እየሞከርኩ ነው!

ሰሞኑን በጣም በብዙዎች የታየ፣ የተወደደ እና መነጋገርያ የሆነ ቪዲዮ ለዛሬ ጽሑፌ ከነርእሱ መነሻ ሆኖኛል፡፡ ላላያችሁት ግን ትንሽ ስለቪዲዮው ልንገራችሁ፡፡ አንድ አከራይ ተከራዩን መንገዱ ላይ ጠብቆ የቤት ኪራይ ሳይከፍል በመዘግየቱ እንዲከፍል ሲያስታውሰው ግራ የተጋባው ተከራይ ምርር ብሎ ሳይከፍል የዘገየበትን የተደራረበ ችግር የሚናገርበት አባባል ነው፤ “እየሞከርኩ ነው!” ማለቱ፡፡ ሁላችንም ችግሮቻችንን ለማሸነፍ እየሞከርን ነው፡፡ ግን ደግሞ ችግርን የሚቀርፍ ወይንም ፈቀቅ አድርጎ እና እፎይታ የሚያስገኝ ሙከራም እያደረግን ለመሆኑ ብዙዎቻችን እርግጠኞች አይደለንም፡፡ ታድያ “ሙከራችን ምን አይነት ቢሆን ነው?”
አንድ እውነት አለ፤ በየዘመኑ የኑሮ ውጣውረድን ለማሸነፍ የሚደረጉ የሙከራ ዘርፎች የሚለያዩ ይመስለኛል፡፡ ለዚህ እንደምሳሌ የማነሳው ነገር አለኝ፡፡ ድሮ ገና ስራ የጀመርኩ ዘመን የመጀመርያ መካሪዬ እናቴ ነበረች፡፡ በወቅቱ እናቴም የመንግስት ሰራተኛ ነበረች እና እኔ ስራ እንደጀመርኩ ለታክሲ የማወጣውን ወጪ ትቃወም ነበር፡፡ ምክንያቱም በዲፕሎማ ተመርቄ ስለነበረ ስራ የጀመርኩት ተቆራርጦ የሚደርሰኝ ደመወዜ አልበቃ እያለኝ ከእሷው ብድር እየጠየቅሁ ደመወዜን እዳ በመክፈል ነበር የምጨርሰው፡፡ ከወጪዎች አይቀሬ ከሚባሉት ትራንስፖርትን እንይ፡፡ እሷ በወቅቱ ለደርሶ መልስ ጉዞ በዘመናችን 0.30 ሳንቲም ብቻ በሚከፈልበት የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ስትጠቀም እኔ ደግሞ ለተመሳሳይ ርቀት (መ/ቤቶቻችን አንድ አካባቢ ነበሩ) ለደርሶ መልስ 2.40 ሳንቲም እከፍል ነበር፡፡ በወር 22 የስራ ቀናት አሉ ብለን ብናስብ ሁለታችንም በመረጥነው የትራንስፖርት አገልግሎት ዋጋ ልዩነት ብቻ ወጪአችን የተለያየ ነበር፡፡ እና በወቅቱ ደመወዜ አንሶኝ ስነጫነጭ ቢያንስ የትራንስፖርት ወጪዬን ለመቀነስ እንድሞክር ትመክረኝ ነበር፡፡ ወጪዬን ለመቀነስ የምሞክረው በአውቶቡስ ከመሄድ ይልቅ የተወሰኑ ኪሎሜትሮችን በእግሬ በመሄድ ነበረ፡፡ እናቴ በአውቶቡስ ሄጄ ገንዘብ እንድቆጥብ ስትመክረኝ ያልሰማኋት በወቅቱ ለእሷ ለመንገር የማልደፍረው ከግፊያውና ከመተፋፈኑ ባሻገር ይቀፈኝ የነበረው የጾታ ትንኮሳው ነበር፤ ቀላል ይተሻሻሉ እንዴ! ይህንን በአውቶቡስ የሄዳችሁ እህቶች ብቻ ናችሁ የምትረዱት፡፡
አሁን ደግሞ አማራጮች የበዙበት ዘመን ሆኖም ትራንስፖርት እንደልብ አይገኝም፡፡ ግን ወደተነሳንበት የ “እየሞከርኩ ነው!” ሀሳብ እንመለስ እና የአብዛኛው የአሁኑ ወጣቶች ገቢና ወጪ ያለመመጣጠን እያስተዋልኩ ነውና “እየሞከራችሁ መሆኑን እንዴት እርግጠኛ ናችሁ?” ብዬ ልሞግታችሁ ወደድሁ፡፡ ለምሳሌ ሰርታችሁም ይሁን ነግዳችሁ ከምታገኙት ወርሀዊ ገቢ ላይ ስንት ስንተኛውን ነው ትራንስፖርት ላይ እያወጣችሁ ያላችሁት!? የብዙዎች አማራጭ ኮንትራት ታክሲ (ራይድ፣ ፈረስ፣ ወዘተ) መጠቀም የሆነው አቅም ስላለ ነው ወይንስ ምቾት ቀዳሚ ስለሆነ!? በነገራችን ላይ እኔም የኮንትራት ትራንስፖርት አገልግሎቶች አድናቂ ነኝ፤ ግን የሁልጊዜ ተጠቃሚ አይደለሁም፡፡ መኪና ከመግዛቴ በፊትም (በእኛ ዘመን ላዳ ብቻ ነበር) በጣም ካልተቸገርኩ ኮንትራት ተጠቃሚ አልነበርኩም፤ ምክንያቱም እየሞከርኩ ስለነበር፤ የራሴን መኪና ለመግዛት! ለዚያ ደግሞ ማጠራቀም ነበረብኝ፡፡
ችግሮቻችንን ለማሸነፍ እየሞከርን በምንገኝበት ወቅት ዋናው እና አዋጩ መንገድ ከምቾት ቀጠናችን (comfort zone) መውጣት ነው፡፡ በምቾት ውስጥ ሆነን የምንሞክረው ሙከራ መዘናጋትን የሚያመጣ እና የማያተጋ ነው የሚል እምነት አለኝ፤ እምነት ብቻ ሳይሆን ተሞክሮም ጭምር፡፡ ብዙዎቻችን ሰርተን ለመለወጥ እየፈለግን መለወጥ ቅንጦት የሆነብን ከተለያዩ ምክንያቶች መሀከል በዋናነት ገቢና ወጪአችን ባለመመጣጠኑ ይመስለኛል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎትን በምሳሌነት አመጣሁት እንጂ ወጪዎቻችን የትዬለሌ ናቸው፤ ለመኖር መብላት መጠጣት፣ ለማደር አንገት ማስገቢያ ማበጀት፣ ለማደግ መማር፣ ማህበራዊ ኑሮ ወዘተ ዝርዝሩን አናንሳው፤ ሁሉሉ ወጪ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ውስስ ግን ለምሳሌነት የትራንስፖርት ወጪ አወጣጣችንን አልኩኝ እንጂ አመጋገባችን፣ አጊያጌጣችን፣ ተዝናኖታችን በአጠቃላይ ወጪ አወጣጣችን “እየሞከርኩ ነው!” ብለን በሙሉ ልብ አንዳንናገር የሚገታን ይመስለኛል፡፡ አመጋገባችን ያልኩበትን ምክንያት በምሳሌ ልንገራችሁ፡፡ ከብዙ ወጣት ሴቶች የምሰማው ወደ ስራ ሲሄዱ ምሳ ከቤት ይዞ መሄድ እንደማይወዱ እና የሚይዙ ሰዎች በተለይ ደግሞ ወንዶች ለእነሱ ዘመኑን ያልዋጁ ፋራዎች እንደሚመስሏቸው አጫውተውኛል፡፡ ከቤት የምንይዘው ምሳ በዋጋ አንጻር ብቻ እንኳን ከውጭ ገዝተን ከምንበላው ምን ያህል ዝቅተኛ እንደሆነ እና ለመቆጠባችን አንዱ ሙከራ እንደሆነ እንደምን ማስተዋል አልቻልንም ይሆን! ውጪ መብላት ደስ ይላል፤ ግን ሁልጊዜ ሲሆን አዋጭ አይደለም፡፡ ማጌጫዎቻችንም ከቀደሙት ጊዜያት በአንጻራዊነት በጣም ውድ መሆናቸውን እኛ ቀደም ብለን የኖርነው እናውቀዋለን፤ ያኔም አሁንም እያጌጥን ስለሆነ፡፡ በአጠቃላይ ዘመናችን “እየሞከርኩ ነው” ብለን የምንሞግትበት እንዳልሆነ ይሰማኛል፡፡
በነገራችን ላይ እውነተኛ ሞካሪዎች በደንብ ሕይወታቸው ሲለወጥ እያየን ነው፡፡ ሁላችንም በምናውቀው እና ሰሞኑን በመጣብን ዱብ እዳ ምሳሌ ልስጣችሁ፡፡ የአሜሪካ መንግስት በእርዳታ(aid) አማካይነት ወደሀገራችን የሚመጣ ገንዘብ ሲያቆም ያው ብዙ ፕሮጀክቶች እና መ/ቤቶች ጭምር በመዘጋታቸው ጥሩ ተከፋይ የነበሩ ወዳጆቻችን ስራቸውን አጡ፤ ገቢያቸውም ነጠፈ፤ ይህ መራር እውነት ነው፡፡ ይህ ይሆናል ብሎ ያሰበ ሰው ባይኖርም አንዳንዶች የሚያገኙትን ገቢ ከፍለው ኢንቨስት ያደረጉ በመሆናቸው ዛሬ ደመወዛቸው ባይኖርም ኢንቨስትመንታቸው በሚያስገኝላቸው ገቢ የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውን ሕይወት ብዙም ሳይንገጫገጭባቸው አስቀጥለዋል፡፡ እየሞከሩ ነበር ማለት ነው፤ ነገን ለማሸነፍ፡፡ ሌለኞቹ ያገኙትን ሁሉ ፍጆታ ያደረጉቱ በሰፊው የለመዱትን ሕይወት መኖር ባለመቻላቸው ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል፡፡ እነዚህኞቹ እየሞከሩ አልነበረም ማለት ነው፡፡
ውዶቼ እስቲ ቆም ብለን ወደእራሳችን የኑሮ ዘይቤ ጽብረቃ (refelection) እናድርግ! እኛስ ይህን ጥያቄ በየግላችን ብንጠየቅ “እየሞከርኩ ነው!” የምንልበት አቅም እና ቁመና ላይ ነን ይሆን!? ሕይወታችንን እየመራን ያለነው “ለነገ እራሱ ነገ ያውቃል!” እያልን ይሆን ወይንስ ዛሬም እኖርን ነገአችንን እያሰብን ይሆን!? በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰማይ ወፎችን ጠቅሶ ለነገ እንዳንጨነቅ ያስተምረናል፡፡ እኔ ትርጉሙ ስለነገ በጭራሽ ሳትጨነቁ ያገኛችሁትን ሁሉ ዛሬ ብቻ ጨርሱ ማለቱ እንዳልሆነ ተረድቻለሁ፡፡ ምክንያቱም ወፎችም እኮ ጎጆ የሚሰሩት የነገ ዝናብና ፀሐይ እንዳይመታቸው ነው! ለነገ ብለን ሰርተን እኛ ባንኖር እንኳን የሚኖሩ ቤተሰቦችና ወገኖቻችን ይጠቀሙበታል እኮ! ስለዚህ የእውነት የምንሞክር እና የምናደርግ ወይንም የምናሳካ መሆን አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዛሬ ጨርሻለሁ! ሙከራዬን አይደለም፤ ጽሑፌን እንጂ!
የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም
Share to your circles!