የ 15 ዓመት ባለልደቷ ጉብል ገራችኝ!

በሕይወታችን ውስጥ አቅጣጫ በማስያዝ፣ በመምከር፣ በመዝከር፣ በመደገፍ፣ እንዲሁም በመገሰጽ ትልቅ ድርሻ ያላቸው ሰዎች በአብዛኛዎቹ ታላላቆቻችን ናቸው፡፡ ምክንያቱም ከተኖረ ሕይወታቸው ቆርሰው ስለሚሰንቁልን፡፡ አንዳንዶች አሉ ወጣቶች ሆነው ታናናሾች ሆነው የታላላቆችን ሚና የሚጫወቱ፤ ሕይወት መቀየር ብቻ አይደለም የመኖርን ትርጉም ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ፡፡ ደግሞ እንዲህ ስል አንዳንዶቻችሁ ከአብራካችሁ የወለዳችኋቸውን ልጆቻችሁን እያሰባችሁ ይሆናል፤ እነሱ ደስታን በመስጠት የመኖርን ትርጉም አቅጣጫ ፈልገን እንድናገኝ ምክንያት ናቸውና፡፡ እኔ የማወራው ከሌላ ሰው አብራክ ተወልደው ለብዙሀን የተረፉ ታናናሾችን ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ደግሞ አሉ እንዴ ካላችሁ ኑ ተከተሉኝ ማለቴ አንብቡኝ!
ይህቺ ታናሼ ሳትገራኝ በፊት እኔ ማን ነበርኩ!? ምንስ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነበርኩ!? የሚለውን በትንሹ ላውጋችሁ፡፡ ማህበረሰባችን ሴት ልጅ አይኗን ሰበር አድርጋ ድምፅ ሳታወጣ (ታፍና) እንድታወራ፣ ቀጥ ብላ ከመሄድ ይልቅ አንገቷን ሰበር እንድታደርግ፣ አደባባይ ቆማ እንዳታወራ ቢቻላት ሸፈንፈን እንድትል ብቻ ገደባገደብ አስምሮ በጨዋነት ጠቅልሎ ባሸከማት ቀንበር ውስጥ መቀንበር ያልቻልኩ ሴት ነበርኩ፡፡ ነበርኩ ስል “አሁንስ” አትሉኝም? ቆይ ከዚያ በፊት ልጨርስላችሁ፡፡ ከዚያላችሁ ሰው ሁሉ (ማህበረሰቡ) “ወየውልሽ እንደዚህ ሆነሽ አትዘልቂውም እናም ድምጽሽንም ቀነስ፣ አረማመድሽንም ደርበብ፣ ፍጥነትሽንም ረገብ፣ አይኖችሽንም ሰበር አድርጊው፤ ባልም ቢሆን እኮ እንዲህ እንዳንቺ ቀና ቀና ያለችዋን ይፈራል!” አሉኝ፡፡ ደግሞ እነሱ እንደዚያ ሲሉኝ እውነትነቱን ተቀብዬ(አምኜ አላልኩም) እራሴን እንዴት እንደምቀይር እያውጠነጠንኩ ነበር፡፡
ይህ ችግር ጎልቶ የሚታየው እኛ ማህበረሰብ ውስጥ እንደሆነ ያረጋገጠልኝ አንድ አለም አቀፍ ኮንፈረንስ ተካፍዬ ነበር የዛሬ 20 ዓመት፤ ይቺ ታናሼ የ15 ዓመቷ ጉብል ሳትወለድ፡፡ የአለም አቀፉ ስብሰባ ሙሉ በሙሉ በሴቶች ተዘጋጅቶ ከ2000 በላይ ሴቶች ከየሀገራቱተውጣትተው የተሳተፉበት እጅግ የተቀናጀ ኮንፈረንስ ነበር፡፡ በሀገራችን ትልልቅ ኮንፈረንሶች በአለም አቀፍ ድርጅቶች ወይንም በመንግስት ቢሮዎች ቢዘጋጅም ሴቶች ያዘጋጁት የሴቶችን አጀንዳ ይዞ የቀረበ ኮንፈረንስ ግን ሰምቼም አይቼም አላውቅም ነበረ እና የእውነት በቅናት አነባሁ፡፡ ካነባሁባቸው ምክንያቶች አንዱ ደግሞ በዚያች አንድ ሳምንት ጊዜ አብዛኛው ሴቶች እራሳቸውን ሆነው እውቀታቸውን እና ስሜታቸውን በነጻ መግለጽ መቻላቸው ምን ያህል ከማህበረሰብ ጫና ነጻ እንደሆኑ ያየሁበት ኮንፈረንስ መሆኑ ነው፡፡ እናንተዬ ለካ ባርነት ቀንበር ውስጥ መሆናችንን (አጋነንኩ እንዴ!) ያንን ኮንፈረንስ ብታዩ ታምኑኝ ነበር፡፡
ከኮንፈረንሱ በኋላ የተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ነበርኩ፡፡ እኔ እኔን ሆኜ ሁልጊዜ አፈንጋጭነቴ እየተነገረኝ መቀጠል ወይንስ ያኛው የእኔ አለም ስላይደለ ማህበረሰቡ የሚፈልጋትን ሴት ለመሆን ማስመሰል፤ እንዴት ፈተና መሰላችሁ፡፡ በስራዬ ላይ ጠንካራ መሆኔ፣ በእራሴ ላይ ሳላሰልስ መስራቴ (መማሬ) በኢኮኖሚ እራሴን እንድችል ስላደረገኝ በእሱ በኩል ስጋት አልነበረኝም፡፡ ግን ደግሞ የእድሜ ቆጣሪው እየቆጠረ ሲሄድ “ደፍሮ የሚያገባሽ የለም” የምትለዋ ተደጋጋሚ ንግርት በመጠኑ ትረብሸኝ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን ሰው አይደለምና ጋብቻው ተሳክቷል፡፡ እሱም ቢሆን ሚስት የምትመስል ሚስት ለመሆን ፈተናዬ ቀላል አልነበረም፡፡
ታድያላችሁ ይህቺ የ15 ዓመቷ ጉብል ተፀንሳ ነበር ተወለደች፡፡ በተወለደች በመጀመርያው የሜይ ኮንፈረንስ ዝግጅቷ በጓደኛዬ በሳምራዊት ሞገስ በኩል አገኘኋት፤ ለመዋሀድ ሁለቴ እንኳን አላሰብኩም፡፡ ዘው ብዬ ገባሁ፡፡ ደግሞ ዘው እንድል ያደረገችኝ ጉብሏን ከመሰረቱት አንዷ የሆነችው ናሁሰናይ ግርማ ጭራሽ ከእኔም የባሰች ሆና አገኘኋት፡፡ ትዝ ይለኛል- ከጠዋቱ ክፍለ ጊዜ በኋላ ምሳ ተበልቶ ለሻይ ቡና እረፍት በነበረበት ሰፊ ቦታ ላይ በቡድን በቡድን ትውውቅ እና ጭውውት ላይ እያለን የእኛን ጆሮ (አቴንሽን) ለማግኘት ጠረጴዛ ላይ ዘላ በመውጣት ድምጽዋን ከፍ አድርጋ ለሁላችንም የሚበቃ መልእክት ያስተላለፈችበት አይን ገላጭ ጊዜ(moment):: ታድያ ማህበረሰቡ እኔ ያለሁበት ቀበሌና መ/ቤት ብቻ ነው እንዴ ያልኩበት ቅጽበት ነበር፡፡ በቃ ደስ አለኝ! ለካ ማህበረሰብ ሁልጊዜ ልክ ነው ማለት አይደለም አልኩኝ ለእራሴ፡፡ እናም የበለጠ ይቺን ጉብል ተዋህጄ እራሴን ለማግኘት ያኔውኑ ወስኜ አባል ሆንኩኝ፡፡ የህች ጉብል አስተማሪዬ፣ እራሴን የመሆኔ ሚስጥሬ፣ መካሪዬ፣ አበረታቼ፣ አጋዤ፣ ታናሽ ሆና ታላቄ በመሆን የገራችኝ፣ ብዙ እህቶች እና ጥቂት ወንድሞችን ጭምር ያፈራችልኝ ኤውብ ናት!
በእሷ ያገኘሁትን መዘርዘር ከጀመርኩ ክፍል ሁለት ብዬ ካልጀመርኩ አሰለቻችኋለሁ፡፡ በግርድፉ ግን በመጀመርያ ለአባላት ሁሉ የሚሰጠው የናሁዬ “Self Confidence” ስልጠና ጭንብሌን በደንብ አውልቆልኛል፤ እኔ እኔን ሆኜ እንድቀጥል ጤነኛ ማንነቴን አቆይቶልኛል፡፡ ማህበረሰቡ የማይቀበላት ሳትሆን የሚያከብራት ሴት፡- ሙያተኛ፣ ሚስት፣ እናት፣ እህት፣ እና ጓደኛ ሆኛለሁ፡፡ ለአባላት ከሚሰጡ ጥቅሞች እኔ ከ”ሀ እስከ ፖ” ተጠቅሜአለሁ፡፡ በተጨማሪም የመጀመርያ መጽሐፌን ያሳተምኩት በኤውብ እቁብተኞቼ/ቤተሰቦቼ ነው፣ “ተቀጥሮ መስራት በቃኝ” ብዬ ስወስን በኤውብ የተዋወቅኳቸውን (ኔትወርክ ያደረኳቸው) እንደ ጥሬ ሀብት ቆጥሬ ነው፤ በአብዛኛው የስልጠና እና የማማከር ስራዎቼን የማገኘው ከኤውብ ሰፈር ነው፡፡ “እርቅ ከእራስ” የሚለውን መድረክ ማዘጋጀት ሳስብም ሆነ ስተገብር ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ የኤውብ እህቶቼ እና ቤተሰቦቼ ድጋፍ አለበት፣ በጣም ጥሩ ጥሩ እህቶች አግኝቼበታለሁ፣ እኔም በአባልነቴ መቀበል ብቻ ሳይሆን መስጠትንም ላስተማረችኝ ለዚች ጉብል በሙያዬ በቦርድ አባልነት፣ በስትራተጂክ አመራር፣ በሜንቶርሽፕ እና በስልጠና እንዳገለግላት እድል ስለሰጠችኝ እራሴን ጥግ ድረስ አብቅቼበታለሁ (ጥግ ስላችሁ ያው የእኔ ጥግ ነው)፡፡ ደስ የሚለው ደግሞ ይህንን በምጽፍበት በዚህ ሳምንት የዚች ጉብል 15ኛ ዓመት ልደት እየተከበረ ነው! እንኳን ተወለድሽ እንበላት! እንኳን የጉብል አዋቂ፣ ጠቃሚ፣ መካሪ፣ አስተማሪ፣ ደጋፊ ሆንሽ እንበላት! የእኛዋ እንቁ፣ አንቂ እና አብቂዋ ኤውብ!
የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም
Share to your circles!
Its like you learn my thoughts! You appear to grasp a lot approximately this, like you wrote the guide in it or something.
I believe that you just can do with a few p.c. to pressure the message home a bit, however instead
of that, that is fantastic blog. A fantastic read. I will certainly be back.