን ይታየኛል፡፡

እናላችሁ በፌሚኒስዝም እና ፀረ-ፌሚኒዝም ቡድኖች መሀከል ያለው የከረረ ፀብ ሄዶ ሄዶ አሁን ላይ ፀረ ፌሚኒዝም አቋም ያላቸው ሰዎች የበላይነቱን የተቆጣጠሩት ይመስላል፡፡ ድሮም ብዙሀኑ ፌሚኒዝምን ከመፃረሩ የተነሳ መጨረሻው ላይ ‘ዝም-sm’ ያላቸው ቃላቶች ሁሉ አይመቹኝም እስከማለት የደረሱ እንዳሉ ጽፌያለሁ፡፡ ብዙሀኑ አይገደኝም ነገር ግን የተማሩ የተመራመሩ (elite) የሚባሉት አንብበው እና መርምረው ከመረዳታቸው በፊት ይህንን የጥላቻ መንፈስ በጭፍን መቀላቀላቸው እና ለንቅናቄው የተለየ ስያሜና ትርጉም መስጠታቸው እያስደነቀኝ ነው፡፡ ምን እንደሚሉ ታውቃላችሁ!? “ከፌሚኒስቶች ጀርባ ሌላ ተልእኮ አለ፣ የ666 ጥልቁ መንፈስ አራማጆች ናቸው፣ የሰዶማዊ አቀንቃኞች ናቸው፣ ፀረ ቤተሰብ ናቸው ስለሆኑም ነጠላ እናትነትን (single motherhood) ያራምዳሉ፣ ፍቺ ያበረታታሉ፣ አስቀያሚዎች እና ባል የሌላቸው ናቸው፣ የተማሩ እና ወንድ ጠሎች ናቸው፣ ኃይማኖት የለሽ (atheist) ናቸው” ወዘተ፡፡ አቤት ስታነቡትም ይሸክካል አይደል!? በነገራችን ላይ እንዲህ ያለውን ጭፍን ፍረጃ የሚሰጡት ጾታቸው ሁሉም ወንዶች አይደሉም፤ ሴቶችም ጭምር እንጂ! “እስቲ ቆይ ይሄ ነገር ምን ማለት ይሆን? በባህላችን፣ በኃይማኖታችን፣ በኢኮኖሚአችን፣ በአኗኗር ዘይቤአችን፣ በማህበራዊ እሴቶቻችን ላይ ምን ተጽእኖ ይኖረው ይሆን?” ብሎ በጥንቃቄ በማንበብ እና በመረዳት የሚተጋ እንዴትስ ጠፋ!?

ለነገሩኮ ሰዉም ላይ ሙሉ በሙሉ መፍረድ አይቻልም፡፡ በአብዛኛው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያሉት የፌሚኒስት ንቅናቄ አቀንቃኞች ከማህበረሰቡ ጋር እልህ የተጋቡ ይመስል አላማቸውን የሚያራምዱበት መንገድ ከረር ያለ ነው፡፡ ሰሞኑን አንዷ ፌሚኒስት ስለ በቤት ውስጥ በባል ፍላጎት ብቻ በግዳጅ የሚፈፀም ጾታዊ ግንኙነት ልክ ያለመሆን ስታወራ “ሰክቶ መውጣት” በማለት ከባህላችን ያፈነገጠ ቃልን በመጠቀሟ ብዙዎችን አስቆጥታለች፡፡ ሌሎችም እንዲሁ ትዳር ሳይመሰርቱ ወይንም ትዳራቸውን ፈትተው ልጆቻቸውን ያለ አባት ድጋፍ ማሳደግን አድቮኬት ሲያደርጉ ይደመጣሉ፡፡ ይሄንን እና መሰል ወጣ ያሉ አመለካከቶች ናቸው ማህበረሰቡን እያስቆጣ ያለው፡፡

የፌሚኒዝም ንቅናቄ መነሻው የእኩልነት መብት መጣስ ነው፤ የወንዶች እና የሴቶች በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና ማህበራዊ ተሳትፎዎች ያሏቸው የእኩልነት መብት ጥሰት የፈጠረው ንቅናቄ ነው፡፡ የዚህ ንቅናቄ መነሻውም ከእነ ፈረንሳይ እንግሊዝ እና አሜሪካ ነው፤ለንቅናቄው ምላሽ መስጠታቸው ዛሬ ለደረሱበት ልእለአያልነት አስተዋፆ እንዳለው አንክድም፡፡ ንቅናቄውም ሂደት ነበረው፤ የመጀመርያው ማህበል ሕጉ ላይ ሆኖ ፍትህ ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ባህላዊ እና ማህበራዊ እኩልነት ላይ ያተኮረ ነበር፤ሶስተኛው ማህበል ደግሞ ልዩነቶችን በማጥበብ ማለትም በኑሮ ደረጃ፣ በዘር፣ በኃይማኖት፣ በጾታ ምክንያት የሚፈጠሩ ልዩነቶች(diversity) ተቀብሎ በመከባበር መኖር ላይ ያተኮረ እንደሆነ ያነበብኳቸው ጥናቶቸ  ያሳያሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ወደ ሌሎቹ በተለይ የሶሺያሊዝም ርእዮት የሚከተሉ ሀገሮች እና አህጉራችን አፍሪካ የተዛመተው፡፡  ወደ እኛ ወደ አፍሪካውያን ስንመጣ እራሱን የቻለ የፌሚኒዝም ንቅናቄ ገጽታ አለ፤ የሌሎች ጥያቄ ያልሆነ የእኛ ብቻ የሆነ እንዲሁም የእነሱ ጥያቄ ሆነው የእኛ ያልሆኑ፡፡ ጥያቄዎች የሚኖሩት ደግሞ ያልተመለሱ መልሶች ስላሉ ነው፡፡ ታድያ ፌሚኒዝም ንቅናቄ ምን ይሆን ክፋቱ? ምንድነው እየካድን ያለነው? ክህደታችን እና መከፋፈላችን የምንፈልገውን የፍትህ ጥያቄ መልስ ያስገኝልን ይሆን ወይንስ ተደፋፍኖ እንዲቀር እና ከአለም ከአሁን በባሰ መልኩ ወደኃላ እንድንቀር ያደርገው ይሆን!?

እኔ ፌሚኒስት ነኝ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከላይ የጠቀስኳቸው የፍትህ መዛባቶች እና የመብት መጣሶች መኖራቸውን ስለማምን እና መልስ አግኝተው ማየት ስለምፈልግ የእራሴን ጠጠር ለመጣል ነው፡፡ እኔ በከተማ ተወልጄ በማደጌ ትምህርት ባገኝም 80% የሚሆኑት በገጠር የሚኖሩት የሀገሬ ሴቶች ትምህርት ሊያገኙ ቀርቶ በጨቅላ እድሜአቸው ለማያውቁት እና በእድሜ አቻቸው ላልሆነ ሰው እየተዳሩ ነው፣ ጾታዊ ጥቃት ገጠር ከተማ ሳይል በየጊዜው የምንሰማው እና የምናየው ፍትሕ ያላገኘ ጉዳይ ነው፣ ብዙ ሴት ተማሪዎች እና ሰራተኞች በነጻነት የማይንቀሳቀሱባቸው እውነታዎች የማይካዱ ናቸው፡፡ የብዙ ትዳሮች መፍረስ ዋነኛ ምክንያት ጥቃት፣ ድብደባ እና መገፋት ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ እኛ ካልታገልን ማን ይታገላል!? በነገራችን ላይ ለሴቶች መብት የሚታገሉ ፌሚኒስት ወንዶች እንዳሉ ታውቁ ይሆን!? ፌሚኒስቶችን የሚቃወሙ ሴቶች ምናቸውም ስላልተነካ ወይንስ በማህበረሰብ በተለይ በአቻ ወንዶች መገለል ፍራቻ? በአጠቃላይ ባልገባን ነገር ለፌሚኒስቶች የተለጠፉት ታጎች እና ጅምላ ፍረጃዎች ያሳዝኑኛል፡፡ እኔና እኔን መሰል ፌሚኒስቶች ኃይማኖት አለን፣ በቤተሰብ እናምናለን፣ ትዳራችንን እናከብራለን…ወዘተ፡፡

የማይገናኝ ነገር በናገናኝ ጥሩ ነው! ትኩረታችንን አንሳት! በነገራችን ላይ የፌሚኒዝም ንቅናቄ አይነቶች ወደ ሃያ አራት ሲሆኑ ሁሉም አይነቶች የእኛ ሀገር ሴቶች የመብት እና የእኩልነት ጥያቄዎች አይደሉም፡፡ ለምሳሌ የጥቁር ሴት ፌሚኒዝም ንቅናቄን ብንመለከት እኛን አይመለከትም ምክንያቱም በሀገራችን የነጭ የበላይነት አጀንዳችን ስላይደለ፡፡ ሌሎችንም የእኛ ሀገር ጥያቄ ያልሆኑትን መዘርዘር እችላለሁ፡፡ እናም በሀገራችን ብዙ መልስ የሚሰጣቸውን ጥያቄዎች መኖራቸውን ለማድበስበስ ወይንም ለመቅበር ሆነ ብለን በጥቂት ፌሚኒስቶች ምክንያት ፌሚኒዝምን ከማይሆን ፍልስፍና ጋር ባንለጣጥፈው መልካም ነው፡፡ እናንብብ፤ ጥናቶችን እንመልከት፡፡ እርግጥ ነው የሀገራችን ወንዶችንም ስጋት እጋራለሁ፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ሴቶች ፌሚኒስት ነን ካሉ መብታቸውን ከጠየቁ የተለመደው የሚስትነት መስፈርት ይንዱት ይሆናል፤ ለዚያ ደግሞ የተዘጋጀ የወንዶች ስብእና ላይኖር ይችላል፡፡ ወንዶችዬ የፌሚኒዝምን ጭራ ይዘው የራሳቸውን አጀንዳ (ካላቸው) የሚያራምዱትን ጥቂቶች ወደጎን ትታችሁ ትክክለኛውን ጥያቄ የሚያቀርቡትን ፌሚኒስቶች ተቀላቀሉ፤አብረን እና ተባብረን ለውጥ እናምጣ! የኑሮ አጣማጃችሁም እዚያ አብሮነት ውስጥ አለች፡፡ እናም ፍትሕ የሰፈነባት፣ ቤተሰብ የሚከበርባት ሀገር አብረን እናምጣ! ለዛሬ ጨርሻለሁ!

የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Share to your circles!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top