ትዳራችን ኮሽታ የለውምì

ድሮ ወደ ኮሌጅ ልገባ ስል ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ወደ ኮሌጅ ለመሄድ የሚያዘጋጅ መጽሐፍ ነው ተብሎ የታመነበትን የሲሳይ ንጉሱ ድርሰት የሆነውን “ሰመመን” አንብቤ እንድዘጋጅ ያደረጉትን የጓደኛዬ የገነት ወንድሞች በሕይወቴ ክብር መዝገብ ላይ ጽፌአቸዋለሁ፡፡ አስባችሁታል ገና ዩኒቨርስቲውን ዋና በር ስትረግጡ በስህተትም ተብላችሁ የማታውቁትን “እንዳንቺ አይነት ቆንጆ ሴት በዚህ ምድር አይቼ አላውቅም!” የሚሏችሁ ሲኒየር ተማሪዎች ሙድ እየያዙባችሁ እንደሆነ አይገባችሁም ነበር እኮ፡፡ ስንቷ ወጣት ሴት የፎርጅድ ፍቅር ሰለባ ሆናለች መሰላችሁ! ልክ እንደዚያው ደግሞ ትዳር ከመያዜ ጥቂት ወራት በፊት በቶስትማስተርስ ክለብ አብረውኝ አባል ከነበሩት ወጣት ተጋቢዎች አንዷ ሰላማዊት የጆን ግሬይን “Men are from Mars, women are from Venus” የሚለውን መጽሐፍ እንድናነብ በጠቆመችን መሰረት ሽማግሌ ከመላኩ ጥቂት ወራት በፊት ፉት አደረግኩታ! ምክር መስማት እንዴት አሪፍ መሰላችሁ!

እንዴ ይሄን ሁሉ ዝርዝር የማወራበትን ዋና ፍሬ ነገር ሳልነግራችሁ፤ እኔና ባለቤቴ የአስራ ዘጠነኛ ዓመት የትዳር ክብረበዓል በዚህ ወር አከበርን! አሜን ብያለሁ “እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳን አደረሳችሁ፣…” እንደምትሉ 100% እርግጠኛ ስለሆንኩ፡፡ አላችሁ አንዳንዶች ደግሞ 50 ዓመት ያከበረች መሰላት ወይ ብላችሁ ሙድ የምትይዙ! ተዉ ግዴላችሁም 19 ዓመት እኮ ትንሽ አይደለም! የግድ 5 ቁጥርን ማየት አለብን ካላችሁ እንግዲያው 570 ወራት ወይም 17100 ቀናት ማለት ነው 19 ዓመት በዝርዝር ሲሰላ! እኔ በበኩሌ እያንዳንዷን ቀን በድል ሂሳብ ነው የማስላት፡፡ ለዚህም ደግሞ አመስጋኝ ነኝ ፈጣሪዬን!

ዋናው ነገር ገና ላላገባችሁ ወጣቶች ወይንም አግብታችሁ የመጀመርያዎቹ አመታት ፈተና ለሆኑባችሁ አዲስ ተጋቢዎች ምስጢሩን ላጋራችሁ እወዳለሁ፡፡ መቼስ “ካልሆነ እፈታለሁ!” ብሎ ያገባ ወይንም የሚያገባ ሰው አለ/አለች ብዬ ስለማልገምት፡፡ ግምት ግን ጥሩ አይደለም አይደል? ስለማላምን በሚለው ይታረምልኝ፡፡

እንግዲህ ምን መሰላችሁ “ትዳራችን ኮሽ ብሎበት አያውቅም! አዎ 19 አመት እንዴት እንዳለቀም አናውቅም…” የምላችሁ እንዳይመስላችሁ፡፡ ቀላል ይንኮሻኮሻል እንዴ! እንዲያውስ ከትዳር የባሰ መንኮሻኮሽ የሚበዛበት ተቋም ይኖር ይሆን? ያው ትዳር ተቋም መሆኑን በዚያው እያስታወስኳችሁ ነው፡፡ ሁለት ተጋቢዎች የመሰረቱት ኃላፊነቱ የተወሰነ ይሁን ሼር ኩባንያ ብቻ እሱን ለሕግ ባለሙያዎች እንተወው፤ ብቻ ተቋም መሆኑን እናስምርበት፡፡

አስታውሳለሁ በተጋባን በሦስተኛ አመት ቶስትማስተርስ ክለብ እያለን ሲኒየራችን የነበረው አንደበተ ማሩ፣ በኤውብ የድርድር (negotiation) ስልጠና የሚሰጠው መስፍን “ስለ ትዳር ምስክርነት ለመስጠት በትዳር ውስጥ አስር ዓመት መዝለቅ ያስፈልጋል!” ሲል እጢዬ ዱብ ነበር ያለው፡፡ እኔ ሦስተኛ ዓመት ላይ ሆኜ ብዙ ያወቅሁ ስለሚመስለኝ “ትዳር ማለት በቃ ይሄ ነው!?” ብዬ የተዘበራረቀ ስሜት ውስጥ ነበርኩ፡፡ ከዚያ ደግሞ አንዳንድ ሀሳቦችም በጨዋ ደንብ ድምጼን አጥፍቼ አስተናግድ ነበር ዛሬ ለእናንተ የምዘረግፈው፡፡ ሀሳቡ ምን የሚል መሰላችሁ “እሱስ ምን በወጣውና ነው እንደዚያ ከደመቀ ቤተሰቡ ተለይቶ ከእኔ ጋር የሚኖረው? እኔስ እንዴት አስችሎኝ እንደዚያ ለአንድ ሌሊት አምኜ የማልለያትን እናቴን ትቼ ከእሱ ጋር ብቻ አድራለሁ?” የሚለው በጨዋ አስተሳሰብ ሲገለጽ ሲሆን ጭብጡ እድሜ ልክ ያኖሩንን ቤተሰባችንን ትቶ ከማናውቀው ሰው ጋር እድሜ ልክ ለመኖር የመፈራረሙ  አስገራሚነት ላይ ነበር፡፡

እንደዚህ ዓይነት ሀሳቦች በመጀመርያዎቹ ዓመታት የሚንሸራሸሩት ወንድ እና ሴት ከተለያየ ፕላኔት የመጣን መሆናችን እስኪገባን ድረስ ነው፡፡ ከገባን በኋላ መንኮሻኮሹን እንለምደዋለን፡፡ በጣም ሲገባን ደግሞ መንኮሻኮሹ ወደ መንከሻከሽ እንዳይሄድ ጥረት፣ ትጋት፣ ትእይንት(ተወና)…ብቻ የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ሳይታወቀን አስረኛ ዓመት ላይ እንደርሳለን፡፡ ለካ ያኔ ስለምንለምደውና እኛም ስለምንለማመድ ከነመንኮሻኮሹ የፍቅራችን ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደርሳለን፤ መተሳሰብ፡፡ ኮሽታው የቤተሰቡ አባል  ሆኖ ይቀጥላል፤ የከፋ አንከሻካሽ አያምጣብን እና በትዳሩ እንቀጥላለን! የእኛ ጥረት እንዳለ ሆኖ ግን የትዳር ጠባቂው እግዚአብሔር ነው!

እኔ ትዳር ውስጥ የመቻቻልን አስፈላጊነት አምናለሁ፡፡ መቻቻል ለትዳር ብቻ የተሰጠ አይደለምና፡፡ ማንኛውም የሰው ልጆች ግንኙነት የመቻቻል ድግሪው ይለያይ እንጂ በመቻቻል የታጠረ ነው፡፡ መቻቻል ግን የራሱ የሆነ ገደብ (boundary) አለው፡፡ ለምሳሌ እኔ ስለባለቤቴ መልካምነት ሳወራ ብዙዎቻችሁ (የምታውቁኝ) ሰምታችሁ ይሆናል፤ እሱም እንደዚያ እንደሚያወራ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰምቼዋለሁ፡፡ (አራራቅኩትና ስለመንግስታት ወይንም ለየብቻ ስለሚኖሩ ሰዎች የማወራ አስመሰልኩት እኮ!)  ይህ ማለት ግን ኮሽታ ወይንም የሀሳብ አለመግባባት ፈጽሞ የለንም ማለት አይደለም፡፡ ይሄ ይሰመርበት፡፡ እንዲያውም ሁልጊዜ በሀሳብ የምንግባባ ልንሆን እንችላለን ምክንያቱም ከተለያየ ፕላኔት መምጣታችንን አትርሱ፡፡ ቀላል ምሳሌ ልስጣችሁ ለምሳሌ እኔ እና እሱ አንድ ላይ የሆነ ቦታ እየሄድን የሚጠብቁን ሰዎች የት እንደደረስን ለማረጋገጥ ሲደውሉለት “እየደረስኩ ነው!” ይላል፡፡ ለእሱ እኔ በእሱ ውስጥ ተጠቃልዬ እንዳለሁ ነው የሚያስበው፡፡ እኔ ደግሞ “እየደረስን ነው!” ማለት ነበረብህ ብዬ አቧራ አስነሳለሁ፡፡ ይህ አቧራ 19ኛ ዓመቱ ከእኛ ጋር አከበረ፡፡ እኔ ደግሞ አንድ ነገር አስር ጊዜ እነግረዋለሁ፤ በቀጣይ ለአስራ አንደኛ ጊዜ ስነግረው “ደጋግመሽ ነገርሽኝ እኮ!” እያለኝ 19 ዓመት ሙሉ ወሬ ስደጋግምበት እኖራለሁ፡፡ መቻቻል ማለትም አይደል!

ነገር ግን ባልዬ እየጠጣና እየሰከረ እየመጣ የሚደበድበኝ፣ ሲፈልገው “አልመጣም የውጭውንም የቤቱንም በር በደንብ መዘጋቱን አረጋግጠሸ ተኚ” ብሎ ከእኔ ይልቅ የቤቱ መቆለፍ የሚያሳስበው ቢሆን፣ እዚያ ሰፈር አራርቆ ወልዶ  ወደእኛ ቤት እናቀራርባቸው ቢለኝ፣ እዚያም ሳይደርስ ቢወሰልት፣ የሰራውን በሱስ እያባከነ ቤቱን የሚያራቁት ቢሆን፣ የቤተሰብ (ሦስተኛ ወገን) ጣልቃገብነት አክባሪ ቢሆን፣ መማርና ማደግ አትችይም እንዲያውም ኤውብ እና ማንኛውም ፕሮፌሽናል ማህበር መሳተፍ አትችይም ሚስት ነሽና ሚስት ሁኚ አይነት አሰቃቂ ትህዛዛት አምጥቶ ቢጭንብኝ…ወዘተ ከዚያ ይህንኑ አጓጉል አመሎች እኔ ሚስቲቱ ባደርገው ብላችሁ ገልብጡትማ! እናሳ መቻቻልን አስባችሁታል? ምን ለማለት ነው ብዙ ትዳሮች የፍቺ ሰለባ የሆኑት ከመቻቻል በላይ የሆኑ እፀፆች በዝተውባቸው እንጂ ትዳሩንማ ማን ይፈታ ነበር!

ለማንኛውም ወጉን ላሳጥረው እና እኔ ይቺ ሚስት ለመሆን ያበቃኝ ከላይ የጠቀስኳትን መጽሐፍ አንብቤ የወንዶችን ጥቅል ባህርይ ከመረዳቴ በተጨማሪ እናቴን ጨምሮ የፈረሱ ትዳሮችን በማጥናቴ እና በመዘጋጀቴ ነው፡፡ እናም ከላይ የጠቀስኳቸው ጉምቱ ምክንያቶች አይምጡብኝ እንጂ ለጥቃቅን እና አነስተኛ ጸቦች እድል አልሰጣቸውም፡፡ ሲሞግተኝ በጸባይ እየሞገትኩ አንዳንዴም ስሌታዊ እጅ መስጠት እያደረግሁ ሕይወት እስከተፈቀደልን ይቀጥላል፡፡ ከመነሻው እኮ ባለቤቴን ያገባሁት አፍቅሮኝ እና አፍቅሬው፣ ሴት ነኝና ደፍሬ ባልጠይቀውም “አግቢኝ ብሎ በጠየቀኝ!?” ብዬ በጸሎት ሳይቀር ተመኝቼው ነው፡፡ ደግሞስ እንደ እኔ ያለች ደፋር፣ መድረክ ላይ የምትቆም፣ ሀሳቧን በነጻነት የምትናገር፣  እራሷ ላይ የምትሰራ…ወዘተ ሚስት ወዶ እና ፈቅዶ ያገባ በራሱ የሚተማመን፣ ሴት አክባሪ እና ጀግና ባል እንደሆነ አስባችሁታል!? ከዚህ በኋላም በዚሁ ከቀጠለ ገና እያከበርኩት እና እያነገስኩት የምዘልቅ ነኝ! ዛሬ በምርቃት ላጠቃልል፤ ትዳርን ለምትሹ ሁሉ ጥሩ ሚስት ሆናችሁ ከጥሩ ባል ጋር ያገናኛችሁ! ለባሎችም እንደዚያው! ኮሽታ የቤታችሁ አፍራሽ (አንከሻካሽ) ሳይሆን የሚያንጻችሁ ይሁንላችሁ!

የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

4 thoughts on “ትዳራችን ኮሽታ የለውምì”

  1. ጎበዝ!
    “ምን መንገር ያስፈልጋል ጎበዝ መሆኔንማ አውቀዋለሁ!” እንዳትዪኝ እንጂ?! “A woman of inherent inbuilt confidence!”

  2. ጎበዝ!
    “ምን መንገር ያስፈልጋል ጎበዝ መሆኔንማ አውቀዋለሁ!” እንዳትዪኝ እንጂ?! “A woman of inherently inbuilt confidence!”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top