በየዓመቱ ማግባት!

ዘመን በተቀየረ ቁጥር አዲስ ዓመትን ተከትሎ ብዙዎቻችን “ይሄን አዲስ ዓመት በአዲስ ጉልበት እና እቅድ ነው የምኖረው፤ እስካሁን ያላሳካሀሁትን ሁሉ ነው የማሳካው…ወዘተ እንላለን፡፡ የዘንድሮ ዘመን እንደሆነ ገባ ብለን ሳንጨርስ አልቆ ቁጭ ነው የሚለው፡፡ ቆይ የድሮ አመት 365/6 ቀናት ነበሩ አይደል!? አሁንም ግን ያው ነው ወይንስ ተኝተን ስንነቃ የሚሰርቀን የማናውቀው መንፈስ አለ!? ይሄ ጥያቄ የሁላችንም ስለሚመስለኝ እና መልሱን ማናችንም ስለማናውቀው እዘለዋለሁ፡፡ ደስ የሚለው ግን እኛ በተለይ የሁለት አዲስ ዓመት ባለፀጎች ስለሆንን መጀመርያ መስከረም ሲጠባ በእራሳችን ዓመት ብዙ እቅዶች እና ግቦች እናስቀምጥና አንድ አራተኛውን በጥቂት ወይንም በምንም ስኬት ላፍ አድርገን ከኖርን በኋላ እራሳችንን ለማጽናናት በእነሱ አዲስ አመት በእኛ የአራተኛ ወር መገባደጃ ላይ ቆመን እንደገና እናቅዳለን ወይንም ያንኑ እንከልሳለን፤ የእቅድ እና የግብ (goal) መዓት እንመዘግባለን አንድም በወረቀት አልያም በአእምሯችን ተማምነን፡፡
አንዳንድ ሰዎች ግን “እቅድ ምን ያደርጋል ዝም ብሎ ያለጭንቀት ተረጋግቶ እንደአመጣጡ መኖር ሲቻል!” የሚሉም አሉ፤ አመጣጡ ግን ከየት ይሁን ከወዴት እርግጠኛ ባይሆኑም፡፡ እነሱም ግን ያው በመረጡት ልክ ያለእቅድ እና ያለግብ ከመኖር ጋር ተስማምተው ይኖራሉ፡፡ በመረጡት መኖር ጥሩ ነው፤ ምርጫችን ምን ያህል አዋጭ ነው የሚለው ስሌት ውስጥ ሳንገባ ነው ታድያ፡፡ እኔ እራሴ በእኛ ዘመን መለወጫ አቅዳለሁ፣ ግብ አስቀምጣለሁ፣ አመቱ ሲያልቅ ግን በድንጋጤ ክው እላለሁ፤ የማይበጀን ክው ይበልና፡፡ ምክንያቱም ካቀድኩት በላይ ያላቀድኳቸው ብዙ ስራዎችን የሰራሁ ቢሆንም ያቀድኳቸው እያፈጠጡ ስለሚያዩኝ እና ስለሚያሳቅቁኝ፡፡
አንዲት ወዳጅ አለችኝ፡፡ በየዓመቱ ታቅዳለች፤ በጀት ሳይቀር ትበጅታለች፤ በጀቷ ደግሞ የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የጊዜ፣ የሰውና የመሳሰሉትን ያካትታል፤ ከዚያም ባስቀመጠችው ልክ ትተገብራለች፡፡ ባልተሳካላት ነገር በመሞከሯ ብቻ ለእራሷ ታጨበጭባለች፡፡ በቃ ምን ልበላችሁ ጥንቅቅ ያለች ናት፡፡ እርግጥ አንዳንዴ በመስመር ብቻ ከመኖሯ ብዛት ከእቅዷ ውጪ የሚመጡ እድሎችን አታስተናግድም እና የዚህኛውን አካሄድ እኔ በልቤ ደካማ ጎኗ እለዋለሁ፤ መቼስ ሰዎች ሆነን ደካማ ጎን ከሌለንማ የሆነ የጎደለን ነገር አለ ማለት ነው፤ እንደዚያ በሉት፡፡ በየዓመቱ ማግባት የሚለውን ርእስ ስታዩ “ምንኛ መታደል ነው በየዓመቱ ማግባት!” ያላችሁ ትኖሩ ይሆን!? ወይንስ “አበስኩ ገበርኩ በየዓመቱ ማግባት ነውርም አይደል! መቼ አግብቶና ኖሮ ከዚያ ተፋቶ ነው እንደገና ወስውሶ ወይንም ተወስውሶ ድጋሚ ማግባት የሚቻለው?”አላችሁ? ከምር ግን በየዓመቱ ማግባት ምን ገጽታ ይኖረው ይሆን!? ነገሩ አንዳንድ የዚህ ችሎታ ያላቸውን ደፋሮች የምታስተዳድር አለም ነው ያለችን እኮ፤ አራርቀው የሚያገቡ፡፡ ይሄ ለወንዶች ቀለል የሚል ይመስለኛል፤ ስለማያረግዙ እና ስለማይወልዱ ማለቴ ማስረገዝ እና ማስወለዳቸው እነሱ ካልነገሩን እንደ እኛ ሴቶች ስለማይናገርባቸው ወይንም ስለማይናገርላቸው፡፡ ሰሞኑን እንዲያውም በማህበራዊ ሚዲያ የሚቀርቡ ሴቶች እሮሮ ይሄን መሰል ነው፡፡ “ሚስት እንዳለው ደብቆ ካገባኝ እና ካስረገዘኝ በኋላ ወደሚስቱ ተመለሰ፣ እኔን በሕግ አግብቶ ልጆች ከወለድን በኋላ ከቤት ጠፋ እና ሌላ ከተማ/ሀገር ሄዶ ሌላ ሚስት አገባ፣ …ወዘተ፡፡ ስለዚህ ለእንደዚህ ያሉ ሰዎች በየዓመቱ ማግባት ተችሏል ማለት ነው፡፡ እነሱ ስራቸው ያውጣቸው፤ እኔ ያልኩት ማግባት ግን ሌላ ነው እና እንዳትፈርጁኝ፡፡
በየዓመቱ ማግባት ያልኩት ከላይ እንደጠቀስኳት ወዳጄ በየዓመቱ ቀምሮ እቅድ በማውጣት፣ ጊዜን፣ ሀብትን፣ አቅምን እና አቋምን በመበጀት፣ ትኩረት በማድረግ፣ ዲስፕሊን በተሞላበት ሁኔታ በመተግበር በየዓመቱ ግብ/ጎል ማግባት ለማለት ነው፡፡ ለካ ግብ ማግባት ልክ ባል/ሚስት የማግባት አይነት ትርጉም አለው! እና ይህቺ ወዳጄ በየዓመቱ እቅዷን እና ግቧን ስለምታጋራኝ ጥሩ ተምሳሌት ሆናኛለች፡፡ እኔ ከመነሻዬ እንደነገርኳችሁ የማቀድ ችግር የለብኝም፡፡ ነገር ግን እቅዴን ከግብ ለማድረስ በምውተረተርባቸው መንገዶቼ አንድም የሌሎች ሰዎች እቅዶች ጣልቃ ይገቡብኛል አልያም ካቀድኩት የተሻለ የምለው የሚተገበር ነገር ይገጥመኝና ሙሉ በሙሉ እወሰዳለሁ፡፡ ስለዚህም በዓመት አንዴ ከሚያገቡት ማለቴ ግብ ከሚያገቡ የመስመር ሰዎች አንዷ አይደለሁም ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ዝም ብዬ በተቀደደበት እፈሳለሁ ማለትም አይደለም፡፡ “እሱ ደግሞ ምን ማለት ነው?” ካላችሁኝ የብዙ ሰዎችን ስብእና ቃኘት ቃኘት እንዳደርግ ግድ ይለኛል፡፡
በጓደኝነትም፣ በአብሮ መስራትም ብቻ በተለያዩ ማህበራዊና ሙያዊ ሕይወታችን የሚያጋጥሙን ሰዎች የየእራሳቸው ቀለም አላቸውም አይደል! እና ብዙ ጊዜ ምን አስተውያለሁ መሰላችሁ አንዳንዶች ወደግባቸው ሲንደረደሩ ሌሎች ደግሞ አጃቢ ሆነው የሚኳትኑ ብዙ ገጥመውኛል፡፡ አብሮ በመሄድ፣ አብሮ በማሳለፍ ጓደኝነትና ወዳጅነት ይጠነክር የለ! ግን ደግሞ እንደእነዚህ ያሉ ሰዎች ጠዋት ተነስተው ስራ ወይንም ትምህርት ከሌላቸው የወዳጅ ጓደኛ ስልክ ጥሪ ነው የሚጠብቁት፤ እንዲያውም ካልተደወለላቸው እራሳቸው ሊደውሉ ይችላሉ፡፡ ከዚያ የት ነሽ/ህ ሲባሉ የትም ብለው ወደተጠሩበት ሄደው ቀናቸውን በአጃቢነት ያሳልፉታል፡፡ ይሄ ባህርያቸው ትናንትም እንደዚያ ነበር፤ ዘንድሮም የቀጠል ለከርሞም የማይቀየር፡፡ እነዚህን ዓይነት ብዙ ሰዎች አውቃለሁ፤ በተቀደደበት የሚፈሱ ያልኳችሁም እነሱን ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች እድሜአቸውን ቀብድ አስይዘው የሚኖሩ ሳይሆኑ የሚያኗኑሩ ምስኪኖች ናቸው፡፡ እንኳን በአመት ሊያገቡ ግብ እራሱ ምን እንደሆነ አይተውም ሰምተውም ሰርተውም የማያውቁ ይመስለኛል፡፡ ታድያ ከዚህኞቹም መሀከል መሆን ጸጋ አይመስለኝም፡፡ እንግዲህ ሳይንሱም የሚነግረን በአመት ማቀድ እና ግብ ማግባት ጤናማ አካሄድ እንደሆነ ነው፡፡ የትኛው ሳይንስ እንዳትሉኝ ደግሞ፡፡ የእቅድ እና ግብ የአንድ ሳይንስ ውጤት ሳይሆን የ psychology, neuroscience, behavioral economics እና ሌሎችም ጥምረት ውጤት ነው ይሉናል ሳይንቲስቶች፡፡ ላስቻለው ሰው እቅድ መልካም ነገር ነው፡፡ ይህ ማለት ግን “እቅዴ አይደለም” በሚል የዋህ ምክንያት ፊትለፊት የሚመጣን ተግባር አለመፈጸም አዋቂነት አይመስለኝም (ለእኔ)፡፡ የጽሑፌን ጭብጥ ጠቅለል ሳደርገው በአመት ማግባት ከጉዳቱ ጥቅሙ ይበልጣልና አቅደን ግባችንን እናግባ የሚል ይሆናል፡፡ “በየአመቱ አቅዳለሁ ግን አንዱንም አላሳካውም ስለዚህም ምን አደከመኝ!?” የምንል ሰዎች ካለን ሳይንሱ ምን ይላል መሰላችሁ “እቅድ ከሌላችሁ የሌሎች እቅድ ውስጥ ትሸጎራላችሁ” ብሎ እቅጩን ይነግረናል፡፡ መሸጎር በእንግሊዝኛ ምንድነው እንዳትሉኝ፤ የመቀርቀር (ቀ-ትጠብቃለች) አቻ ትርጉም ነው፡፡ ስለማግባት ማለቴ ስለግብ ደግሞ ሲነግረን “እቅድ የሌለው ግብ ምኞት ነው!” ይለናል፤ ሳይንሱ ነው ያለን፡፡ እና ምን ለማለት ነው በአመት አቅዶ ማግባት ትክክለኛው የስኬት መንገድ ነው! መልካም አቅዶ ማግባት! ለዛሬ ጨርሻለሁ!
የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም
Share to your circles!
“በየዓመቱ ማግባት” እና የ2026 ሁለተኛ ዕድላችን 💍⚽️
ሰላም የAWIB ቤተሰቦች! ወዳጄ ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪዳነማርያም ያሰፈረችው ሃሳብ ልክ እኔም አስቤው ከነበረው ሃሳብ ጋር በእጅና በጓንት ተገጥሟል።
ፍጹም በጽሁፏ “በየዓመቱ ማግባት” ስትል—ልክ እንደ ትዳር ጥንቅቅ ባለ ዝግጅት፣ በበጀት እና በዲስፕሊን “ግብ ማግባት” (Goal Scoring) ላይ ማተኮር እንዳለብን ትመክረናለች። በተለይ እኛ የሁለት አዲስ ዓመት ባለፀጎች በመሆናችን፣ የመስከረሙ እቅዳችን “ላፍ” ካለብን፣ ይሄኛው የ2026 መጀመሪያ የከሸፈውን ለመጠገን ወይም አዲስ ግብ ለማግባት ለሁላችንም ትልቅ አጋጣሚ ነው።
እሷ እንዳለችው፦ “እቅድ ከሌላችሁ የሌሎች እቅድ ውስጥ ትሸጎራላችሁ (ትቀረቀራላችሁ)”። እውነት ነው! የሌሎች አጃቢ ከመሆን ወጥተን የራሳችንን ግብ የምናገባበት ጊዜ አሁን ነው።
እኔም ይህንኑ እያሰብኩ ሳለ፣ ሁላችንም ይህንን “ግብ የማግባት” ጉዞ እንዴት እንጀምር ለሚለው 3 ቀላል እርምጃዎችን አዘጋጅቻለሁ። ኑ አብረን እንለማመደው፦
1️⃣ እንቅፋቶቻችሁን ለዩ፦ ግብ እንዳታገቡ የሚከለክሏችሁ፣ ጊዜያችሁን የሚሰርቁ አላስፈላጊ ልምዶች ምንድን ናቸው? 2️⃣ ሰኔ 2018 (Gregorian 2026) እራሳችሁን ተመልከቱ፦ ያኔ ምን ዓይነት ስኬት አግብታችኋል? ኑሯችሁስ ምን ይመስላል?
3️⃣ አዳዲስ ልምዶች፦ ያንን ግብ ለማግባት ዛሬውኑ ምን 3 አዳዲስ “የጨዋታ ስልቶችን” (ልምዶችን) መጀመር አለባችሁ?
የእኔ ቁርጠኝነት ለዚህ ሳምንት፦ ፍጹም እንዳለችው በመስመር ለመጓዝ እና ግብ ለማግባት፣ እኔ በዚህ ሳምንት፦
1. ከምሽቱ 3:30 በኋላ ስልኬን አርቃለሁ።
2. ጠዋት ለ20 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አደርጋለሁ።
3. በዋና ስራዬ መሃል ለ45 ደቂቃ የጀምርኩት ፕሮጀችት ፕላን ላይ አተኩራለሁ።
Thank you Fetsè!