ሽፍንፍን!

Image Source: A Student News Magazine for UW Tacoma
እንደ ሀገር ብዙ ጥሩ ጥሩ የሆኑ ባህሎች እና ትውፊቶች ያሉን ዜጎች ነን፡፡ እንደ ሰው የምንረዳዳባቸው የምንደጋገፍባቸው አበረታች የሆኑ እሴቶቻችን የትዬለሌ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ኑሮ ቢከፋ (ቢወደድብን) “ከእኔ ችግር የእነሱ ይብሳል” ብሎ የተቸገሩትን የሚዳብሱ እና የሚያጎርሱ ዜጎች ያለባት ሀገር ናት፣ ኢትዮጵያ፡፡ ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ ብዙ ነገሮች ሲገጥሙን ተስፋችንን የሚያለመልሙ እነዚህ ሰዎች ምስጋና ይግባቸው፡፡ ይሄ ባህላችን (ልበለው?) የጨካኞችን ቁጥር በድብ የቀነሰልን ይመስለኛል፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ወጥተን መግባት እንኳን አሳሳቢ በሆነ ነበር ምክንያቱም የሚረዱ (የሚለግሱ) እጆችን ጠብቀው የሚያድሩ ወገኖች “ደጋፊ ወገን አለን” ብለው ተስፋ ባያገኙ አስገድዶ መቀማትና ዝርፍያ ከፍተኛ ይሆን ነበር፡፡ ይህ ድርጊት የለም እያልኩ አይደለም፤ ቢኖርም በችግራችን ልክ ላለመግዘፉ የመደጋገፍ ባህላችን እና እንዲሁም እምነታችን አግዞናል ባይ ነኝ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን እድለኛ ያልሆንንባቸው በሽፍንፍን ያሉ ጉዳዮቻችንም ቀላል አይደሉም፡፡
ብዙ ነገሮች ተሸፋፍነው የሚኖሩባት ዓለም ላይ ነው የምንኖረው፡፡ በተለይ የሴቶች እና የሕጻናት ጉዳይ እጅግ ተሸፋፍኗል፡፡ ሰሞኑን የሕጻን ሄቨን ተደፍሮ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል ብዙዎችን አስለቅሷል፤ አሳዝኗልም፡፡ ይህም ድርጊት ምክንያት ሆኖ ብዙሀን ሴቶችም ወንዶችም ድምጻቸውን እያሰሙ ነው፡፡ እንደዚህ ያለ አሰቃቂ ወንጀል ተሰምቶም አይታወቅም እየተባለ ነው፡፡ እርግጥ ነው ጨቅላ ሕጻንን በአሸዋ አፍኖ፣ ጉልበት ተጠቅሞ ደፍሮ፣ ገድሎ፣ ለመሸፋፈን ሌላ ጉዳት አድርሶ በጭራሽ ሰውኛ ያልሆነ ድርጊት ነው፡፡ ይዘገንናል፡፡
በዚህ አጋጣሚ በጣም ብዙ መሰል አሰቃቂ ድርጊት በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎች ተሰምቷል እኮ! ልክ እንደዚህ በአስከፊ ሁኔታ ተደፍረው ታፍነው የተገደሉ ሕጻናት እና ሴቶች እኮ ብዙ ናቸው፡፡ ከአንድም ሁለት ሦስት አራ አምስት እየሆኑ ደፍረው ሲያበቁ ተደፋሪዋ “በሕይወት ከተረፈች ታጋፍጠናለች” በሚል ገድለው ለአውሬ ሰጥተዋቸው የተቆራረጠ ሰውት እና ልብሳቸው የተገኙ እኮ ብዙ ናቸው! አስገድዶ መድፈሩ በሕይወት ላይ ጉዳት ካላመጣ ደግሞ ታፍኖ የቀረበት ሁኔታ ቤት ይቁጠረው! ብዙ ጥቃቶች የታፈኑት ወላጆች ወይንም አሳዳጊዎች እንደ ሄቨን እናት ደፍረው ባለመውጣታቸው አልያም የወጡትም ደግሞ ከቀናት ያለፈ ትኩረት ያለማግኘታቸው ነው፡፡ የመድፈር የባሰ እና ያነሰ የሚባል ባይኖረውም በአባቶቻቸው የተደፈሩ ሴት ልጆች፣ በወንድም እና በሌሎች የቅርብ ቤተሰብ እየተደፈሩ ያሉ ሴቶች እና ሕጻናት እኮ ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ክፉን ከክፉ ማወዳደር ደግ ባይሆንም በአባት ከመደፈር የከፋስ ይኖር ይሆን? የአባታቸውን ልጅ ወልደው የሚያጠቡ ልጆች እኮ አሉ! ውይ በጣም ይዘገንናል! መሞትማ በምን ጣእሙ ብለን አናውቅም?
ሀገራችን በወንድማማቾች እና እህትማማቾች መሀከል በሚደረግ ጦርነት ተወጥራ ባለችበት እዲሁም ደግሞ የኑሮ ውድነቱ የሰውን ናላ እያዞረ በሚገኝበት በዚህ በከፋ ዘመን እንደ ምክንያት ሆኖባቸው ከቄአቸው እየተፈናቀሉ፣ እየተደፈሩ መደፈራቸው ሳያንሳቸው መጠቋቆምያ እና መዘባበቻ የሆኑ ሴቶች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ባልጠና ሰውነታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ የሚደፈሩ ሕጻናት፤ በዚያ ምክንያት ለሕመም እና ለሞት የተጋለጡትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ይህንን የልጆቻቸውን ሰቆቃ በቁማቸው እያዩ የስነልቦና ቀውስ የደረሰባቸው እናቶች ብዙ ናቸው፤ አባቶችም ጭምር፡፡ ለነገሩ እናቶች እና አረጋውያን ሳይቀሩ እኮ የአስገድዶ መደፈር ሰለባ ሆነዋለል! መገለሉ እና መገፋቱስ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ አስባችሁታል!? አንዲት እናት በደረሰባት የአስገድዶ መደፈር ወንጀል ባለቤቷ እና የልጆቿ አባት እኮ ፈልጋ ያደረገችው ይመስል “አዋረድሽኝ መጠቋቆምያ አደረግሽኝ” ብሎ ከነልጆቿ ጥሏት ጠፍቶ እሷና ልጆቿ በጎዳና ላይ በልመና ላይ እየወጡ አይተናል፡፡ እንግዲህ እንደዚህ ያሉ ብዙ ታሪኮች ያሉን ዜጎች ነን፡፡
አስገድዶ መድፈር እንደ ወንጀልነቱ የሚገባውን ቅጣት እያገኘ አይደለም፡፡ ከቅጣቱ መቅለል፣ ድርጊቱ የተፈፀመባቸውን ከማሸማቀቁ እና ከማስፈራራቱ የተነሳ ሪፖርት የማይደረገውን ጥቃት ቤት ይቁጠረው፡፡ በዚያ ላይ የአንድ ወቅት ጩኧት ከመሆን የማያልፍ የተድበሰበሰ የአንድ ወገን የድረሱልን ጥሪ መሆኑን ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ እንዲያውም የሄቨን ጉዳይ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል፤ የሴቶችንም የወንዶችንም፡፡ ከዚህ ቀደም በሚዘገቡ ጥቃቶች እኮ ሴቶች በሶሻል ሚዲያ እና ባገኙት መድረክ ሁሉ ይጮሀሉ፤ ከዚያ ማንም አይሰማም፤ ምንም አይደረግም እናም ታፍኖ ይቀራል፡፡ አንዳንዶቹ ወንጀለኞችም ተፈትተው ሕጋዊ ሰው ሆነው ኑሯቸውን ሲያጣጥሙ ይታያሉ፡፡
ብዙ ሴቶች የአስገድዶ መደፈር አልያም የጾታዊ ትንኮሳ ሰለባ ይሁኑ እንጂ መጠቋቆምያ ላለመሆን ሲባል እንደተዳፈነ የሚቀር አጀንዳ ነው፡፡ የተቀበረ ነገር ያልታከመ ማንነት ይዞ ይቆይና አንድ ቀንወይ ትዳር ከያዙ በኋላ አልያም በሌላ ማህበራዊ ኑሯቸው ላይ ተጽእኖ ሲያሳድርባቸው ይታያል፤ ምስጢሩን ግን እነሱ እና ያልታከመው ማንነታቸው ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ አንዳንድ ሴቶች እንዲያውም “ትዳር ለምኔ?” ብለው የወሰኑ አሉ፤ በእራሳቸው ወይም በሌሎች ላይ በደረሰ ጾታዊ ጥቃት ምክንያትነት፡፡ ትዳር ደግሞ ቤተሰብ ብሎም ሀገር የሚገነባበት ተቋም መሆኑን ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡
እናም አስገድዶ መድፈር እና ማንኛውም የጾታዊ ጥቃት እና ትንኮሳ የእለት ተእለት የኑሯችን አካል ከመሆኑ ብዛት ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ እያስከተለ የሚገኝ መሆኑ ታምኖበት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ የሚሆነው መቼ ይሆን!? መቼ ይሆን እንደዚህ ያለውን ጥቃት እየፈፀሙ ያሉ ጥቂት ወንዶች መልካም ወንዶችን በጅምላ ማስፈረጅ የሚያቆሙት? ይሄ ጉዳይ ለምንድነው ሴቶችን እንዳሳሰበን ሁሉ ወንዶችን የማያሳስበው? አንድ ወንድ እኮ ሴት ልጅ ባትኖረው ሚስት፣ ሚስት ባትኖረው እህት፣ እህት ባትኖረው እናት አለችው! መቼስ ያለ እናት የተፈጠረ ሰው የለምና! ይሄ ሕመም ሁላችንንም ካላመመን፣ ሁላችንም እንደዜጋ ካልታከምነው ስር እየሰደደ ሄዶ ሄዶ ከዚህም የከፋ ማህበራዊ ቀውስ እንዳያመጣ እሰጋለሁ፤ እርግጠኛ ነኝ ስጋቴን እናንተም ትጋሩኛላችሁ፡፡ እናም ዛሬ ጥሪ ነው የማደርገው! መልካም ወንዶች በጥቂት ወንጀለኞች ምክንያት ስማችሁ መጉደፍ የለበትም፡፡ “አቤት ወንዶች!!!!” ተብላችሁ በጅምላ መወረፍ የለባችሁም፡፡ ሽፍንፍኑም ይገለጥ! ሁላችንም ወንጀለኞችን በቃ እንበላቸው! በተለይ ወንዶች ይሄ ጉዳይ ጉዳያችሁ ነውና ግቡበት እና ወንጀሉን አብረን እንከላከለው! ሽፍንፍኑ በቃ እንበል! ለዛሬ ጨርሻለሁ!
የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም
Share with your circle!