ማህበራዊ ኃላፊነት እና የእራስ ኃላፊነት

ምን ሆነ መሰላችሁ! ሰሞኑን አንድ የቤተሰብ የምሳ ግብዛ ላይ አንድ ወጣት በትህትና ሲያስተናግድ ቆይቶ ለመሄድ ሊሰናበት ሲል ግብዣውን ያዘጋጁት ታላቅ ሰው ልጁን ለታዳሚዎች ማስተዋወቅ ፈለጉ፡፡ በጣም ጥሩ ልብ ያለው ልጅ መሆኑን፣ የዩኒቨርስቲ ምሩቅ መሆኑን እና ድግሱንም በደንብ ያገዘ መሆኑን አስተዋወቁና እስቲ እራስህን አስተዋውቃቸው በማለት እድሉን ሰጡት፡፡ እሱም ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ የተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎችን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ጭምር ወስዶ ነገር ግን ስራ አጥ መሆኑን በቀዳሚነት ካስተዋወቀ በኋላ፣ የተለያዩ ንግዶችን (የስራ ፈጠራ ስራዎችን) የሞከረና ያልተሳካለት መሆኑን፣ በዋናነት ሜንቶርሽፕ፣ ካውንስሊንግ (የጋብቻ ማማከርን ጨምሮ) የተለያዩ የበጎ ስራዎች ላይ ተሰማርቶ እያገለገለ መሆኑን ረዥም ደቂቃዎች ወስዶ ነገር ግን ብትንትን ባለና ውሉ ባልተጨበጠ መልኩ አብራራ፡፡ የታዳሚዎቹ የብስለት ስብጥር (የአካዳሚክ ብቃት እና ልምድ) የአንድን ወጣት ይሄን ሁሉ ጥረት አድንቆ ዝም ብቻ የሚል አልነበረም፤ ለማገዝም አቅም የነበራቸው ጭምር እንጂ፡፡ እናም በጥሞና ካዳመጡት በኋላ የተለያዩ ጥያቄዎችን ጠየቁት (እኔንም ጨምሮ)፡፡ እነዚህም ጥልቅ ፍላጎት ኖሮት ሊሰራው የሚችለው ስራ (passion), ዓላማውን (objective) የነገ ራእዩ (dream) ትክክለኛ ትኩረቱ (focus area) ዋና ዋናዎቹ ነበሩ፡፡ እሱ ግን የአንዳችንንም ጥያቄ በትክክል ማብራራት አልቻለም ነበር፤ ከተሰጠው ረዥም ጊዜ አንጻር፡፡
እንደዚህ ወጣት ዓይነቶች ሲያጋጥሙኝ የመጀመርያዬ አልነበረም፤ የመጨረሻም አይሆንም፡፡ ወጣቶቻችን (በአብዛኛው) አቅጣጫ መለየት ላይ በቂ እገዛ ስለሌላቸው፣ የትምህርት አሰጣጡ ሂደቱ እና ጥራቱ፣ ማህበራዊ ሚዲያው የፈጠረባቸው ጫና፣ የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ እና ሌሎችም ተግዳሮቶች ውዝግብግብ አድርገዋቸዋል፤ ከምር አንጀት ይበላሉ፡፡ እኛ እኮ ልክ እንደተመረቅን የስራ ምደባ ተደርጎልን እየሰራን ከዚያ ነው አማራጮችን የምንፈልገው፡፡ የእኛ ጊዜ በእርግጥ ከቅጥር ውጭ ሕይወት ያለ ባይመስለንም በአንጻራዊነት ደጉ ጊዜ የሚባል ነው፡፡ ዛሬ የተመረቁትም እውቀታቸው አጠያያቂ ነው፤ ሰቃዮችም(እውቀታሞቹ) ቢሆኑ አማራጮችን ፈላጊዎች ሳይሆኑ የተመቻቸ ሁኔታ ጠባቂዎች ናቸው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ግን ነጥረው የሚወጡ ስራ ሳይንቁ ተሯሩጠው ሰርተው እራሳቸውን የሚችሉትን ያለማድነቅ ንፉግነት ነው፤ እነሱ ደግሞ ይብዙልኝ!
እኔ ከዚህ መነሻዬ ከሆነው ወጣት የተበታተኑ ሀሳቦች ውስጥ አንዱ እና ቀልቤን የገዛው ለዚህም ጽሑፌ ዋና ርእስ አድርጌ ያመጣሁት ማህበራዊ አገልግሎት ለመስጠት ያለው ተነሳሽነት ብቻ ሳይሆን ጥልቅ ፍላጎት ነው፡፡ ታድያ መልካም ልቡ ደስ ቢለኝም ከጋሪው ፈረሱ ነው የሆነብኝ፡፡ በነገራችን ላይ ይሄን ሀሳብ ወደዚህ ያመጣሁበት ምክንያት ይሄ ሀሳብ በዚህ ልጅ ላይ ብቻ ያስተዋልኩት ሳይሆን በብዙ ወጣቶች ላይ ያስተዋልኩት ነው፡፡ በተለይ አሁን ሶሻል ሚዲያው ስለበዛ ብዙ የማየት እና የመስማት አጋጣሚውም አለ፡፡ ቲክቶክ ላይ ብዙ ወጣቶች ማህበራዊ አገልግሎት ሲሰጡ አስተውያለሁ፡፡ ከዚያም አልፎ ለሚሰሩት ስራ ከሰዎች የሰበሰቡትን ገንዘብ “ገንዘብ ስለቸገረኝ በልቼዋለሁ” የሚሉትንም ሰምተናል፡፡ እና ምን ያስመስላል፤ በጎ ስራ መስራት የስራ አማራጭ ሆኖ ያበላል የሚል አንድምታ ያለው መሆኑ ያየነውም ሐቅ ነው፡፡ ግን ዘላቂ እንጀራ የሆነላቸው በጣም ጥቂት ናቸው፡፡
ማህበራዊ ኃላፊነትን/ግዴታን በመወጣት አዎንታዊ ለውጥ የማምጣት ኃላፊነት በየደረጃው የሁሉም ድርሻ ነው፡፡ ግለሰብ፣ ድርጅት፣ የገንዘብ ተቋማት፣ አለማቀፍ ድርጅቶች ሁሉም ኃላፊነት እንዳለባቸው የታወቀ ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ ካየነው ግን አንድ ሰው ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት መጀመርያ የእራሱን ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡ ይህም እራስን መቻል ማለት ሲሆን በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በልምምድ፣ በስሜት ብስለት እና በመሳሰሉት ማለት ነው፡፡ ገንዘብ ለማግኘት ስራ መሰራት አለበት፤ ይህም በቅጥር አልያም ንግድ (ቢዝነስ) ላይ በመሰማራት ሊሆን ይችላል፡፡ ታድያ ይሄንን ያላሟላ ሰው እንደምን ሌሎችን መርዳት፣ የሕይወት ክህሎት ማጋራት፣ ካውንስል ማድረግ፣ ሜንቶር ማድረግ፣ ማሰልጠን (coatching) ይቻለዋል? ግድ የላችሁም ዘመናችን በደንብ ተወዛግቧል!
ይህንን ወግ ወደ እናንተ ያመጣሁት ለወቃሽነት ሳይሆን የዛሬ ወጣቶች የሁላችንም በተለይ የእኛ የጎልማሶቹ ኃላፊነቶች መሆናቸውን ለማስታወስ ነው፡፡ መንግስትም በመንግስትነቱ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ ስራ ፈጠራ ለሁሉም የተሰጠ መክሊት አይደለም፡፡ የተፈጠረ ስራ ውስጥ እንደእነዚህ ያሉ ተመራቂዎች ተቀጥረው የሚሰሩበት እድል እንዲያገኙ ሀገሪቱ ለኢንቬስትመንት ምቹ መሆን አለባት፡፡ አንዳንዴ እኮ ለኮንሰርቶች እና መዝናኛዎች የሚወጡት ብሮች (እንዲያው በሰው ገንዘብ ማን ፈራጅ አደረገሽ እንዳትሉኝ እንጂ) ግብግብ ያደርገኛል፡፡ መዝናናት ለአእምሮ ጥሩ ቢሆንም ቅሉ ጥሩ ነገር ማሰብና መስራት ላልቻለ አእምሮ ግን የእለት ጩኸት ከመሆን ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ መንግስት ምን ያድርግ ትሉኝ ይሆናል፡፡ ቀላል ምሳሌ ድሮ ድሮ በእኛ ዘመን እርሻ ክፍለ ጊዜ የሚባል ነበር፡፡ ከአፈር ጋር እየቦካን በየጊዜው ውሀ እያጠጣን ያበቀልነውን ጥቅል ጎመን፣ ካሮት…ወዘተ ቤታችን ይዘን እንሄድ ነበር፡፡ ዛሬ በየወረዳው ጥቃቅን ቦታዎች እየተፈለጉ ወጣቱን እርሻ፣ ንባብ፣ የተለያዩ ሙያ ልምምዶች፣ አካላዊ ብቃት እያደረጉ የሚውሉበት ቦታ ቢፈጠርላቸው እና (እኛንም አዋጡ ብለው ቢያሳትፉን) ስራ ሳይንቁ የሚሰሩ ወጣቶች ማውጣት ይቻላል ብዬ የማምን ነኝ፡፡ ከዚህም የተሻለ ማድረግ ይቻላል፤ እኛም ማህበራዊ ግዴታችንን (ኃላፊነታችንን) በትክክለኛው ቦታ እንወጣለን ማለት ነው፡፡ ይህ አንድ ምሳሌ ነው፡፡ ብዙ አማራጮች ለወጣቶች መታደግያ ይምጡ!
ይሄ ወጣት ልጅ ብዙ አስወራኝም አይደል! አዎ ከማጠቃለሌ በፊት ሌላ ያየሁትን ደግሞ ላክልላችሁ፡፡ አብዛኛው ወጣቶቹ የራሳቸው ራእይ ላይ ገና ስላልደረሱ የሌላ ሰው ራእይ የሚደግሙ ተናጋሪ ወፎች (parrot) የሚመስሉትስ ነገር፡፡ ልክ እንደዚህ ወጣት ብዙ ሙያተኛ (ሊቃውንት) ከዚህም ከዚያም በተቆርቋሪነት በጥያቄ ሲያዋክቡት ውል የሌለው ነገር ተናግሮ እንደጨረሰው ዓይነት ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ቢያንስ ሲጠየቁ ሀሳባቸውን ሰብሰብ አድርገው በአጭር ደቂቃዎች ለሙያተኛ ወይንም ለአጋዥ እንዴት ማቅረብ እንዳለባው (pitching) ባገኘነው አጋጣሚ ብናስተምራቸው ለጽድቅ ሳይሆን ማህበራዊ ግዴታችንን እየተወጣን መሆኑን ከአደራም ጭምር ላስታውስ እወዳለሁ፡፡ እኔ ይህንን እያደረግሁ ስለሆነ እና በአንድም በሁለትም ወጣቶች ለውጡን እያየሁ ስለሆነ ነው የምመክረው፡፡
ይህንን ብሎግ የምታነቡ ወጣቶች ካላችሁ በአጽንኦት አንድ የምመክራችሁ ነገር ቢኖር ማህበራዊ ኃላፊነት የእራስን ኃላፊነት ከመወጣት የሚጀምር መሆኑን ነው፡፡ እራሳችሁን በአቅም ሳታበቁ (በገንዘብ፣ በእውቀት እና በልምምድ) ሌሎችን መርዳት ዋነኛ ስራችሁ መሆን የለበትም፡፡ በእርግጥ አልባሌ ቦታ (የማይሆን ቦታ) ከመዋል የበጎ ፈቃደኝነት ስራ ላይ መሰማራት ስራ መልመድን ከማስገኘቱ በተጨማሪ የአእምሮ እርካታም ይሰጣል፡፡ ነገር ግን በጎ ፈቃደኝነት የሙሉ ጊዜ ስራ አይደለም፡፡ ሌሎች ደግሞ የበጎ ፈቃደኝነት ፈቃድ አውጥታችሁ ከሰው እርዳታ እየሰበሰባችሁ መስራትም እንደ እኔ አሪፍ አማራጭ አይደለም፤ ምክንያቱም በጎነትን ቢዝነስ እያደረጋችሁት ነውና! ዘላቂነት ያለው እራስ የሚያስችል ስራ በሙያችሁ አልያም በጥልቅ ፍቅራችሁ ለመስራት የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ክፈሉ የምል ነኝ፡፡ ለዛሬ ጨርሻለሁ!
የተፃፈው በ: ፍጹም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም
Share with your circle!