አትሞገሽ ያላት ፍጡር!

ሰው የሚለው ስያሜ ውስጥ ሁለታችንም አለን፤ ሴቶችም ወንዶችም፡፡ ነገር ግን ለአገላለጽ ስንጠቀመው ሰው የሚለውን ስያሜ በወንድ እንጠቀልለውና ሴቶችን እንዘላቸዋለን፤ ማለቴ እኛ ሴቶች እንዋጣለን፡፡ ለምሳሌ “ሰው መጣ” ስንል የመጣችው/የመጣው ሴት ወይንም ወንድ ሊሆን ይችላል፡፡ ያኔ ነበር ከመነሻው “ለምን?” ብለን መጠየቅ የነበረብን፡፡ ምክንያት ካላችሁኝ ኋላ ላይ ልመለስበት፤ አይሻልም? ወይንም ሳልመለስም ቢሆን ሀሳቤ ይገልፀው ይሆናል፡፡ ከዚያ በፊት ግን እንኳን ለአድዋ የድል መታሰብያ እና ለማርች የሴቶች ወር አደረሰን! ወቅቱ የአድዋ ድል የሚዘከርበት እና ተከትሎም የማርች ወር የሴቶች እኩልነት ይረጋገጥ በሚል ብዙ መድረኮች የሚዘጋጁበት እና እኛም የምንሳተፍበትም አይደል፤ እኮ!
የአድዋ ድል ሲዘከር ኢትዮጵያ ከፍ የምትልበት ትርክታችን ነው፡፡ የምር እድለኞች ነን፡፡ ኢትዮጵያን ግን እናት ሀገር ብለው በሴት የሰየሙ ሰዎች እነማን ይሆኑ!? ተሳስተው እንዳይሆን ግን ከምር ያሳስበኛል፡፡ ሀገሪቷ ወንድ እንጂ ሴት መቼ ተከበረባት፣ መቼ ተሞገሰባት!? ለነገሩማ አጼ ምኒሊክንም እምዬ ምኒሊክ ይሏቸው የለ! እንደ እናት ለማለት፤ ደስ ይላል፤ይሁን! ግን የአድዋ ድል የምኒሊክ እና የወታደሮቻቸው ሆኖ ነው አይደል በሰፊው የሚነገረው፤ እሳቸውም የእናት ኢትዮጵያ ልጅ ስለሆኑ እንኮራለን፡፡ ነገር ግን “አትሞገሽ” ያላት ፍጡር ከጎናቸው ነበሩ፤ ሴቷ እቴጌ ጣይቱ ብጡል! ብዙም አይነገርላቸውም አይደለ! በእርግጠኝነት እሳቸው የሰሩትን ገድል ሌላ ጾታ ቢሆን የሰራው መነገር ብቻ አይደለም ሀውልት ይቆምለት ነበር፡፡ አምርሬ ከሆነ የማወራው ልክ ነኝ፡፡ ሴት ልጅ አትሞገሽ ያላት ፍጡር ናት! ባይገርማችሁ የአድዋ ድል በዋናነት የእቴጌ ጣይቱ ስትራተጂያዊ ስልት ነው፤ ይህንን እውነታ ስንቶቻችን እናውቃለን ይሆን!? እንዲያውም ለአጼ ምኒሊክ የተዳሩላቸው በእድሜም፣ በትምህርትም በብስለትም ስለሚበልጧቸው አማካሪ እንዲሆኗቸውም ጭምር ታስቦ እኮ ነው፤ ከታሪክ እንዳነበብኩት፡፡ ሀገራችንን ሊያሳጣን የነበረው የውጫሌ ስምምነት ላይ ያለውን አንቀጽ 17 አንብበው እና ተረድተው ሲያበቁ እምዬ ምኒሊክን “አንቀበልም በላቸው!” ያሉት እሳቸው ናቸው እኮ! ባይገርማችሁ ብርቅዬዋን አዲስ አበባን በመመስረትም ግንባር ቀደም ናቸው፤ እቴጌ ጣይቱ ብጡል፡፡ ይህ ግን ጮክ ተደርጎ አይነገርም ምክንያቱም ሴት ልጅ አትሞገሽ፣ አትመስገኝ ያላት ፍጡር ናትና!
የጣልያንን ጦር ሰራዊት ውሀ በማስጠማትና በማዳከም የተገኘው ይሄ የአድዋ ድላችን ፍሬ ሀሳቡ የእቴጌ ነበር፡፡ እራሳቸውም ወደ 5000 ጦር ሰራዊት አሰልፈው ዘምተው እንደነበር ከታሪክ አንብበናል፤ እቤት ተቀምጠው ጀግናውን ባላቸውን “በድል ተመለስ” ብለው ሰስመው እያለቀሱ የሸኙ ሴት አልነበሩም፡፡ የተሳካ ጦረኛ ለመሆን መሰረታዊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ምግብ ነው አይደል? ምገባ የእቴጌ የጦር ቡድን የስራ ድርሻ ነበር፡፡ ታድያ የምግብ ዝግጅቱ ብቻ መሰላችሁ እንዴ ጦሩ እንዲበረታታ በሽለላ፣ በፉከራ፣ በዜማና በቀረርቶ አይዟችሁ እያሉ አቅም (ቲፎዞ) የነበሩት የእቴጌ ጣይቱ ሰልፈኞች ነበሩ እኮ፡፡ ቁስለኛ (ኢትዮጵያዊ ሆነ ጣልያናዊ) የሚያክሙት የእቴጌ ጣይቱ ሰልፈኞች ነበሩ እኮ፡፡ አድዋ ሲዘከር ይሄ ታሪክ ተቆርጦ ነው ቀሪው የሚተረክልን፡፡ ዛሬ ላይ በዋና ከተማችን የድምጻውያን እና ሌሎች ታዋቂ ሰዎች ሀውልት ተሰድሮ እንደምናየው ያህል እንኳን ክብር ተሰጥቷቸው ሀውልት አልቆመላቸውም ለእቴጌ ጣይቱ፤ ምክንያቱን ደግሞ አትሞገሽ ያላት ፍጡር እላችኋለሁ!
የአድዋ ድል በየአመቱ ሲዘከር በተስረቅራቂ እና ጣፋጭ ዜማዋ ነጋሪቱን የምትጎስምልን እስኪመስለን በጉጉት የምንጠብቃት ድምጻዊት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) “የሰው ልጅ ክቡር፣ ሰው መሆን ክቡር… እያለች ትልቅ አሻራ ትታለች፡፡ በዚህ ድንቅ ዜማ “ትናገር አድዋ ትናገር ትመስክር፣ ትናገር አድዋ ትናገር ሀገሬ፣ እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ!” ትለናለች፤ (በነገራችን ላይ አድዋንም ሴት አድርጋታለች ልክ እንደ ሀገር ኢትዮጵያ፤ ከፍቅሯ የተነሳ)፡፡ ታድያ ጂጂ በዚህ እና በሌሎችም ሀገርኛ፣ ባህልኛ እና ፍቅር ሰባኪ ዜማዎቿ ተሸልማ ይሆን? ባንክ በስሟ ቢሰየምስ ያንሳት ይሆን? ወፍ የለም አሉ የዘመኑ ልጆች! በአጠቃላይ እጅግ ብዙ ያልተዘመረላቸው ሴቶች ያሏት ሀገር ናት ያለችን፤ግን በቃ በዚች ሀገረ ምድር ወደድንም ጠላንም ሴት ማለት አትሞገሽ ያላት ፍጡር ነች!
ወደ ማርች የሴቶች ወር ደግሞ ላቅና፡፡ አሁን ሰሞኑን ቸብ እረብ የምንልበት መድረክ ይፈጠራል፤ እሱንም አያሳጣን መቼስ፡፡ ልክ ነዋ ቢያንስ በአመት አንዴ እንኳን ስለ እኛ እናውራ፣ ሲወራ እናዳምጥ፤ የሆነ የአንድ ሰሞን ግርግር ቢሆንም፡፡ እኔ ጥላቻ ለመስበክ አይደለም ይህንን ጽሑፍ የምጽፈው፡፡ መሞገሱ ቀርቶብን ያልታዩ፣ ቸል የተባሉ፣ የሴቶች ብቻ የሆኑ ጉዳቶች፣ ጥቃቶች፣ መገለሎች፣ ማሳነሶች እንዲያበቁ መሰራት ያለበትን ያህል እየተሰራ ያለመሆኑ ስለሚያንገበግበኝ ነው፡፡ ማርች ስምንትን ወይም የማርች ወርን ጠብቆ “ሴቶች እኩል የመማር፣ የማደግ፣ የመምራት፣ በኢኮኖሚው የመሳተፍ…ወዘተ እድል ይሰጣቸው” ከማለት ያለፈ ተግባራዊ ድርጊት ላይ ብዙ ይቀረናል፡፡
አንዳንድ መ/ቤቶች ውስጥ ሴቶችን እናብቃ ይባልና ትምህርት፣ ስልጠና፣ ሜንቶርሽፕ…ወዘተ የመሳሰሉት የማብቂያ እድሎች ከተሰጡ በኋላ ሴቶቹ መብቃታቸው ሲረጋገጥ የአመራር ቦታው ለካ በወንዶች ተይዘዋል፤ በቃ ምንም አይነት ትግበራ አይደረግም፡፡ ከምር ደግሞ ስታስቡት ወንዶቹ የት ይሂዱ? ግራ የገባ ነገር እኮ ነው! ማነው “ውረድና ሴቷ ትምራህ” ቢባል እሺ የሚል ወንድ!? እንኳን ሊወርድ ይቅርና የጀንደር ዲፓርትመንት ኃላፊ ተብሎ አዲስ ዲፓርትመንት ቢከፈት እንኳን ቀድሞ የሚያመለክተው እና የሚወዳደረው ወንዱ ነው፡፡ አንድ ሴት አክባሪ የሆኑ ወንድ ምሁር የወንዶችን ስልጣን መውደድ ሲያወጉን “ድከሙ ቢላችሁ ነው፣ እኛ ስልጣን እንወዳለን!” በማለት የነገሩንን ግልጽነታቸውን መቼም አልረሳውም፡፡ ለነገሩ እኮ ከስልጣኑ በፊት እኩል መብት የሚጠየቅባቸው ብዙ መሰረታውያን ነገሮች አሉ፤ ለእሱም ድከሙ ቢላችሁ ነው ካልተባለ በስተቀር፡፡
እንደዚህ በሀገር ጉዳይ እና በየመ/ቤቱ መሞገሱ ቀርቶ እኩል ባቆሙት ቤት እንኳን እኮ ሴቶች ለአቅመ ቁጥር አይበቁም፡፡ ለምሳሌ የአንድ መንደር ቤቶች ስንት ናቸው ለማለት “ስንት አባወራዎች አሉ?” ተብሎ ነው የሚጠየቀው፡፡ አስባችሁታል አባወራ የሌለበት በእማወራ የሚተዳደር ቤት ከሆነ ጭራሽ ከቁጥር ተፍቋል ማለት እኮ ነው፤አልያም በግዳጅ አባወራ ትባላለች፡፡ በአባወራ የሚጠራበት ቤት ያሉት ሴቶች ደግሞ በአባሪ ወይንም በአኗኗሪ ይቆጠራሉ፡፡ ቆጠራውም ይቅር! ልጆች እዚያኛው ቀዬ ለጨዋታ ቢሄዱ እና የማን ልጅ እንደሆኑ ቢጠየቁ አባታቸውን ነው መናገር ያለባቸው፤ እናትየዋን ማን ያውቃታል፤ ማንስ ሊተዋወቃት ይፈልጋል!? በተለይ ጎበዝ ልጅ ከሆነ/ከሆነች የሚሞገሰውና ያሳደገው ተብሎ የሚደመደመው አባትየው ነው፡፡
ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል፤ በዚህ ሁሉ የሴቶችን ስነልቦና ማንም ያሰበለት የለም፡፡ ለካ እኔም ጸሐፊዋ ሴት ነኝ! “ታድያ ምን ብናደርግ ይሻላል?” የሚለው ጥያቄ የተከሰተባችሁ ይህንን ጽሑፍ የምታነቡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታችሁ/የሚመለከተን ሴቶች እና የሴትን ስራ እና አስተዋጾ በማጉላት ላይ ያላችሁ ወንዶች አንድ ላይ በመሆን የሚከተሉትን አቋም ብንይዝስ?
1ኛ. ሴቶች ለሴቶች እርስ በእርስ እንደጋገፍ፤ አንዳችን የሌላችንን ጉድፍ የምናጎላ ከመሆን ይልቅ አቅም እንሁን፣ሜንቶር እንደራረግ፤ በስሜት እንደጋገፍ፣
2ኛ. እራስን ማሳደግ እና ማብቃት ላይ ትኩረት እናድርግ፤ ሁልጊዜ ሌሎች እድሉን እስኪሰጡን አንጠብቅ፣
3ኛ. ከሚደግፉን ወንዶች ጋር በመሆን ለተሻለ ለውጥ እንትጋ፣
4ኛ. በሙያ ማህበራት እና ክበባት ውስጥ በመቀላቀል በትስስር (Networking) የሚገኘውን ፍሬ በቀላል አንየው፤ እናጣጥመው፤ እንጠቀመው! ጥሩ ጥሩ መረጃዎችን እንለዋወጥ፣
5ኛ. ከእራሳችን እንታረቅ፣ ለእራሳችን ዋጋ እንስጥ! መብታችንን ከሰው አንጠብቅ! ለመሞገስ ባንታደልም ወደ ከፍታ እንወጣለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ያን ጊዜ እርስ በእርሳችን እንሞጋገሳለን! ደስ የሚለው ነገር እንደ ሴት፣ እንደ እናት፣ እንደ እህት(በተለይ ታላቅ እህት) ካልተሞገስን ብለን ተንጨርጭረን አናውቅም አይደል? “አትሞገሽ ያላት ፍጡር!” መሆናችንን በፀጋ መቀበላችን ካላስፈላጊ ጭንቀት (stress) ስለሚጠብቀን ጥሩ ነው ያለነው! ለዛሬ የዓመቱን ብሶቴን ይህን ያህል ካልኩ የዓመት ሰው ይበለን!
የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም
Share to your circles!
ጥሩ ሀሣብ ነው