እናጣራ!

የመጪውን የኢትዮጵያ 2018 ዓ.ም. በትዳር ለመጀመር የአቀዱ ተጣናጆች ሰሞኑን ሽምግልና እየላኩ ነው፡፡ ትዳር ደግሞ ታቅዶ ሲጀመር ፍጻሜው ያማረ ይሆናል አይባልም ለካ፤ ምክንያቱም ትዳር የ80 ዓመት ውል ስለሆነ ቀድመን የምንፈጸመው እኛ ስለሆንን (መሰለኝ)! ዋናው ቁምነገር የታቀደ ነገር ካልታቀደ እና ከግብታዊ ውሳኔ በብዘ እጥፍ ይሻላል፡፡ ታድያ ስናቅድ በጀት ነክ ነገሮችን እንደ ሰርግ፣ የቤት ኪራይ፣ የልጆች ብዛት፣ የቤት ቁሳቁስ ወዘተ ብቻ አይደለም ማቀድ ያለብን፤ ብዙ ከእቅድ ጋር ተጓዳኝ ይሁኑ አይሁኑ ባይታወቅም ብቻ መጠናት ወይንም መጤን ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡

ሰሞኑን የገጠመኝን ላጋራችሁ እና ምን አይነት ቅድመ ሁኔታ ማድረግ እንደሚገባን አብረን እናስብበታለን፡፡ ወጣቷ ልጅት ከወደደችው እና ከወደዳት ፍቅረኛዋ ጋር ትዳር ለመመስረት ይወስናሉ፤ ደስ ይላል! አብረው በፍቅር ጓደኝነት የቆዩት ሁለት ዓመታት ሊሞሉት ጥቂት ወራት የቀሩት ቢሆንም ግልጽነት የተሞላው ቅርርባቸው (እሷ እንደነገረችኝ) ከኋላቸው ምንም ዓይነት ነገር ይከሰታል ብለው አልጠበቁም፡፡ ለነገሩ ላደለው በወራት ትውውቅ አልያም ያለትውውቅ ጋብቻ ይደረግስ የለ!? ላደለው አልኩ እንዴ የእኔ ነገር፤ መታደል ይሁን አይሁን ባለቤቶቹ ብቻ ናቸው እኮ የሚያውቁት እና ምን ነክቶኝ ነው!? ወደ ልጅት ወግ ልውሰዳችሁ! እናም ለቤተሰቦቿ አሳውቃ የሽምግልና ቀን ይቆረጣል፡፡ ያው ሁላችንም የምናውቀው አንድ እውነት አለ፡፡ ሽምግልና ባህል እና ወግ እንጂ በድሮ ቅርጹ እንዳልሆነ የምናየው እውነት ነው፡፡ እንዲያውም አሁንማ ሽምግልና ላኪው በጋሪ የሚገፋ አበባ እና ውስኪ በማምጣት ሀብቱን ሲያሳይ ሽምግልና ተቀባይ ደግሞ ቤተሰቡ ያለውን አቅም ለማሳየት ኃይለኛ ድግስ ደግሶ የሚጋብዝነት ነው፤ እሰይ እንኳን ለአቅመ አቅም ደረሱ!

ሌላው ቀደም ሲል ሽምግልና ላይ ሙሽሪት እና ሙሽራው ባይተዋር ሆነው በኋላ ነው ሪፖርቱን በቪዲዮ የሚኮመኩሙት፤ እሱም እየቀረ ነው መሰለኝ ሽማግሌዎቹ በሁለት ተከፍለው ወደሙሽሪት ቤተሰቦች ይሄዳሉ፡፡ የመጀመርያው የሽምግልና ቡድን የመጡበትን እንደወጉ አስረድተው ልጃቸው ሙሽሪትን የማስተዳደር አቅም እንዳለው የሀብት ቁመናውን ዘርዝረው እሺታን ያገኛሉ፡፡ ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ሙሽራው ያለበት ይሆንና ምሳ የሚጋበዙበት የሚደሳሰቱበት ፕግራም ላይ የሚቀላቀል ይሆናል ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ሽምግልና ላይ የልጁ አባትም አብረው መጥተው አይቻለሁ፡፡ ይሄ ሁሉ ክፋት የለውም፤ ዝምድናውን ያፋጥነው እንደሆነ እንጂ፡፡ ታድያላችሁ የልጅት ጠያቂ ሽማግሌዎች እሽታ ካገኙ በኋላ በሁለተኛው ዙር የልጅት እጮኛ በጥቂት ሰዎች ታጅቦ የእሷን ቤተሰብ በአክብሮት ሰላምታ ሰጥተው ተቀላቀሉ፡፡ የዚህን ጊዜ የልጅት አክስት (የአባቷ እህት) ሁኔታዋ ሁሉ ተቀያየረ፤ ከተቀመጠችበትም በመነሳት መታጠብያ ቤት ገብታ ቀረች፡፡ ግራ የተጋባች የልጅት እናት ሁኔታውን መከታተል ጀመረች፤ እናቶች ንቁ አይደሉ!?

ለካ የልጅት እጮኛ ከአክስት ጋር ይተዋወቃሉ፤ መተዋወቅ ስላችሁ ቀላል መተዋወቅ እንዳይመስላችሁ፤ የቀድሞ እጮኛዋ ነበር፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ከጋብቻ በፊት በነበራቸው ጾታዊ ግንኙነት በማርገዟ “ኃላፊነት አልወስድም ብትፈልጊ አስወርጂው ብትፈልጊ ወልደሽ ጣይው ነገር ግን ወልደሽ ማሳደግ ከሆነ ምርጫሽ በእኔ ስም ማስጠራት አትችይም” በማለት ለሕይወቷ በሚያሰጋት ሁኔታ ክዷት ልጁ ተወልዶ፣ በቅዱስ ሚካኤል ቀን ክርስትና አስነስታው ስታበቃ የአባቱ ስም ሚካኤል በማለት በነጠላ እናትነት ያለአባት የምታሳድገው የእሱ ልጅ አላት፡፡ “አባቱ ማነው?” ለሚለው አታካች ጥያቄ “ክዶኝ ጠፍቷል” እያለች እየተንገበገበች ባለችበት ሁኔታ ዛሬ ወጣቷን የወንድሟን ልጅ በክብር ለማግባት በደመቀው ሽምግልና ጋሪ ሙሉ አበባ ከውስኪ ጋር ልኮ ቤታቸውን የሞላው ሰውዬ እሱ የልጇ አባት ነው፡፡ እና ይሄንን ምስጢር እንዴት ትንገራቸው!? አክስት ናትና የልጅት ወግ ማእረግ እንዲበላሽ አልፈለገችም፤ ለእናትየውም ምንም ሳትተነፍስ ያችን ቀን ከማሳለፍ ውጪ ምንም አላደረገችም፡፡

እናት ግን ሴት ናትና የአክስትየውን ሁኔታ በቸልታ ማለፍ አልፈለገችም፡፡ ለታጨችው ልጇ አክስቷ ስለእጮኛዋ የምታውቀው ነገር ያለ መሆኑን የተጠራጠረች መሆኑን ከነገረቻት በኋላ ከቤት ወጣ ብለው እንዲጨዋወቱ ትመክራታለች፡፡ አክስት ከሙሽሪት በእድሜ ከፍ ያለች ብትሆንም ስለሚቀራረቡ ብዙ ምስጢር ይጨዋወቱ ስለነበር ይህንን ማድረግ ለሙሽሪት አልከበዳትም፤ ምንም እንኳን እንደዚህ የገዘፈ መርዶ የጠበቀች ባይሆንም፡፡ አክስት ልጅትን ቤተክርስትያን ወስዳ የምትነግራትን ምስጢር ለእናቷም ሆነ ለአባቷ እንዳትናገር በማስማል ሁሉን ነገር ትነግራታለች፡፡ ልጅትን አያድርጋችሁ፤ እንደነገረችኝ ከሆነ እራሷን አልሳተችም እንጂ የስሜት መደበላለቋ መላ ሰውነቷን በክሎት መራመድም ሆነ መጮህ አቅቷት ለሰዓታት በድን እንደሆነች ነበር የነገረችኝ፡፡ ከተዘበራረቀው ስሜቷ ከወጣች በኋላ ግን ውሳኔዋ ምን መሆን እንዳለበት የታላላቆች ምክር ፈልጋ ነበር ወደ እኔ የመጣችው፡፡ ግራ የገባ ነገር ሆነብኝ፡፡ የልብወለድ ታሪክም መሰለኝ፡፡ የአክስቷ ወሬ ምን ያህል ትክክልነት እንዳለው የምታውቀው አክስትየው ብቻ ናት፤ ለእናት እና ለአባቷ እንዳትነግር ከተቻለም እራሷም ተረጋግታ ሰርጉ ቢከናወን እንደሚሻል የአክስትየው ምክርም ታክሎበታል፡፡ ለወጣቷ ለባለራእይዋ ሴት መምከር ከባድ ቢሆንብኝም ትዳሩን ደጋፊ መሆን አቃተኝ፡፡ ነገ እሷ የምትወልዳቸው ልጆች የአክስቷ ልጅ ወንድምና እህቶች መሆናቸውን ሳስበው ሸከከኝ፡፡

የሜንቶርነት ጉዞዬ ካሳየኝ የከፋ የሕይወት ልምድ እና ተሞክሮ ማማከር ይህንን የሚወዳደረው የለም፡፡ ወጣቷም ፈርጠም ብላ የጠየቀችኝ “አንቺ ብትሆኚ ምን ታደርጊያለሽ?” ነበር፡፡ አንዳንዴ ያልደረሰባችሁ ነገር ላይ ምክር መሰንዘር ቡጢ ከመሰንዘር አይተናነስም፡፡ ጊዜ እንድትሰጠኝ ከጠየቅኳት በኋላ ውዬ አድሬ የመጣልኝ ምክር ሁኔታውን አሳውቃው (አክስትየው እውነተኛ ብትሆን እንኳን ያው መካዱ ስለማይቀር) ለጋብቻ የተቆረጠውን የሦስት ወር እድሜ ላልተወሰነ ጊዜ አራዝሞ የሕጻኑን እና የእጮኛዋን አባትና ልጅነት ለማጣራት ዲኤንኤ ማስመርመር ከውጤቱ በኋላ ውሳኔው ያንቺ እና የእሱ ይሁን የሚል ነበር፡፡ ታሪኩን እዚህ ላይ ልቋጨው እና ለወጣቶች እና ለነጠላ እናቶች የምላችሁ ነገር ቢኖር ይሄ ነገር በእናንተስ እንደማይደርስ በምን ታውቃላችሁ? በምንም? ታድያ ምን ብናደርግ ጥሩ ነው?

ሳጠቃልለው ብዙ ጊዜ የእጮኝነት ዘመን ድብቅ ነው፤ ምክንያቱም መጨረሻው ስለማይታወቅ፡፡ ነገር ግን አያያዙ ጥሩ ሆኖ ወደ ሽምግልና እና ጋብቻ ሲንደረደር ብዙ ነገሮችን በግልጽነት መወያየት ከዚያም ባለፈ ማጣራት ጥሩ ነው፡፡ የሚሰራበትን መ/ቤት/ቢዝነስ እንኳን ሳታውቁ የምትጋቡ ሴቶች እንዳላችሁ ይታወቃል ይቅርና የቤተሰቡን ሁኔታ፡፡ ለዚህም እኮ ነው የቀድሞ ሚስቶቻቸውን እና ልጆቻቸውን አስቀምጠው እዚህ ሰፈር ደግሞ በሰርግ የሚያገቡ ወንዶች ታሪክ የምንሰማው፡፡ የሴት ልጅ ሕይወት ጥንቃቄ ይፈልጋል፤ (የወንድ ሕይወት አይፈልግም እያልኩ አይደለም!) እናም የኋላ ኋላ “ድስት ጥዶ ማልቀስ” ከሚሆን ከእራሱ አንደበት በተጨማሪ ከመ/ቤቱ፣ ከሚኖርበት አካባቢ፣ ቢቻል ከጓደኞቹ ሳይቀር የቀድሞ ማንነቱን ማጣራት ይበጃል፡፡ የቀደመ ትዳር ከነበረው ከማን ጋር እንደሆነ እና ልጅ/ልጆች ካሉትም ተናግሮ የሚመጣ እውነተኛ ወንድ ካፈቀርሽው እና ካፈቀረሽ ገደብሽን (boundary) እንደሚጠብቅልሽ ከተማመናችሁ እሰየው! ሽማግሌዎችም ማስተዳደር መቻሉን የምትጠይቁትን ያህል ያለፈ ታሪኩን ማለትም ከዚህ ቀደም ማግባቱ፣ ልጆች ወልዶ ከሆነ እና ኃላፊነት ወይንም ተጠያቂነት ያለበት መሆኑን መጠየቅ አትዘንጉ፡፡ መጠየቅ እና ማጣራት የተጋቢዋ ኃላፊነት ነው ብላችሁ አትለፉት! አብረን እ-ና-ጣ-ራ!!! መጪውን ዘመን በእውነተኝነት ላይ የተመሰረተ ትዳር የሚመሰረትበት ያድርግልን! ለዛሬ ጨርሻለሁ!    

 የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Share to your circles!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top