ሀሜት እና ሴት!

ሰሞኑን ሁለት ታዋቂ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎች በሀሳብ ሳይግባቡ ቀርተው ኖሮ የብእር ጦርነት ገጥመዋል፤ በአካል የሚተዋወቁ እንኳን አይመስለኝም፤ ምክንያቱም አንደኛው ኑሮው ከሀገር ውጭ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ ጦርነቱ እየተጋጋለ መጥቶ (እንኳንም በአካል አልተገናኙ) የቃላት ድብድብ ጀምረዋል፡፡ አንደኛውን በጣም ስለማውቀውና ስለማከብረው የእሱን ብቻ የመልስ ምት ነበር የማነበው፡፡ ይህ የማከብረው ሰው ግን ያኛውን ለማጣጣል “ሀሜተኛ ነህ፣ እንደ አንተ አይነቱ ሀሜተኛ ደግሞ ሴት ይባላል፤ ከዚህ በኋላ ሙናዬ ብዬሀለሁ” ብሎ ጻፈ እና ከልቤ ደነገጥኩ፡፡ አንዳንድ የተለመዱ ሴትን የሚያጣጥሉ አባባሎች አብረናቸው ብንኖርም ከምናከብራቸው እና ከምናደንቃቸው ሰዎች አእምሮ ፈልቀው ሲነገሩ ወይንም ሲጻፉ ያስደነግጣል፡፡ “ሕዝበ አዳሙ በቃ ሴቶችን ማሳነሱ ከደሙ የተዋሀደ ነው ማለት ነው?” ብዬ አስብና መልካም ሕዝበ አዳሞችን አብሮ መውቀስ አግባብ እንዳይደለ ሲታወሰኝ እታቀባለሁ፡፡ ሀሜት እና ሴት ግን ማነው ያጋባቸው!? ሀሜት ግን የሴት ብቻ ይሆን?

በቅጥር ዘመኔ የተለያዩ መ/ቤቶች የሰራሁ እንደመሆኔ መጠን የአሰራር ስልቶችን የተማርኩትን ያህል ስለሰዎች የሀሜት ባህርይም ጠንቅቄ ለማወቅ የቻልኩ ይመስለኛል፤ እውቀት ከተባለ፡፡ ብዙ መ/ቤት መስራት ብቻውን ስለሰዎች የሀሜት ባህርይ ሙሉ በሙሉ እንድናውቅ ላይረዳን ይችላል፤ ግን ስብእናችን ማለቴ ከሰው ጋር የመግባባት ችሎታችን ፈጣን የሆንን ሰዎች የሀሜት ተጋላጭ ማለቴ ሀሜት አዋቂ ያደርገናል፡፡ እኔን የምታውቁኝ ደግሞ ባህርዬ ለመግባባት የተፈጠርኩ እስኪመስል ድረስ ነው ፍጥነቴ፤ ግን የምወደው ባህርዬ ስለሆነ ባልኮራበትም ደስተኛ ነኝ፡፡ መግባባቴ ብዙ ሰዎችን ስለሚያደራርሰኝ ብዙ ሀሜት አዳምጫለሁ፤ ተሳትፌም አውቃለሁ፡፡ ሀሜት አብዝቶ ስለ ሌላ ሰው ማውራት ስለሆነ ወሬንና ሀሜትን ማህበረሰባችን ከሴት ጋር አያይዞታል፡፡ ሀሜተኛ ወንድን ለመግለጽ ሴት ይመስል ወይንም ይሄ ደግሞ ሴት የሆነ ይባላል፡፡ እውነታውስ?

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ሀሜት ሰውኛ የሆነ ባህርይ ስለሆነ ከሴት እና ከወንድ ማን ብዙ ያማል ለሚለው ጥያቄ “ሁለቱም እኩል ያማሉ፤ የሀሜታቸው ርእሰ ጉዳይ ይለያይ ይሆናል እንጂ!” ይሏችኋል፡፡ የሀሜት ርእሰ ጉዳይ ላይ ሴቶች ስለ ሌላ ሴት፣ ስለወንድ፤ ስለአለቃ እና ሰው ነክ ነገሮች ላይ አብዝተው የሚያሙ ሲሆን ወንዶች ደግሞ ስለቢሮ ፖለቲካ፣ ስለአለቆች፣ ስለሀገራዊ ፖለቲካዎች ወዘተ አብዝተው እንደሚያሙ ተረጋግጧል፡፡ እሄ በጥቅሉ እንጂ ወደ የአካባቢያችን ስናወርደው የተገላቢጦሽ ወይንም የተደበላለቀ ሊሆን ይችላል፡፡ ታድያ እነዚሁ ጥናቶች እንደሚነግሩን የሰው ልጅ ስለ ሌላ ሰው ሀሜት ሲያደርግ በቀን ከአንድ እስከ ሁለት ሰዓት ሊያጠፋ ይችላል ይላል፡፡ እንግዲህ ጥናቶቹ አለማቀፍ ስለሆኑ ወደእኛ ሀገር ሲመጣ በሀሜት የተሻለ ብዙ ጊዜ የምናጠፋ ዜጎች ስለሆንን (አትቀየሙኝ አደራ) ከዚያም በላይ እናጠፋለን ማለት ነው፤ ሴቶችም ወንዶችም፡፡ ለዚህ ደግሞ እኔ ከጥናቶቹ በተጨማሪ ሀሜትን በአካል ቆሞ ያየሁትን ያህል አረጋግጥላችኋለሁ፡፡ እንዴት በሉኝ?

በተለይ ስለሀሜት ሳስብ 10 ዓመታት የወጣትነቴን ዘመን በስራ ያሳለፍኩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ ድቅን ይልብኛል፡፡ ሴቶቹም ወንዶቹም በጣም በትምህርት የገፉት ምሁራኖቹም፣ መጠነኛ ትምህርት ያላቸውም (መቼስ ያልተማረ የለም ብለን ስለምናስብ እንጂ መደበኛ ትምህርት እስከ 12 ያልጨረሱ ሰራተኞችም ነበሩ) ብቻ ሁሉም ስለ ሌላ ሰው በደንብ ጊዜ ወስደው ያማሉ፡፡ አንዳንዴ ሀሜቱ በምሳ እረፍት ከተጀመረ እና ካላለቀ አድሮ ለነገም የምሳ ማባያነት ይቀጥላል፡፡ ለሀሜት አጀንዳነት የሚቀርቡት ደግሞ ከዚያው አብረው ምሳ ከሚበሉት ውስጥ በሌሉበት ሊሆን ይችላል፡፡ ዞር ሲሉ ይታማሉ፤ ሲመለሱ እነሱ ደግሞ በአዲስ የሀሜት ርእሰ ጉዳይ ሌላ ለማማት ይቀላቀላሉ፤ ብቻ ምናለፋችሁ አብሮ እየበሉ እየጠጡ መተማማት የተንሰራፋበት ያ ዘመን እና የስራ አካባቢ መቼም ከአእምሮዬ አይወጣም፡፡ ሀሜትን ከሴት ጋር አጋብቶ እየተነገረው ሲሰማ ያደገው አእምሮዬን ያስተካከለልኝ የወንዶችንም ሀሜተኝነት ያረጋገጠልኝ ባለውለታዬ የሆነ ዘመን!

ይሄን ሁሉ ያስወራኝ የማህበራዊ ሚዲያ ጓደኛዬ ታድያ እንደምን ፀበኛውን “ሴት የሆንክ ሀሜተኛ” አለው!? የወንድን ሀሜተኝነት በወንዶች ተከሽኖ ያየሁት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ረዘም ያለ የስራ ሕይወቴ ይሁን እንጂ እኮ በየገባሁባቸው መ/ቤቶች የሴትም የወንድም ሀሜተኞችን አይቻለሁ፡፡ ታድያ የተማረውና የማከብረው እንደእኔው በተለያዩ መ/ቤቶች በቅጥር ያገለገለው ጓደኛዬ ስለምን ሀሜትን ሴታዊ አደረጋት!? ለነገሩ ማህበረሰባችን (ከጥቂት መልካም የማህበረሰባችን አባላት በስተቀረ) አነስተኛ እና ጥቃቅን ባህርያትን እና ስያሜዎችን ለሴት መለጠፍ ልምድ ሆኖባቸው እንጂ ለክፋት አይደለም የምትሉኝ እንዳላችሁ አውቃለሁ፡፡ ደግሞ እንደ እኛ ዓይነቶቹን እንደዚህ አይነት ሴትን የሚያሳንሱ ስያሜዎች እና አጠራሮችን የምንቃወም ሴቶችንም ምን ብላችሁ እንደምታብጠለጥሉን አይጠፋንም፡፡ እኔ አላዝንም፤ ካዘንኩም የማዝነው ለእንደዚህ ያሉ ሰዎች ነው፡፡ ለምን እንደሚያሳዝኑኝ ማወቅ ትፈልጋላችሁ!?

እንደ እነዚህ  ያሉት ሕዝበ አዳሞች ሀሜትን እና የመሳሰሉትን ጥቃቅቅ የሰው አሳናሽ ባህርያትን የሴቶች ናቸው ብለው ብይን ሲሰጡ እና ሲቀስሩብን ከሕይወታችው እሩቅ ወደ ሆንነው  ወደ እኛ ከመድረሱ በፊት ወላፈኑ አስቀድሞ ዘጠኝ ወር አምጣ የወለደቻቸውን እናታቸውን፣ በተኙበትን የእናታቸውን ማእፀን የተጋራቻቸውን እህታቸውን/እህቶቻቸውን፣ ግማሽ አካላቸው የሆነችውን ሚስታቸውን እና የአብራካቸው ክፋይ የሆነችውን/የሆኑትን ሴት ልጆቻቸውን እንደሚገርፋቸው አለማሰባቸው ያስገርመኛል፡፡ ሰው እንዴት በዚህ ልክ ይሸወዳል!? ለዚህ ነው የሚያሳዝኑኝ፡፡ የፈለገ ግለኛ የሆነ ሰው ቢሆን ስለ እነዚህ ቤተሰቦቹ ካልተጨነቀ እና ካልራራ አዳማዊ ሰው መሆኑ ያጠራጥራል፡፡ ጽሑፌን ለማጠቃለል ሀሜት ሰውኛ እንጂ ሴተኛ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ሀሜት ሁሉ አሉታዊ ላይሆን ይችላል፤ አዎንታዊ የሚሆንበት ጊዜም አለ፡፡ ትዝ ይለኛል አንድ መ/ቤት እያለሁ በትምህርት ዝግጅት እና ልምድ ከሌሎች የማትበልጥ እንስት ያለውድድር ለከፍተኛ የስራ መደብ ተመረጠች እና መራጮቿም እሷም ለከፍተኛ ሀሜት ተዳረጉ፡፡ ሀሜት የሆነውም ማንም ሰራተኛ ሹመት ሰጪውን ፊት ለፊት መጋፈጥ ስላልደፈረ ነበር፡፡ ሹመት የተሰጣት ሴት ግን የስሚ ስሚ የመታማትዋ ወሬ ደረሳት፡፡ ከሀሜት ባለፈም ያኮረፏት ነበሩ፡፡ ሹመቱ ላይ ወቆየት ባትችልም አውርዱኝ ማለትም አልቻለችም ነበረና ወደ ሌላ መ/ቤት ገባች፤ እናም አስባው ያልነበረውን ትምህርት በመማር የጎደላትን አሟልታ ስራዋን ቀጠለች፡፡ የሹመቱም ሆነ የሀሜቱ አካሄዱ አግባብ ባይሆንም ለእሷ ግን ጉድለቷን ስለሞላችበት “ሀሜትን ያኑረው!” ማለቷ ይቀራል ትላላችሁ!? ለማንኛውም ወገኖች ሀሜት የግለሰቦች ባህርይ ነው፤ ግለሰቦቹ ወንዶችም ሴቶችም ሊሆኑ ይችላሉ እና ሀሜትን ቀሚስ ባናለብሰው ጥሩ ነው! በቃ ሀሜት ጾታ የለውም!  ለዛሬ ጨርሻለሁ!

Share to your circles!

1 thought on “ሀሜት እና ሴት!”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top