ትዳር ለእሷ እና ለእሱ

ሕይወትን በሁለት ትላልቅ ምእራፎች ከፍለን እንድናወጋ ፈለግሁ እና ይህንን ጽሑፍ ጫር ጫር አደረግሁ፤ የሚመለከተንም የማይመለከተንም ካነበብን በኋላ የእኛ ሕይወት የቱ ጋር እንደሆነ ቆም ብለን እንድናይ ያመላክተናል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሕይወት ከትዳር በፊት በተለይ በእኛ ሀገር በቤተሰብ ቤት ውስጥ ዘና ብለን ያለሀሳብ የምንኖርበት ዘመን ነው፡፡ የቤት ኪራይ፣ ቀለብ፣ ሌሎችም ወጪዎች የግድ አያሳስቡንም፡፡ ይባስ ብሎ የኪስ ገንዘብ ልንደጎምም እንችላለን፤ እንደቤተሰቦቻችን የአቅም (የኑሮ) ደረጃ፡፡ ገቢ የምናመጣም ከሆነ በቤተሰብ (በወላጆች) ተመን ሳይሆን እኛ የፈቀድነውን እንደጉማለን ማለት ነው፡፡ እንዲያውም ወላጆች የራሳቸው የሆነ በቂ መተዳደርያ ካላቸው ከድጎማ ይልቅ ለነገ ብንቋቋምበት ይመክሩናል፡፡ በእርግጥ ይህ ሁሉ ባልተሟላበት ሁኔታ ደግሞ ቤተሰቡን ሙሉ በሙሉ በኢኮኖሚ የመደጎም  ኃላፊነትም ግዴታም ሊኖር ይችላል፡፡  በገንዘብ የማይተመነው እና በአድካሚነቱ የሚታወቀው የቤት ማስተዳደሩ ኃላፊነት ግን አይመለከተንም፤ አቤት ግልግል!

በአብዛኛው ከተማ ውስጥ ተወልደን ያደግን ሰዎች (የገጠሩ ኑሮ በድካም ተጀምሮ በድካም እንደሚጠናቀቅ ልብ ይሏል) እንደዚህ እንኖርና ወደ ትዳር ሕይወት ስንገባ በጣም ፈታኝ ይሆንብናል፡፡ ምክንያቱም ትዳርን አጅበው የሚመጡ ኢኮኖሚያዊ እና አስተዳደራዊ ኩነቶች ከትዳር ውጭ ቆመን ከምናስበው በላይ ናቸውና፡፡ አቅምን እና ትእግስትን የሚፈትኑ መሆናቸውን የሚነግረንም የሚመክረንም የለም፤ ብቻ የቀን መቁጠሪያ እያዩ አግቢ. አግባ የሚለውን ዘልማዳዊ ምክር ከማቀባበል ውጪ፡፡

ዛሬ በዚህ ርእስ ላይ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ከተለያዩ ባለትዳር ሰዎች በተለይ ከሴቶች የምሰማው አቤቱታ ነው፡፡ እኔ የትዳር አማካሪ ባለሙያ አይደለሁም፡፡ ይህንን አሳውቄም “ቢያንስ አዳምጪኝ እና እንደ እኔ ሆነሽ ጉዳዩን አስቢበት እና ምከሪኝ” የሚሉኝ አሉ፡፡ እናም የግዴታ ውዴታ ነው የሚባለው? አዳምጣለሁ ማለት ነው፡፡  ታድያ አዳምጬ ሳበቃ እንዳልኳችሁ ባለሙያ ባለመሆኔ በጉዳዩ ላይ “ይሄ ትክክል ነው ወይንም አይደለም አልያም እንደዚህ ብታደርጉ ያንን ደግሞ ባታደርጉ… ወዘተ” የማለት አቅም በማጣቴ ኮርሱን ወስጄ ሙያተኛ ለመሆን ሁሉ ይዳዳኛል፡፡  መለስ እልና ደግሞ “ግን እኔስ ብሆን ምን አደርጋለሁ?” ብዬ እራሴን በእነሱ ቦታ አስቀምጥና (እራሴው እንዳለሁበት ዘንግቼው) ሳውጠነጥነው ጭራሽ ተጠምጥሞብኝ ቁጭ ይላል፡፡ ግድ የላችሁም በዚህ ዘመን በጣም የሚያስፈልገን ይመስለኛል፤ የትዳር አማካሪ፡፡

እንድ ጥንዶች የገጠማቸውን ላውጋችሁ፡፡ በትዳር ከአስር ዓመት በላይ ቆይተዋል፡፡ ባለሙያዎች እንደሚሉን ደግሞ አንድ ትዳር አስር ዓመት ከተሻገረ በኋላ በጥቃቅን ነገሮች የመፍረስ እድሉ የተመናመነ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ ጥሩ ቁመና ላይ ናቸው ማለት ነው፡፡ ሁለቱም ሀገሪቷ በፈቀደችላቸው ልክ ተምረው በሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ስለዚህም ባል ዳቦ አቅራቢ (Bread winner/provider) ሚስት ተቀባይ እና ተንከባካቢ (Care giver) የሚለውን ልማድ አፍርሰውታል፡፡ በውጭ ሰርተው በሚያገኙት ገቢ በኢኮኖሚ እየተጋገዙ ትዳራቸውን ቀጥ አድርገው አቁመውታል፤ እንደቤታቸው፣ እንደአቅማቸው፡፡ ይህ ሲሆን ግን አሁን ላይ ለጭቅጭቅ የዳረጋቸው የሆነ ሚዛን መዛነፉን ልብ ካለች በኋላ ነው፤ ሚስት፡፡ ሁለቱም ውጭ ከ8-10 ሰዓት ሰርተው ደክመው ከገቡ በኋላ እሷ የቤት አሰተዳደር ሥራ ይጠብቃታል፡፡ ልጆች መንከባከብ፣ ቤቱን ቀጥ አድርጎ ማስተዳደር (የቤቱን ስራ በዝርዝር አናስበው ጃል)! ሞላ ጎደለ ብሎ ማሰቡ፣ ማብቃቃቱ…ወዘተ ሁሁታ ሲያንሰው እኮ ነው፡፡  ለእነዚህ ሁሉ ክፍያ ቢተመንላቸው ስንት ብር ይደርስ ይሆን!? ለዚህ ነው ሚስት በትዳር ሕይወት ውስጥ የሚከወኑ ክዋኔዎች ሚዛን መዛነፍ ከነከናት ያልኩት፡፡ ለነገሩ እኔም ስጽፈው ከነከነኝ፡፡ ሚስትም አይደለሁ!

ታድያ ወደተነሳሁበት ጥንዶች ቤት ልመለስ እና ከሰሞኑ ያጨቃጨቃቸው እና በተለይ ባለቤቷ በጣም የተማረረባት እና ሁለቱም የተበሰጫጩበትን ባወጋችችኝ ልክ በዲያሎግ መልክ እንደወረደ ላቅርብላችሁ፡-

ሚስት፡- ከዚህ በኋላ ከቤት ውጪ የሚፈፀሙ በተለይ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ቢሮዎች ዘንድ በወቅታዊነት (ወራዊ፣ አመታዊ፤ ኳርተራዊ (ካለ)እንደ ውሀ፣ መብራት፣ ግብር እና የመሳሰሉት መክፈል  እና መሰል ጉዳዮች ማስፈፀም ያንተ ድርሻ መሆን አለባቸው፤  ከዚህ በኋላ አንተ ተከታትለህ ማስፈፀም አለብህ! እኔ በዛብኝ!

ባል፡-  ምን ሰርተሸ ነው የሚበዛብሽ! ቆይ እነዚህን ጉዳዮች ማስፈፀም ካቃተሸ ታድያ አንቺ ምን ልትሰሪ ነው!?

ሚስት፡- እኔም እኮ እንዳንተ 24 ሰዓት እኮ ነው ያለኝ! እንዳንተ ውጪ ስሰራ ውዬ ከዚያ መልስ ቤትም ማህበራዊ ጉዳዮችም እኔኑ  ይጠብቁኛል፤ እናም የተደራረበ ስራ እየሰራሁ መሆኑን ላንተ መንገር ለቀባሪው ማርዳት አይሆንም? በቃ ደከመኝ!

ባል፡- ጭራሽ የቤቱን ስራ ከቁጥር ውስጥ ታስገቢዋለሽ! ማን ሊሰራልሽ ኖሯል…ዛሬ የሚደክምሽ ከየት የመጣ ነው!(ቁጣውን ቀጠለ! ቤቱ በሁለቱ ጭቅጭቅ ደመቀ…!)

ስራዋን መናቁ፣ የቤቱን ማስተዳደር ኃላፊነትን ከቁብ ያለመቁጠሩ ብቻ በአጠቃላይ ሁኔታው ” ለካስ ይሄንን ሁሉ አመት አንተዋወቅም!?” የሚል አስተሳሰብ ላይ እንድትደርስ ዳረጋት፡፡ እኔም እሷን ብሆን ይዳርገኛል፡፡ በአንድ በኩል ደግሞ ለጭቅጭቅና ለኩርፍያ የሚያበቃ ነወይ ብዬም አሰብኩ፤ ቁጭ ብሎ መነጋገር ሲቻል፡፡  በእርግጥ አስር ዓመት የቆየ ትዳር በዚህ ይፈርሳል ማለት ባይሆንም ሌሎች ነገሮች በተከሰቱ ቁጥር እንዲህ ያሉ ጥቃቅን እና አነስተኛ ክርክሮች ትንሽ እርሾ ብዙ ሊጥ ኩፍ እንደምታደርገው ፀብ አኮፍኳፊ እንደማይሆኑ ምን መተማመኛ አለ? ምንም!  እኔ ግን ወደ እራሴ ትዳር እንድመለከት እና “ትዳር ለእሷ እና ትዳር ለእሱ” ብዬ ዳግም እንድጽፍ እድል የሰጠኝ ገጠመኝ ነው፡፡  ዳግም ያልኩት በትዳር ጉዳይ ከዚህ በፊትም ብሎግ ስለጻፍኩ ነው፡፡ 

ትዳር የሁለት ሰዎች ጥምረት ሆኖ ሳለ ሸክሙ ግን አንዳቸው ላይ ያጋደለ ነው፤ እንደትዳሩ ዓይነት፡፡ እይታችንን በኢኮኖሚ እና በአስተዳደር ከፋፍለን እናድርገው እና እንየው፡፡ ውጪ ሰርተው ገቢ የማያመጡ ሚስቶች ባሉበት ትዳር ውስጥ የኢኮኖሚው ጫና በባልየው ጫንቃ ላይ ሙሉ በሙሉ የተጣለ ነው፡፡ ኢኮኖሚው ከሌለ አስተዳደሩም አይኖርምና እሱ ይባዝናል ቤቱን ለመሙላት፡፡ የእሱ ገቢ ከሌለ ትዳሩ ይናጋል! በእርግጥ ውጭ የማይሰሩ ሚስቶች ስራ የላቸውም ማለት እንዳልሆነ በተለያዩ መድረኮች እና ፊልሞች ተምረናል፤ በገሀድም አይተናል፡፡ የቤት ውስጥ አስተዳደር እራሱን የቻለ ትልቅ ስራ በመሆኑ ኢኮኖሚ ብቻውን ትዳሩን አያቆመውምና፡፡

 ይህ በእንዲህ እንዳለ ውጪ ሰርታ በኢኮኖሚ ጫናውን የምትሸከም ወይንም የምትጋራ፣ በቤት ውስጥ ያለው አስተዳደራዊ ኃላፊነት የምትወጣውን ባለድርብርብ ጫና የሆነችውን ግን ወጣ ስትል ድምቅምቅ ብላ የምትታየውን ሴት ማንም አላያት፡፡ ማንም  የማያዝንላትና የማይሸልማት፤ በቃ ሕይወቷ ግን ባለድርብርብ ጫና ነው! አራት ነጥብ! እናም ያቺን ምክር ፈላጊዋን ሴት “እውነት ነው ድርብርብ ጫና አለብሽ፤ ይህንን አሳምኝው እና የውጭውን ጉዳይ የማስፈፀም ኃላፊነት ይረከብሽ፣ አንቺም ለትዳርሽ በኢኮኖሚ እና በቤት አስተዳዳሪነትሽ ግፊበት፣ ግን ደግሞ እራስሽንም እየጠበቅሽ፣ ምክንያቱም ለራስሽም፣ ለእሱም፣ ለመላው ቤተሰብሽም ታስፈልጊያለሽና…ወዘተ” ብዬ እንደምን ልምከራት! የትዳር አማካሪ ባለሙያ አይደለሁማ! ደግሞስ ጠንቋይ ለራሱ መች ያውቅና! ለዛሬ ጨርሻለሁ!

የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top