ሙስና ወይንስ ጉቦ!?

Image source: https://www.freepik.com/free-photo/hands-passing-money-table-corruption-bribery_18642905.htm
የስራ ዘመኔን ወደኋላ ሄጄ ሳስታውስ በጣም የሚናፍቁኝ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከሰው ጋር አብሮ እንደመስራት ድንቅ ትምህርት ቤት አለ ይሆን!? እኔ በጭራሽ የለም ነው የምለው፡፡ ለምን መሰላችሁ ትምህርት ቤት (ኮሌጅ እና ዩኒቨርስቲን ጨምሮ) የምንማረው በተግባር የሚወርደው ተቀጥረን ስንሰራ ወይንም የራሳችን ድርጅት ኖሮን ቀጥረን ስናሰራ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ደግሞ እንደ ቀስተደመና ቀለም የተዥጎረጎርን ሰዎች አለን፤ የድርጅቱን አላማ ለማሳለጥ (በአዲሱ አባባል) የምንጣመር፡፡ እኔ በአብዛኛው የስራ ዘመኔ የቅጥር ሰራተኛነት ነው፡፡ በስራ ዘመን ብዙ ሰዎች ታገኛላችሁ፡፡ እንደብዛታችን አንዳችን ሌላችንን በደንብ ጠንቅቀን ሳንተዋወቅ ደግሞ ወደ ሌላ መ/ቤት እንሻገራለን፤ ባለንበት ብንቆይም ተሻጋሪዎችን እንቀበላለን፡፡ እኔ ደግሞ አዲስ ባህርይ እንደማወቅ የሚያስደስተኝ ነገር አልነበረም፡፡ እስቲ እንደመግቢያ የሩሲያዊውን ፀሐፊ ፊዮዶር ዶስቶቭስኪን ጥቅስ ጀባ ልበላችሁ፡- “Man is a mystery. It needs to be unraveled, and if you spend your whole life unraveling it, don’t say that you’ve wasted your time.” እናም እሱ እንዳለው ምስጢራዊ ማንነታችን ተገልጦ ስለማያልቅ እኛም እስትንፋሳችን እስክትቆም እየገለጥን እየተገለጥን እንኖርና እናልፋለን! በሰው ውስጥ ብዙ መልካም ባህርያት እንዳሉ ሁሉ መልካም ያልሆኑም አሉ፡፡ ዛሬ ስለእኛ ድብቅ ባህርይ በስራዬ ምክንያት ያሳወቀኝን (ምናልባትም ባልሰራ ኖሮ በወፍ በረር ብቻ የማውቀውን) ሙስና ወይንም ጉቦ ልናዘዝ ወደድሁ!
አንዳንዶቻችሁ “ምን ትናዘዣለሽ በልተሻል እንዴ!?” ስትሉኝ ውስጣችሁን ሰማሁት ልበል!? ከላይ እንደጠቀስኩት በቅጥር ብዙ ዘመን አሳልፊያለሁ፡፡ ልክ የማኔጅመንት ድግሪዬን እንደያዝኩ ቀጥታ ወደ ግዢ ክፍል ኃላፊነት ነበር ያደግኩት፡፡ መማር ደጉ! ቀጥታ ከላይብራሪያን ወደ ግዢ ክፍል ሰራተኝነት ግን አይከብድም!? እኔን አያድርጋችሁ እንዳልላችሁ ያለፈ ታሪክ ነው፤ብቻ በጣም ነበር የሚከብደው፡፡ ስራ ሳይሆን የሚከብደው በአይን የማይታየው በጣም ረቂቅ የሆነው በግዢ ስርዓት እንደዋና ቤተሰብ ተንሰራፍቶና ተደላድሎ ስለሚኖረው ጉቦ ወይንም ሙስና ጋር ግብግብ ነበር የሚከብደው፡፡ “ነበር” ያልኩት የዚያን ዘመን እየተረክሁ ስለሆነ ነው፡፡ ቆይ ግን ድሮ ስሙ ጉቦ ነበር አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሙስና የተባለው ለምንድነው!? ስሜቱ እንዳይነካ ይሆን? የትኛው ነው ቀለል ወይንም ከበድ የሚለው? “ጉልቻ ቢቀያይሩት ወጥ አያጣፍጥም” ያሉት አበው/እመው እኮ ሊቅ ነበሩ! ምናልባት ፈረንጆቹን ስለምንከተል ኮራፕሽን (corruption) የሚለውን ቃል ቀይረውት ይሆን!? ያው እሱ ራሱ ነው ብዬ ነዋ!
እናላችሁ የእቃ ግዢ ልምዴ እየተከማቸ እና እየካበተ ሲሄድ እኔም የተለየ ሰው ማለቴ ሲስተም እና እድገት ፍለጋ በተለያዩ መ/ቤቶች በኃላፊነት ሰራሁ፡፡ እናም መጨረሻ ላይ ያለእድሜዬ እራሴን በበቃኝ በጡረታ አገለልኩ! ከምሬ ነው የምላችሁ ተቀጥሬ ላለመስራት ዋና ምክንያቴ ይሄና ተያይዘው የሚመጡብኝ ግጭትና ፍጭቶች ናቸው፤ እንጂማ በስራዬ፣ በትምህርቴ እና በገቢዬ ማደጌ ሕልሜም አልነበር! ሕልሜን አቋርጬ እንደወጣሁ ቀረሁ እንጂ፡፡ “አይቶ እንዳላየ ዝም አልልም!” የምትሉት ነገር አይደለም፡፡ ምክንየቱም ጉቦ ማለት በዓይን የማይታይ፣ በእጅ የማይዳሰስ፣ በአንደበት የማይገለጽ፣ ድምጽ አልባ ረቂቅ መሳርያ ነው፡፡ ታድያላችሁ ማን ከማን ጋር በየት አቅጣጫ እንደተዋዋሉ ሳላውቅ እኔ ባይተዋር ሆኜ የምውተረተርባቸው ገጠመኞቼ ብዙ ነበሩ፡፡ “የሕይወቴ ቅኝት” የሚለው መጽሐፌ ላይ ከገጠመኞቼ ለማጋራት ሞክሪያለሁ፡፡ ብቻ ምናለፋችሁ የሰውን ማንነት ማወቅ ስለማይቻል ትወዛገባላችሁ፤ እንደመወዛገብ አስፈሪ ነገር እንደሌለ እንደ እኔ የደረሰበት ያውቀዋል፡፡ የግዢ ኃላፊ ስትሆኑ ከምትታዘቧቸው ለምሳሌ ጥራቱን የጠበቀ ናሙና (sample) በማቅረብ ዋጋ ሰብሮ ገብቶ ካሸነፈ በኋላ ጥራቱን ያልጠበቀ እቃ የሚያቀርብ ነጋዴ፣ በነጋዴው ማማለያ የሚማልሉ የስራ ባልደረባዎች ለነጋዴው የሚቶፍዙት (ቲፎዞ) ነገር፣ ከአንድ መሸጫ ሱቅ ሶስት የዋጋ ማቅረቢያዎች የሚያመጡ የግዢ ሰራተኞች (ያውም ከሌላ ሱቆች በጨመረ ዋጋ) ፣ ገና ይፋ ያልወጣ የግዢ ጨረታ መረጃ ተቀባብሎ ቀድሞ የሚወጣበት ኩነት…ወዘተ፡፡ እና ይሄን ሁሉ ትወና ማን እንደሚያደርገው ያወቃችሁ(ማወቅ እንኳን አይቻልም መጠርጠር እንጂ) ሰሞን ከጉቦኞቹ ይልቅ እናንተ የምትሸማቀቁበት፣ የምትሳቀቁበትና የቆማችሁበት ምንጣፍ እስክትወድቁ የሚጎተትበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አሪፍ ትርክት ይሰራላችሁና ከሳሻችሁ እና የሚፈርድባችሁ ይበዛል፡፡ “ላም ባልዋለበት…” እንዲሉ! እናም ስራውን ለቃችሁ ብን ትላላችሁ፤ ያው ያባርሯኋል ማለት ነው፡፡ ሲባረሩ መኖር ሲሰለቸችሁ እጅ ትሰጣላችሁ፤ወይ ከጀማው መቀላቀል አለበለዝያ መቀጠር አቁሞ ሙያ ቀይሮ በግል መስራት (እንደ እኔ)!
በመጽሐፌ ላይ እንደጠቀስኩት ጉቦ ለሀገራችን ድህነት ትልቅ አስተዋጾ ከሚያደርጉ ጎጂ ድርጊቶች አንዱ ነው፡፡ ሰዎቸ የግል ጥቅማቸውን ብቻ እያዩ ሀገሪቷን ወደ ገደል ጫፍ አድርሰዋታል፡፡ ዛሬ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመጻፍ የተወሰወስኩት ከዚህ ቀደም የኤውብ ብቁ ሴቶች (Women of Excellence) አንዷ የሆነችው ክብርት ፍሬአለም ሽባባው በማህበራዊ ሚዲያ ገጽዋ ላይ “ጉቦን እንዲሰራፋ የሚያደረገው ተቀባዩ ነው ወይስ ሰጪው ነው?” በሚል ጥየቄ ካነሳች በኋላ ምክንያት ያለቻቸውን እንደምርጫ በሰባት ነጥቦች ዘርዝራ በማስቀመጥ “መፍትሔውስ ምንድነው?” ብላ ለውይይት ክፍት ያደረገችው ጽሑፍ ነው፤ብሶቴን ክፉኛ ቀሰቀሰብኝ፡፡ ጉቦ ወይንም ሙስና የሚጠፋው ሰጪና ተቀባይ ሲጠፋ ነው፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ ከሁሉም በላይ የሀገር ሰላም ይቀድማል፡፡ ሀገራችን ከእርስ በእርስ ጦርነት ወጥታ ትኩረት ወደ ልማት ሲሆን የለማች ሀገር ደግሞ ጥሩ ሲስተም ይኖራታል፡፡ ሲስተም ውስጥ ደግሞ ጠንካራ ሕግ ይኖራል፡፡ ይህ ከሆነ የሀብት ክፍፍልም ፍትሐዊ ይሆናል፤ ያን ጊዜ ድህነት ይጠፋና ጉቦ አማላይነቱ ይቀራል፣ እናም ሁሉ መልካም ይሆናል የምል ነኝ! የሆነ ሕልም የሚመስል ምኞት መሰለ አይደል! ሲስተም ምንድነው ካላችሁ ወደኋላ ሄዳችሁ “ሲስተሙ” በሚል ርእስ ያደገች ሀገር ጎብኝቼ ስመለስ በተከታታይ በዚሁ ድረ-ገጽ የከተብኩትን እንድታነቡ ጋበዝኳችሁ፡፡ እንግዲህ ከመነሻዬ ከሰው ጋር መስራት ት/ቤት ነው ያልኳችሁ ለዚህ ነው፡፡ ጥሩ ጥሩውን ብቻ ሳይሆን ጥሩ ያልሆነውንም እንማራለን፣ እንመራመራለን፤ ግን አውቀን አንጨርስም፡፡ ሰው ማለት ተገልጦ የማያልቅ ነውና! ዋናው ነገር ግን ሙስና ወይንም ጉቦን በተመለከተ ተዋናይ ሆኖ ባለመገኘት የእራስን ድርሻ መወጣት ለምንፈልገው የሲስተም ለውጥ አስተዋጾ አለው፡፡ እኛ ባንደርስበት ልጆቻችን የተሻለች ሀገር ትኖራቸው ዘንድ! ለዛሬ ጨርሻለሁ!
የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም
Share to your circles!