ትዳር ፈሪዎች?!

ሰሞኑ የሰርግም አይደለ! በአንደኛው የሰርግ ስነስርዓት ላይ በክቡ ጠረጴዛ የተቀመጥን ሰዎች በሰዓት በመድረስ የማይታሙትን ሙሽሮች በመጠበቅ ውስጥ በነበረን ዘለግ ያለ ሰዓት በጋብቻ እና በሰርግ ርእሰ ጉዳዮች ዙርያ ላይ የያዝነው ወግ ጥሩ አቆያይን፡፡ መቼስ ይህ የሰርግና የጋብቻ ወግ ገራሚ ነው! ቆይ ግን ትዳር የሚፈሩ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ታውቃላችሁ!? ግልጽ ለማድረግ ጥላቻ እና ፍራቻን ለይተን እናስብ፡፡ በዚህ ርእስ የታቀፈው ፍራቻ የሚለው ነው፡፡ ልክ የተለያዩ ነገሮችን የሚፈሩ ሰዎች ፎብያ አለባቸው እንደሚባሉት እና የፎብያው አይነት ስያሜ እንደተሰጠው ሁሉ ትዳርን የሚፈሩ ሰዎችም ፍርሀት ጋሞፎብያ ያባላል፡፡ መቼስ ሳይንስ የማያጠናው ነገር የለም፡፡ እንግዲህ የትዳር ፍራቻም እንደማንኛውም የፍራቻ አይነት በቀላል የማይታይ ነገር ስለሆነ ለጥናት በቅቷል፡፡ ጉድ እኮ ነው እናንተዬ ለካሰ ያላገቡ ሰዎች ላይ ጅምላ ፍረጃ ስናደርግ የኖርነው ሁሉ ስህተት ኖሯል!? ለነገሩ የጅምላ ፍረጃ ትክክል የለውም! አግቢ/አግባ እያሉ መወትወቱስ ቢሆን በተለይ ለእኛ ማህበረሰብ እኮ እንደዘበት በአለፈ አገደመ ጣል የሚደረግ ቃል እኮ ነው! የማያገባው/የማታገባው እዚህም እዚያም ማለት ለምደው እኮ ነው ተብሎ ከአፈንጋጭ ልማድ ጋር ሲታሰርም ሰምተናል፡፡ ለማንኛውም ትዳር አለመመስረት የግል ጉዳይ ቢሆንም ለጠቅላላ እውቀት ግን አንዱ ምክንያት ይህ ፍርሀት እንደሆነ ባወቅኩት ልክ ጠቆምታ ለማድረግ ወደድሁ!
“ሸብ እረብ አለች ምድር…” የሚባልበት የሰርግ ሰሞን መቼስ ብዙ ያሰማናል፡፡ ሸብ እረብ ግን መሰረታዊ ቃሉ ከየት የመጣ ነው? ሳስበው ሸብ የሚለው ጠበቅ አድርጎ ከማሰር ጋር የሚገናኝ ይመስለኛል፤ እረብ የምትለዋን ግን ከምገምት ልለፋት! እና ጋሞፎቢያ ጥልቅ የሆነ የፍቅር ግንኙነትን እና ኃላፊነትን መፍራት እንደሆነ ነው ትርጉሙ የሚያመለክተው፡፡ የዚህ ፍርሀት ደግሞ መነሻዎቹ የተለያዩ ናቸው፡፡ ከእነዚህም በግንባር ቀደም የተቀመጠው ልብ ሰባሪ የሆነ የግንኙነት (የፍቅር ግንኙነት) መቋረጥ ወይንም ክህደት (መካድ) ሲሆን በተለይ የፍቅር ጓደኝነት በተደጋጋሚ በዚህ መልኩ ሲፈርስ/ሲናድ ፍርሀት ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ “በትዳሩ ምክንያት ነጻነቴን አጣለሁ” ብሎ መስጋት ነው፡፡ ከነአባባሉ “በትዳር ታሰረች/ታሰረ” ተብሎም አይደል የሚነገረን! ሦስተኛው በልጅነት ያጋጠመ ከትዳር ጋር የተገናኘ የመገለል ክስተት የሚፈጥረው የፍራቻ ስሜት ነው፡፡ አራተኛው ትዳርን የመመስረት አቅም እና አቋም (Economical and psychological) የለኝም በሚል በራስ መተማመን (Self Confidence) ማጣት ነው፡፡ አምስተኛው ምክንያት ደግሞ ማህበረሰቡ እና ባህሉ በትዳር ምስረታ ላይ የሚጥለው ከእውነታው አለም የራቀ ጫና ነው፡፡
በነገራችን ላይ የምናወራው ስለ ትዳር ፍራቻ እና ምክንያቶቹ ነው፡፡ ልብ በሉማ፤ ትዳርን አለመፈለግ ወይንም ደግሞ ከመነሻዬ እንደጠቀስኩት መጥላት ከዚህ ይለያሉ፡፡ ፍርሀት ማድረግ እየፈለግን ነገር ግን ከላይ በዘረዘርናቸው እና በሌሎችም ምክንያቶች ፈርተን ስንሸሽ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ትዳርን በመጥላት ምክንያት ከማይፈልጉ ሰዎች አንዷ ነበርኩ ብላችሁ ታምናላችሁ!? በተለይ አሁን ያለሁበትን ሁኔታ ለምታውቁ እውነት አይመስልም አይደለ? ምን ሆነ መሰላችሁ፤ ተወልጄ ያደግኩት አዲስ አበባ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል አካባቢ ነበር፡፡ የእኔ አባት በሕጻንነቴ በሞት ስለተለየ እና እናቴም እኔን የመጨረሻ ልጇ እንድሆን ስለወሰነች የወጣትነት እድሜዋን ያለትዳር ነበር የዘለቀችው፡፡ በነገራችን ላይ እናቴ በ16 ዓመቷ የፈቀደችውን አግብታ ስለነበር እኔን አራተኛ እና የመጨረሻ ልጇን ስትወልድ 30 ዓመት እንኳን አልደፈነችም ነበር፡፡ እናም ቤታችን ትዳር አልባ ነበር ማለት ነው፡፡ ልጅነቴ የሁለት መንደር ውጤት ሲሆን በተለይ ትንሽ ከፍ ካልኩ በኋላ የገባንበት መንደር በአብዛኛው በሚባል መልኩ ባሎች ሚስቶቻቸውን ከልጆቻቸው እኩል አስረው የሚገርፉ ነበሩ፡፡ ብቻ ምናለፋችሁ የኡኡታ ድምጽ ሲሰማ እናቴ እና አያቴ “ዛሬ ደግሞ ማን ትሆን የፈረደባት?” ይባባሉ ነበር፡፡ ኡኡታው ቶሎ ካልቆመ ጎረቤት ወጥቶ ለግልግል ይሰማራል፡፡ እናቴ ጤና ረዳት ስለነበረች የመጀመርያ እርዳታ (first aid) ቤታችን እየመጡ የሚሰጣቸውም ነበሩ፤ በዚያው “ነገር እስኪበርድ” አረፍ ስለሚሉ ጉርምርምታቸውን እንሰማ ነበር፤ “አሁንስ መረረኝ የት ልሂድለት፣ ለልጆቼ ብዬ እንጂ እኔስ ለአንድ እራሴ ብን ብዬ መጥፋት አያቅተኝም ነበር…ወዘተ” እያሉ አልቅሰው፣ አብርደው የሚሄዱ እናቶችን አንጀቴን እየበሉት ነው ያደግኩት፡፡ እናም የዚያን ጊዜው ጨቅላው አእምሮዬ ባል ማለት የሚደበድብ፣ የሚያቆስል፣ የሚያስለቅስ፣ የሚበድል ነበር እና “ባል አላገባም!” በሚል ቁርጠኛ ውሳኔ ነበር ያደግኩት፡፡ የዚህኛው ዓይነት ፍራቻ ምክንያታዊ ስለሆነ ጋሞፎብያ ውስጥ መጠቃለሉን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
ጋሞፎቢያ በሚል ጥቅል ስም የታሸግነው ኢ-ምክንያታዊ (irrational) የሆነ ነው ይለዋል፡፡ ለምሳሌ ከላይ የገለጽኩላችሁ የእኔ ገጠመኝ ባየሁት ነገር ላይ ተነስቼ ያዳበርኩት ጊዚያዊ ፍርሀት ስለነበር በጊዜ ሂደት ደብዝዞ ሀሳቤን ቀይሬ ወደ ትዳር ለመግባት ምንም አይነት ቴራፒ አላስፈለገኝም፡፡ ባለቤቴ ጓደኛዬ በነበረ ጊዜ ገና ለገና ትዳር ቢጠይቀኝስ ብዬም አልሸሸሁም፤ እንዲያውም እየቀረብኩት እና እያወቅኩት ሲሄድ “እንጋባ?” የምትለዋን ጥያቄ በጉጉት ጠበቅሁ እንጂ፤ እንዲያውም ፀሎት ሁሉ አድርጊያለሁ(ሚስጥር አወጣሁ እንዴ)! ጋሞፎብያ ግን ከዚህ ስለሚለይ የተለያዩ ዓይነት ቴራፒዎች በማድረግ እና በካውንስሊንግ እንደሚድን ነው ያነበብኩት፡፡ እንግዲህ ይሄ ትዳር ፈሪነት ከላይ በዘረዘርኳቸው የተለያዩ ምክኒያቶች በውሳኔያቸው ወይንም በአቋማቸው የፀኑትን እንጂ ትዳርን የማይፈልጉትን ሰዎች አይመለከትም፡፡ ምንም አይነት ፍራቻ ሳይኖርባቸው ትዳር መመስረትን የማይሹ እንዳሉ ልብ ይሏል! የምርጫ ጉዳይ ነው፤ እሱ ላይ አስተያየት አንሰጥም! እንግዲህ ትዳር ሲታሰብ ላብ ላብ የሚለን፣ የሚያጥወለውለን፣ ረዥም ግንኙነት የምንሸሽ፣ ነጻነታችን በትዳር የሚናጋ የሚመስለን፣ ፍቅር የማይዘልቁት ኃላፊነት መስሎ የሚታየን ነገር ግን ደግሞ በሰውኛ በተሰጠን ዘመን ውስጡ ገብተን ቤተሰብ ብንመሰርት የምንፈልግ ሰዎች ካለን ይህ የትዳር ፍራቻ ይወገድ ዘንድ ባለሙያ ብናማክር እና አስፈላጊውን ቴራፒ (ሳይኮቴራፒ) ብናደርግ ወይንም እንደየእምነታችን ብንፀልይ እና ከፍርሀታችን ብንፈወስ መልካም ይሆናል የምል ነኝ! በሉ ለዛሬ ጨርሻለሁ!
የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም
Share to your circles!