ስለ ሴት መልካም አባባሎች!?

አንዲት የኤውብ ቤተሰብ የሆነች እህት ስልክ ደወለችልኝ እና “እስቲ ስለ ሴት የተተረቱ አዎንታዊ አባባሎች ንገሪኝ?” አለችኝ፡፡ ጥያቄው ቅጽበታዊ ቢሆንም ጊዜ ወስጄ ባወጣና ባወርድ በቶሎ ሊመጣልኝ አልቻለም፡፡ አስቤ ሳበቃ አሉታዊ የሆኑት እንደ “ሴት ሲበዛ ጎመን ጠነዛ” አይነቶቹ ከማንቋሸሽም አልፈው አጥንት ሰባሪ የሆኑት ብቻ ድቅን አሉብኝ፡፡ “እንዴ ለካ ለተረትም አልበቃንምና!” ብዬ በአግራሞት ብቻዬን ስብሰለሰል ቆየሁና ቆይ ለምን ከእኔ የተሻለ አማርኛ የሚያውቁትን ሰዎች አልጠይቅም አልኩና ባለቤቴን ጠየቅኩት “መልካም ሴት ለባሏ ዘውድ ናት!” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ነገረኝ፡፡ በፍጥነት ስለነገረኝ ደስ ቢለኝም እኔ የፈለግኩት ሀገራዊ አባባል እንጂ መች ይሄንን ሆነና!  “ይህም እኮ ንጉስ ዘውድ ካልጫነ ንጉስ ስለማይሆን እሱን ልታነግሰው ነው እንጂ ለእሷ?” ብዬ አሰብኩና ሀጥያት ማሰብ እንዳይሆንብኝ ተውኩት፡፡

ታድያ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ባሰብኩበት ቅጽበት የነፍስ አባታችን መጡልኝ፤ ከአማራ ክልል የመጡ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ብዙ የቤተክህነት አስተምሮቶች አማርኛ እና ግእዝ ስለሆኑ አባባሎች እንደሚያውቁ ገምቼ፡፡  አባ ስደውልላቸው ስልኬን ወድያው መለሱልኝ እና ከወትሮው ወጣ ያለ እና ያልጠበቁትን ጥያቄዬን አስተናገዱልኝ፡፡ እናም ብቸኛ ሆኖ የመጣላቸውን “የሴት እና የቄስ እንግዳ የለውም!” ብለው በመልካምነቱ ነገሩኝ፡፡ ይሄንንስ ማን አየ ብዬ በሆዴ “ግን እኮ የፈለግሁት መልካም አባባሎች ነው፤ ይሄማ በየደረሱበት ቄሱም እንዲያሳልሙ እና ጠበል እንዲረጩ ሴቷም ጓዳ ገብታ እንድትሰራ ነው ያው ሁለቱም እንዲያገለግሉ የተጣለባቸውን ግዴታ ነው የነገሩኝ” ብዬ ልሞግታቸው አልኩና ለካስ ለነፍስ አባት እንደዚህ ያለ ክርክራዊ ማብራርያ አይሰጥም ብዬ ዋጥ አደረግኩት፡፡

በቀጣይ ወደመጣልኝ ድንቅ አማራጭ ሄድኩ፤ እንደ መተንፈሻ የምጠቀምበት፣ ብዙ መልካም ጓደኞች ያፈራሁበት፣ እውቀት የማገኝበት እና የእኔንም፣ የማጋራበት፣ በጎ ስራዎችን የምሰራበት ዋና ሶሻል ሚዲያዬ ፌስቡክ፡፡ በፌስቡክ ጥያቄዬን ሳቀርብ የተሻለ ምላሽ አገኘሁ፤ ብዙም ባይሆን ተስፋ የማያስቆርጡ ጥቂት መልካም አባባሎች አግኝቻለሁ፡፡ በእርግጥ በትእግስት በመጠበቄ እንጂ የመጀመርያ ችኩሎቹ በተለይ ወንዶቹ ጓደኞቼ አሉታዊ የሆኑትን በመላክ አጥለቅልቀው አስደንግጠውኝ ነበር፡፡

እስቲ አብረን እንደንግጥ! የመጀመርያው መላሽ “ክፉ ሴት ውልቅልቅ እንደሚል የበሬ ቀንድ ናት” ነበር ያለኝ፤ እንዲህም ዓይነት አባባል አለ? ሌላኛው ደግሞ “በሴት እና በሌሊት የሚታወቅ የለም” የሚል አቀበለኝ፤ ሴት ልጅን የጨለማ ያህል ድቅድቅ የማትታወቅ የሚያደርግ አባባልም አለን ለካìì ብቻ ሁሉን መዘርዘር እናንተን ማድከም ነው፡፡ ታድያ ሲያልቅባቸው ነው መሰለኝ “ሴት ያቦካው ለእራት አይበቃም!” በማለት የአባባል ሽግግር አደረጉ እና ፈገግ አስባሉኝ፡፡ አባባሉ እኮ እንዲህ ሳይሸጋገር “ልጅ ያቦካው…” ነው፡፡ እኔ እራሴ “የሴት አጭር ሴት ወይዘሮ የወንድ አጭር አውራዶሮ!” ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ይሄ አግላይ እና አጉል አባባል ወንዶችን ለመሸርደድ የተሰላ መሆኑ ነው፡፡ ከሚያናድዱኝ አባባሎች አንዱ ነው ምንም እንኳን ርእሴ ስለ ሴቶች ቢሆንም፤ ማንም ቁመቱ ላይ ቅንጣት አስተዋጾ የለውማ! ለነገሩ ሴቷም ከረዘመች ሴት ወይዘሮ ላትሆን ነው ማለት እኮ ነው እንደ አባባሉ ከሆነ፡፡ ብቻ ብዙ አሉታዊ አባባሎች የተንሰራፈፉብን ዜጎች የመሆናችን ነገር ወቸው ጉድ ያሰኛል፡፡

ሴት ልጅ በማህበረሰባችን እና በባህላችን ውስጥ የማትወደስ በመሆኗ አኗኗሪ እንጂ መደበኛ ኗሪ ተደርጋ እንደማትታይ እኮ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነገር ነው፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች ስብጥር ያላት ሀገር ስለሆነች በሌሎች ብሔረሰቦች የሚነገሩ እና ያልዳሰስናቸው መልካም አባባሎች ካሉ አፉ በሉኝ!

ከላይ እንደገለጽኩላችሁ ተስፋ እንዳንቆርጥ ጥቂት አዎንታዊ አባባሎች አግኝቻለሁ ያውም ከወንዶችም ከሴቶችም የተውጣጣ፤ እና ለመጽናኛ ይሆነን ዘንድ ለምን አላጋራችሁም! የሴትን ብልሀት የውሀን ጉልበት ይስጥህ! ከሴት ብልሀትን ከጉንዳን ትእግስትን ተማር! ጀነት እናት እግር ስር ናት! ከጠንካራ ወንድ ጀርባ ጠንካራ ሴት አለች! ሴት የላከው ሞት አይፈራም (ስለሚያፈቅራት እና ስለሚያምናት ብለን እንውሰደው)! በሴት የበከረ የመከረ (ሴት ልጅ በኩር ስትሆን ባለጸጋ ታደርጋለች እንደማለት ነው)! ሴት የሕይወት ድምቀት! ሴት ለመላ፣ ጌሾ ለጠላ! ሴት ብታልም፣ የነገን ሕልም! ቤት ያለሴት፣ ከብት ያለበረት! ሴት ታውቅ፣ በወንድ ያልቅ (የሴት እውቀት ለወንዱ ውሳኔ ይጠቅማል እንደማለት)! ከሴት የመከረ፣ ከእግዜር የመከረ! የሴት ብልሀት፣ የጎራዴ ስለት አይረታም! የሚሉት ናቸው፡፡

እንግዲህ ስለ ሴቶች የተባለ የመልካም አባባል ወይም የተተረተ እጥረት የኖረበትን ምክንያት ወደኋላ ሄደን መፈተሸ ሳይኖርብን አይቀርም፡፡ አሁን እራሱ ይህንን ጽሑፍ እየጻፍኩ በቅርቡ አብዱኪያር  “አይዞህ” እያለ ያዜመውን እያዳመጥኩ ነው፤ መልእክቱ ደስ ስለሚል፡፡ ግን ወንዶችን ከውድቀታቸው እንዲነሱ ለማበረታታት የተዘፈነ ነው፡፡ መውደቅ በወንድ ብቻ ይመስል! (አጋነንኩ እንዴ!)  በቀደም እለት ደግሞ ዳዊት ድሪምስ የሚባል አነቃቂ ሰውዬ የጻፈውን መጽሐፍ ከገዛሁት ቆየት ስላለ እስቲ ላንብበው ብዬ ገና ስጀምረው በወንድ ጾታ “አንተ” እያለ ነው የጻፈው እናም በቃ እኔን አይመለከተኝም ወይንም አላካተተኝም ብዬ ማንበቤን አቁሜ ከደንኩት፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይህንን ጽሑፍ (ብሎግ) ለምታነብ ወንድሜ መጽሐፉን ልሸልምህ ፍቃደኛ ነኝ፤ ሸልፍ ላይ ከማስቀምጠው፡፡ እርግጥ ነው ለዚህ ሁሉ አባዊ ስርዓታችን ምንጩ ነው፤ እሱም እጅግ የተንሰራፈፈ ስለሆነ እና ለአንድ ወገን አመቺ ስለሆነ ለውጥ እስኪመጣ መቻል ነው፡፡ ዓለም መቼም እማዊ አትሆንም፡፡ ግን ደግሞ ሰዋዊ መሆኗ አይቀርም፤ ሁሉም ሰው እኩል የሚሆንበት፤ ሴት በአባሪነት በወንድ ስር የማትካተትበት እና እራሷን ችላ የሚነገርላት፣ የሚተረትላት፣ ስራዋ የሚመሰከርላት ዘመን ይመጣል፤ እኛ ባናየውም የልጅ፣ ልጅ፣ ልጆቻችን የሚያዩት! ለዛሬ ጨርሻለሁ!

የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Share with your circles!

2 thoughts on “ስለ ሴት መልካም አባባሎች!?”

  1. ፍፄ ብዙ ቁም ነገሮችን ፋስቡክ ላይ ስለምታጋሪን እናመሰግናለን እውነት ነው ስለሴት የተባሉት መልካም ነገሮች ውስን ናቸው ያሉትም ክለሳ ይፈልጋሉ ወደ ዳዊት ድሪምስ ስመጣ እሱ የትግረኛ ተናጋሪ በመሆኑ አንቺን አንተ እያለ እንደሚጠቀም ተመልክቻለው ግቢ ሌሎች ትግራውያን ይህንን ሲጠቀሙም ተመልክቻለው ከተሳሳትኩኝ እታረማለው፡፡በርቺ ጀግኒት፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top