አለቃ ወይንስ መሪ?!

Image source: https://dannyspina.com/images/blog/leadership_ego/leadership_meme.webp
አለቃ (Boss) የሚለው አጠራር የሚያስደስታቸው ብዙ ሰዎች እንዳሉ ተረድቻለሁ፡፡ አለቃ እየተባሉ ሰዎችን መጋበዝ፣ በሰዎች መከበብ፣ ተደማጭነት ማግኘት፣ ተከታይ መፍራት፣ አዛዥ ናዛዥ (ናዛዥ ግን ምንድነው!?) መሆን የብዙዎች ሕልም መሆኑን በእለት ከእለት ገጠመኜ ታዝቢያለሁ፡፡ እንዲያውም ከእውነተኛ ስማቸው በላይ አለቃ ወይንም በእንግሊዝ አፍ ቦስ-Boss (ቦስዬ) ሲባሉ የሚኩራሩ ሰዎች በሽበሽ ናቸው፡፡ እኔ በጣም ነው የሚያስቀኝ፡፡ ከባዮቹ ይልቅ የተባዮቹ በአጽንዖ መቀበል ያዝናናኛል፡፡ መዝናናት መብቴ ነው አይደል! ግን ለምን ስለዚህ ነገር ማውራት ፈለግሁ መሰላችሁ፤ ያው አለቃ (ቦስ) ማለት መሪ እንዳልሆነ ለማስታወስ ነው፡፡ እንዴት ካላችሁኝ በምችለው ሁሉ ለማብራራት ዝግጁ ነኝ፡፡
አለቃ ማለት ሰዎችን የሚያስተዳድር ነው፡፡ በቃ ማስተዳደር ማለት በቀላሉ መንዳት እንደማለት ነው፡፡ ለምሳሌ እሱ የሚፈልገው አቅጣጫ ወደፊት ብቻ ከሆነ ሰዎቹ ወደ ግራ፣ ወደቀኝ፣ ወደታች ወይንም ወደላይ እንዲያዩ አይፈቅድም፤ ወደፊት ብቻ! ስራዎች በሰዎች ማሰራት መደበኛ አቋሙ የሆነ ማለት ነው፡፡ እንዲያውም ቴዎዶር ሮስቬልት (የአሜሪካ 26ኛው ፕሬዝደንት) አለቃ (ቦስ) የሚለውን ቃል ከመሪ ጋር አነጻጽሮ “አለቃ የሚነዳ(who drives) መሪ የሚመራ (lead) የሚያደርግ” ይለዋል፡፡ መንዳት ማለት እንግዲህ ለእናንተ አይነገርም፡፡ ለምሳሌ የሚነዳ (አለቃ) መሪውን እራሱ ብቻ ስለያዘው የራሱን ሀሳብ ብቻ የሚያራምድ፣ የራሱን ውሳኔ ብቻ መሬት የሚያወርድ የሌሎችን የሚገድብ ማለት ነው፡፡ መሪ የሆነ ሰው ታድያ ከዚህ የሚለየው መንዳቱ እንዳለ ሆኖ ግን አነዳዱ ሌሎችንም በማነሳሳት፣ አዳዲስ ሀሳቦችን በመፍጠር፣ በማበረታታት፣ እምቅ ችሎታቸውን በማውጣት፣ ሰርቶ በማሰራት፣ ተተኪ በማፍራት፣ ሌላው ቢቀር ማእድ መቋረስ ቢኖር ሰራተኞቹ ወይንም በስሩ ያሉ ሰዎች ሳይበሉ ቀድሞ የማይመገብ ነው፡፡ ልቀጥል!? ያው ታውቁታላችሁ ብዬ ላሳጥረው፡፡ ታድያ የአለቃ (ቦስ) እና መሪ ልዩነት የትዬለሌ አልሆነባችሁም!? “እንክት!” እንዳላችሁኝ በመተማመን ላስኪደው?!
እና ታድያ እኛ እንደ አለመታደል ሆኖ እጅግ ብዙ አለቆች እንጂ ብዙ መሪዎች ያሉን አይመስለኝም፡፡ ተሳስቼ ከሆነ መቼስ እያረማችሁኝ አደራ! እኔ ብዙ መ/ቤቶች ሰርቻለሁ፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከድርጅት መሪዎች ጋር ተገናኝቻለሁ፣ ፖለቲካውንም በቅርበት ሳይሆን በርቀት (በጎሪጥ) አይቼዋለሁ፡፡ እናም የገጠመኝ ይህንን አስብሎኛል፤ አለቃዎች ሞልተው ፈሰውናል፡፡ ደግሞ የሚገርመኝ አለቃ መሆናቸውን እነሱም ተቀብለውታል፤ ያውም በኩራት፡፡ ከነአባባሉ እኮ የአለቃ እና የምንዝር የሚባል አባባል አለን፡፡ አለቃ አለቃ ነው.፤ ነጂ፡፡ ምንዝርስ ምን ማለት ነው? ስረዳው ስርወ ቃሉ ምንዛሪ፣ ዝርዝር፣ የተበተነ፣ ያነሰ አይመስላችሁም!? የሰው ምንዛሪ ወይም ምንዝር ወይም ትንንሽ አለቃ ያልሆነ…እንደማለት፡፡ እንደው ከየት የመጣን ነን ግን!? ለነገሩ አባዊ ስርዓታችን ሴቶችን ብቻ ሳይሆን ሰዎችንም እንዲህ ሲያበላልጥ የኖረ እና እየኖረ ያለ ነው፡፡ ሌላው የድሮ የአድሀሪ፣ የባላባት፣ እና በተቃራኒው የጭሰኛ እና የባርያ ስርዓቶች አሁንም አልተላቀቁንም ማለት እኮ ነው፡፡
አንድ ስማቸውን የማልጠቅሰው (ስላላስፈቀድኩ) ብዙ ኩባንያዎችን የሚያስተዳድሩ የነበሩ መሪ ስለሳቸው አመራር የሚመሰክሩ ተመሪዎቻቸው በአንድ ወቅት ስለሳቸው ሲመሰክሩ በጥሞና አዳመጥኩኝ እና ስለ መሪ እና ስለ አለቃ ሳስብ ሁልጊዜ ከአእምሮዬ አይጠፉም፡፡ ጠቃሚ ነገር ስላለው ጥቂቱን ላጋራችሁ ወደድሁ፡፡ እኚህ መሪ በጠዋት ቢሮ ይገቡና የሰራተኞች መግቢያ ሰዓት ሲደርስ ብዙ ሰራተኞች ከሰርቪስ የሚወርዱበት ቦታ ቆመው እንኳን ደህና መጣችሁ ይሏቸዋል፤ በቃል ሳይሆን ፊት ለፊት በመገኘት፡፡ ጠጋ ብሎ ማማከር የፈለገ ሰራተኛም በዚያው እድሉን ይጠቀምበታል ማለት ነው፡፡ አንድ በሉልኝ፡፡ ሁለተኛ ከከተማ የሚያስወጣ የመስክ ስራ በሚኖር ጊዜ እና ተሸከርካሪዎች ተከታትለው ሰራተኞችን ጭነው በሚጓዙበት ወቅት የመጀመርያውን መኪና እራሳቸው እያሽከረከሩ መንገድ ይመራሉ፤ የሚሆን ነገር ካለ ቀድሞ ለመጋፈጥ፡፡
ሦስተኛ በመስክ መንገዳቸው አንዳንድ ከባድ መኪናዎች ወይም በብልሽት የቆሙ መኪናዎች ለምልክትና ለታኮነት ተጠቅመው ያላነሷቸው ድንጋዮች ካገኙ አሳብረው ከመሄድ ይልቅ ሀዛርድ አብርተው በመቆም ይወርዱና ተከታዮቻቸው መኪኖች እና ሌሎችም መኪኖች እንዳይደናቀፉ ድንጋዮቹን ከመንገድ ይልቅማሉ፤ አራተኛ ምግብ መመገብ አስፈላጊ ሲሆን በቅድምያ ሰራተኞች ሁሉ መብላት መጀመራቸውን ካረጋገጡ በኋላ በአንደኛው ጠረጴዛ ተቀላቅለው ሁሉም የተመገቡትን ይመገባሉ (የተለየ ነገር አያዙም)፣ አምስተኛ ሰውኛ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በሕመም ከስራው የቀረን ሰራተኛ ክትትል ያደርጋሉ፤ ሕመሙ ከፀና ከፖሊሲ ውጪ ወጥተው በልዩነት እንዲታከም ያግዛሉ፣ ሞት ከገጠመ ሰራተኛው ይሁን ቤተሰቡ ቀብር አይቀሩም፡፡ ልቀጥል? እንዳይበዛባችሁ ልቁረጠው፡፡ ታድያ የሚገርማችሁ የሰራተኛ ፍልሰት በእነዚያ እሳቸው ይመሯቸው በነበሩት ኩባንያዎች ስጋት አልነበረም፡፡ 20 ዓመታት የሰሩ ሰራተኞች ማየት ብርቅ አይደለም፡፡ ጥሩ ከፋይም የሚባሉ ኩባንያዎች አልነበሩም፤ መሪው ፍፁም ናቸው እያልኩም አይደለም፤ ፍፁም ሰው የለምና! ግን ጥሩ መሪ ናቸው፡፡ ይሄ ዓይነት መሪነት እዚሁ ሀገራችን አለ ማለት ነው፡፡ እኔ እኚህን መሪ ስላወቅሁ እንጂ ሌሎችም መሰል መሪዎች ቢኖሩም ግን ቁጥራቸው በጣም ትንሽ ስለሆነ ይሄ ብቃታቸው እና ልምምዳቸው ሊዛመት ወይንም ሊስፋፋ አልቻለም፡፡
በተለይ ደግሞ አሁን ወጣት መሪዎች እየበዙ ነውና ለውጥ ማየት ነበረብን፡፡ ግን ወፍ የለም! ካለ ባለማወቄ አፉ በሉኝ፡፡ ከወራት በፊት የገጠመኝን ላውጋችሁ፡፡ አንድ ወጣቶችን ስራ ፈጠራ አስተምራለሁ፣ አነቃለሁ፣ አበቃለሁ ወዘተ የሚል ድርጅት ባዘጋጀው መድረክ የመሳተፍ እድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ እናም ስራ እና ለውጥ የሚፈልገው ወጣቱ ትውልድ የስራ ፈጠራው እድል ተጠቃሚ ለመሆን አዳራሹን ሞልተው የመሪዎቹን (የአለቃዎቹን የሚለው ይመጥነዋል) መምጣት ይጠባበቃሉ፡፡ ልክ አለቃዎች በአጃቢዎቻቸው ታጅበው ሲገቡ አዳራሹ በጭብጨባ እና በአድናቆት ደመቀ፡፡ መቼስ ወጣቶች አርአያ ሲያገኙ እና ሲያደንቁ እንደማየት የሚያስደስት ነገር የለም፡፡ ግን የእራሴን ትዝብት መውሰዴ አልቀረም፡፡ አለቆች (መሪዎች አላልኩም) ከአቀባበሉ ተከትሎ በተዘጋጀላቸው የፊተኛ ወንበሮች እንደተቀመጡ መስተንግዶ (Refreshment) ቀረበ፡፡ ለማን አትሉኝም? ለአለቆች ብቻ! በእርግጥ ያንን ሁሉ ታዳሚ ማስተናገድ ወጪው ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ደግሞ እንደ ሰራተኛ የመስተናገድ መብት ያላቸው ባለድርሻ መሆናቸውን ማንም አልተገነዘበም፡፡ መስተንግዶ አቅም የሚፈትን ከሆነ ደግሞ አለቆቹ አስቀድመው ተስተናግደው ቢመጡስ ምን ነበረበት? እኔ ታድያ በወቅቱ አስብ የነበረው ከላይ የጠቀስኳቸውን፣ ያንን ሁሉ ኩባንያ እና ሰራተኞች እየመሩ አጃቢዎች (security guards) ያልነበሯቸውን አንጋፋ መሪ ነበር፡፡ እኚህ መሪ በአመት አንድ ቀን የቤተሰብ ቀን ብለው ሰራተኞች ቤተሰባቸውን ይዘው እንዲውሉ ሲያደርጉ ከ5000 (አምስት ሺህ በላይ) ሰራተኞቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን አብልተው ሲያበቁ ነበር እሳቸው የሚበሉት፡፡ ልዩነቶች አያችሁልኝ አይደል! በአጠቃላይ ከሌሎችም አገልግሎቶች አንጻር ቅድምያ ለአለቆች መርሆዎቻችን ተነስቼ መሪነት ገና እንዳልዘለቀን ደምድሚያለሁ፡፡ ወደፊትም አይዘልቀንም፤ አለቆች የምቾታቸው ቀጠና እንዲነካ እስካልፈቀዱ፡፡
እንግዲህ እንደ ማጠቃለያ ብዙ ጊዜ የሰራተኛ መረጋጋት (Retention) የብዙ ድርጅቶች ችግር የሆነበትን ምክንያት በዚሁ ማስታወስ ወደድሁ፡፡ ሰራተኞች ክፍያ ብቻ የሚያስሸሻቸው የሚመስላቸው ቀጣሪዎች (አለቆች) ብዙ ናቸው፡፡ ሰራተኞች ጥ ክፍያ ይፈልጋሉ፤ ሐቅ ነው፡፡ ነገር ግን ኩባንያቸውን የሚለቁት ክፍያ ፍለጋ ብቻ ሳይሆን ሰውኛ የሆኑ መሪዎችን ፍለጋ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ አንዳንዴ ከፍትፍቱ ፊቱ ትልቅ መልእክት ነው፡፡ ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም፤ ሰውነቱ እንዲከበርለትም ይፈልጋል፡፡ እናም አለቃ (boss) መሆን ይብቃ! መሪ (leader) መሆንን እንለማመድ! ክፍተቶቻችንን መዝጋት ቢያቅተን እናጥበው! “መ/ቤቴ የእኔ ነው” የሚሉ ሰራተኞች ከሌሉን ድርጅት የትም አይደርስም! ባለኩባንያዎቸ ቆም ብላችሁ አስቡ! ለዛሬ ጨርሻለሁ!
የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም
Share with your circles!