የዘራነውን ስንዘረዝር!

አንድ ቀን እለት አንድ ሆስፒታል ውስጥ ቁጭ ብዬ ተራ እየጠበቅሁ ሳለሁ ዘለግ ያለች ሴት የተጫማችውን ነጠላ ጫማ በድካም ስሜት እየጎተተች መጥታ ፊት ለፊቴ ተቀመጠች፡፡ ፊቷ አዲስ አልሆነብኝም፤ ግን ደግሞ እሷ ፊት ላይ ምንም “የት ነው የማውቃት?” መደናገር ስላላየሁባት የመልክ መመሳሰል አድርጌ ወስጄው በዝምታ እያለሁ ለየት ያለው ስሟ ከነአባቷ ሲጠራ ግምቴ ልክ እንደነበረ አመንኩ፡፡ አንድ አካባቢ (በድሮ አጠራር ቀበሌ) ነበር ያደግነው፡፡ የአስተዳደጋችንን ልዩነት እና አሁን ያለንበትን ልዩነት እያውጠነጠንኩ ሳላስበው እዚያ ዘመን ላይ ደረስኩ፡፡ ለካ አንዳንዴ የዘራነውን እንዘረዝራለን!

ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ ወቅቱ ድሮ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበርኩበት ነው፡፡ መጀመርያ ዲፕሎማ ተመርቄ እንደገና የማታ ማኔጅመንት እየተማርኩ ነበር፡፡ ያን ጊዜ እንዲህ እንደ አሁኑ በየቤቱ ተመራቂ በሌለበት ዘመን (ከሃያ ዓመት በፊት) በተለይ ሴት ልጅ ተመረቀች ሲባል በቀበሌው ከጫፍ እስከጫፍ የሚሰማበት እና የሚደነቅበት ወቅት ስለነበረ እኔም እውቅና ካገኙት ጥቂት የቀበሌአችን ልጆች አንዷ ነበርኩ፡፡ ታድያ ምርቃት ዲፕሎምም ሆነ ድግሪ ያው እኩል ስለሚታሰብ የእኔ ለድግሪ ሰባት ዓመት ለመማር በድጋሚ መግባት ያስደነቃቸው ያሉትን ያህል መንቻካ የመሰልኳቸውም አልታጡም፡፡ የዚች ከላይ የጠቀስኳት ልጅ አባት አንዱ ነበሩ፡፡  ንግዳቸው ምን እንደሆነ ባላውቅም ነጋዴ እና ከአካባቢው ሰው የተሻለ ኑሮ እንደነበራቸው አስታውሳለሁ፡፡ በየክፍለሀገሩ በንግድ ስራ ስለሚጓጓዙ ጠንካራ ሰራተኛ ናቸው ተብሎ ይነገርላቸውም ነበር፡፡

ታድያ መጥፎ አመል እንዳለባቸውም እኔ ደርሼባቸዋለሁ፡፡ በዚያ ዘመን ስራ እየሰሩ መማር ከበድ ስለሚል አንዳንዴ ትራንስፖርት ወጪ ለመቀነስ የተወሰኑ መንገዶችን በእግር መሄድ (walk) ማድረግ የብዙዎቻችን ኑሮ ነበር፡፡ እንደ እሳቸው ላለ የገቢ ችግር ለሌለበት ሰው ደግሞ መራመዱ ለጤና እና በለስ ከቀና ለጅንጀና ይጠቀሙበት ነበር፡፡ የዚህ አጉል ባህርያቸው ጽዋ ደረሰኝ እና የአብነትን ቁልቁለት በጋራ ስንገፋ እንደ አዲስ ተዋወቅን፡፡ እሳቸው አያውቁኝም ነበር፡፡ ያው ልጆች አዋቂዎችን እናውቃለን እነሱ ሁላችንንም አያውቁንም፤ እንደዚያ ማለት ነው፡፡ ከዚያም የአባትነት ወጋቸውን ትተው እኔን የልጆቻቸውን እኩያ መጀንጀን ያዙ ማለት ነው፡፡ ይሄ ገጠመኝ የብዙዎቻችን ስለሆነ ላይደንቅ ይችላል፡፡ ግን ነገሩ ወዲህ ነው፡፡

የጅንጀናቸው አካሄድ ዙሩ እየከረረ ሲሄድ አንቱታውን ተይው አሉኝ፡፡ ከዚህ በኋላ እሳቸው ያልጠበቁትን ክብራቸውን ልጠብቅላቸው ብዬ “የእነ እንትና አባት አይደሉ? እኔ እኮ ከልጆችዎ ጋር አብረን ነው ያደግነው፤ የወ/ሮ እከሊት ልጅ ነኝ” አልኳቸው፡፡ ምንም አይነት ድንጋጤ ላለማሳየት ሞከሩ፡፡ እናም ከዚያ በፊት ለውበቴ ማጣቀሻነት የተጠቀሙባቸውን እነገንቦ ሁሉ ስብርብራቸውን አውጥተው እና በዜሮ አባዝተው “አንቺ የእሷ ልጅ? እሷ እንኳን ልቅም ያለች ቆንጆ ናት ምነው ታድያ አንቺ…!?” አሉኝ፡፡ የእኔን ውበት ማውረዳቸው ሳይሆን ቆንጅዬዋን እና ቆፍጣናዋን እናቴን ማሞገሳቸው ልቤን እያሞቀው ሳለ አንድ ነገር ተናግረው ሙቀቴን ቀዝቃዛ ውሀ ቸለሱበት፡፡ ” ተመርቀሻል አልተባለም እንዴ ምነው ድጋሚ ትምህርት? ለነገሩ እንደ እናንተ ዓይነት ፉንጋዎች ከመማር ውጪ ምንም አማራጭ የላችሁም፤ የእኔን ልጆች እንዳየሻቸው ቀንበጥ የመሳሰሉ ናቸው፡፡ በመማር መድከም አይጠበቅባቸውም፡፡ ብረት መዝጊያውን ያመጡልናል!” አሉኝ፡፡ ጠላታችሁ ክው ይበልና ክው ነው ያልኩት፤ እሳቸው እንዳሉት አስቤ ሳይሆን አንድ አባት የሴት ልጁን ተመን በጥገኝነት ዝቅ አድርገው ትምህርትን አለማካተታቸው ነበር፡፡

ልጃቸው ተጠርታ ከገባችበት ክፍል ሳትወጣ እኔ ተጠርቼ ሌላ ሐኪም ያለበት ክፍል ስለገባሁ ዳግም መልሼ ላያት እንደማልችል እያሰብኩ ከትዝታዬ ጋር እየተፋለምኩ ቆየሁ፡፡ ነገር ግን ሁለታችንም ለተጨማሪ ምርመራ የተላክንበት ቦታ አንድ ስለነበር በተሻለ እና ሰው ባልበዛበት ሁኔታ በግላጭ አገኘኋት፡፡ መቼስ “አባትሽ ድሮ እንዲህ ብለውኝ ነበር!” አይባል ብቻ ድጋሚ ሳገኛት መደሰቴ ገርሞኛል፡፡ አባቷ ያስቀመጡላት (የገመቱላት) ኑሮ በእጇ ገብቶ እንደሆን ለማወቅ ጓጓሁ፡፡ እንደምንም አካባቢዋ ሄጄ ተቀመጥኩ፡፡ እጅ ነሳኋት እና “ሰላም እከሊት፣ ፍፁም ነኝ (የቤት ስሜንም ጨመርኩላት ይበልጥ እንድታስታውሰኝ)፣ አንቺ እረስተሸኛል መሰለኝ፤ እኔ ግን ገና ስትመጪ ነበር ከትንሽ መደናገር በኋላ ያስታወስኩሽ” አልኳት፡፡ እሷም እጅ ስለነሳኋት ተደስታ እንዳየችኝ እንዳወቀችኝ፣ ቤታቸው በቲቪ መስኮት አልፎ አልፎ እንደሚያዩኝ እና ቤተሰቦቿ በሙሉ (አባቷን ጨምሮ) እንደሚያስታውሱኝ እና እንደሚያደንቁኝ ነገር ግን ቀድማ ሰላምታ ያልሰጠችኝ ላላስታውሳት እንደምችል ገምታ እንደሆነ ነገረችኝ፡፡ አንድ ሁለት እያልን ስለ ቀድሞ የልጅነት ሕይወታችን እና ስለ አሁኑም (በመጠኑ) መረጃ ተለዋወጥን፡፡ በዚህ መሀከል “አባት ሌላ ልጅ ሌላ!” ብዬ ከልብ ነበር ተደስቼ የማጫውታት፡፡ ከሁኔታዋ እንደተረዳሁት ልጅት አባቷ የተመኑላትን ኑሮ እየኖረች አይደለም፡፡ የልጅነት ውበቷ በደምሳሳው የሚታይ ቢሆንም ጎስቆልቆል ብላለች፡፡ ሕይወት መች እንደተሰመረላት ናትና!

እኒያ አባት ልጆቻቸውን ቁንጅናቸውን እየነገሩ እና እየዘመሩ ብረት መዝጊያ አማት እንዲያመጡላቸው በመምከር አሳድገዋቸው ይሆናል፤ ነገር ግን የተሳካላቸው አልመሰለኝም፡፡ ሌላው ቢቀር እራሷ ለእራሷ መዝጊያ እንድትሆን አድርገው አላሳደጓትም፡፡ የሆነውን ለምን አልነግራችሁም!? አባቷ እናቷን ሲያበሳጯቸው ውጭ የሄደች እህቷ ዘንድ ሄደው ቀርተዋል፣ እኒያ አባቷ እሷን ደግሞ በእድሜ አቻዋ ላልሆኑ ሀብታም ጓደኛቸው ድረዋት ሁለት ልጅ ከወለደችላቸው በኋላ በወጣሽ ገባሽ ሲደበድቧት ልጆቿን ይዛ አባቷ ግቢ ሰርቪስ ውስጥ ኑሮዋን እየገፋች እንደሆነ አጫወተችኝ፡፡  አንዳንዴ የአባት ግፍ በልጅ ይደርሳል የሚባለው ነገር ይሆን? ይህን ሁሉ ታሪክ ያስተረኩኝ እኒያ አባቷ  አልከበር ብለው ባደረሱብኝ ትንኮሳም አይደል! በዚህ ዓይነት በስንት ወጣት ሴቶች ሕይወት እንደተጫወቱ ልብ ይሏል፡፡ ወላጆች ግን እዚህ ድረስ ያንሳሉ ብላችሁ ገምታችሁ ታውቃላችሁ? ይህ ትርክት ጨዋ አባቶችን አይመለከትም! ውጫዊ ተክለ ሰውነት ወይንም ውበት እኛ የምንሰራው ሳይሆን በፈጣሪ ብቻ የሚሰጥ መሆኑን የማያውቁ ወላጆች የወላጅነት ክብራቸው መነጠቅ አለበት፤ ዛሬም እዚያ ድረስ ዝቅ ያሉ መሀይሞች (The ignorant) መኖራቸው አይቀርም፡፡ አስቡት ወጣቶች ተምረው ወይንም በሌላ ሙያ ተጣጥረው መክሊታቸውን እንዳያገኙ በወላጆች እና በአካባቢ ሰዎች ያረጀ እና ያፈጀ አባባል ጊዜአቸው እንዴት እየባከነ እንደሆነ! እኚያ አባት የዘሩትን ዘርዝረዋል፡፡ እርግጥ ጥቂቶች በለስ ቀንቷቸው ይሆናል፡፡ ግን ደግሞ ሀብትም ቢሆን ጥረው ተጣጥረው ሲያገኙት የበለጠ ጣእመኛ ነው፡፡ እናም ይህ ያረጀ እና ያፈጀ አመለካከት እንጦሮጦስ መግባት አለበት! አለበለዝያ የዘራነውን እየዘረዘርን እንኖራለን፡፡ ለዛሬ ጨርሻለሁ!

የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top