ወንዶች እና ቀለበት

በስራዬም በትምህርት ቤቶቼም ያፈራኋቸው ድንቅ ድንቅ የሁኑ የወንድ ጓደኞች አሉኝ፡፡ ወንዶች ለጓደኝነት በጣም ይመቻሉ፡፡ ጓደኝነት ስል ግልጽ ለማድረግ ጾታዊ ንክኪ የሌለበት ጓደኝነት ወይንም በተለምዶ ወንድም ጓደኛ ማለት ነው፡፡ በተለይ በአንድ ርእሰ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ያወቁትን እና የገባቸውን በግልብ ያለማለባበስ ለማስረዳት ምንም ወደኋላ አይሉም፡፡ እንደዚያ ማለቴ ደግሞ ሴት ጓደኞች አይመቹም እያልኩ እንዳልሆነ ያሉኝ የሴት ጓደኞች ብዛት ምስክር ነው፡፡ አሁን ለማውራት የፈለግኩት ስለግልጽ ውይይት ነው፡፡ በተለይ እኛ ሴቶች ብዙ ነገር እንደ ነውር (taboo) እየተቆጠረብን ሀሳባችን ተቆነጣጥሮ የሚቀርብበት ይበዛል መሰለኝ፤ ማለቴ መሰለኝ ስል ያው ጥርጣሬ ነው፡፡ እና ግልጽ ውይይት የምንፈራው ወደንና ፈቅደን ሳይሆን ማህበረሰቡ የሰራን በሽፍንፍን እንድንወያይ ነው ለማለት ነው፡፡

በቀደም እለት ከጥቂት ወንድ ጓደኞቼ ጋር ቡና እየጠጣን በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ እንወያይ ነበር፡፡ እናም በመሀከላቸው የነበርኩት ሴት እኔ ብቻ ስለነበርኩ ያው እንደ ቦርድ ስብሰባ በሉት፤ እራሳቸው አውርተው እራሳቸው የሚወስኑበት ርእስ በመብዛቱ እራሴን ከተወያይ እና ተሟጋችነት ወደ ታዛቢነት ተዘዋውሬ አገኘሁት፡፡ የርእሰ ጉዳዮቹ ስብጥርነት ልዩ ህብር ቢያሳየኝም የተወያዮቹ የጾታ አለመሰባጠር ግን ህብረ ቀለሙን አደበዘዘብኝ እናም “ይሄ ጾታ ግን ምን አይነት ነው!?” እያልኩ ለብቻዬን መፈላሰፍ ጀመርኩ፡፡ ደግሞ መገለሌን አንዳቸውም ያለማስተዋላቸው የበለጠ የማሰብያ ጊዜ ሰጠኝ መሰለኝ ያላስተዋልኩት ነገር የለም፡፡ እናም ስራ የፈታው አእምሮዬ ካሳየኝ ነገሮች አንዱ የእጆቻቸው ቀለበቶች ናቸው፡፡ እናንተ ለካስ ያገቡ ወንዶች በአብዛኛው ቀለበታቸውን እቤት አስቀምጠውታል! ከእኔ ጋር ከነበሩት ስድስት ወንዶች አራቱ ያገቡ ሲሆኑ ቀለበት ያጠለቀው አንዱ ብቻ ነበር፡፡ እናም ዝምታዬን መስበር እና እኔንም አሳታፊ የሆነ ርእስ ለማምጣት በማሰብ “ለምንድነው ግን በአብዛኛው ወንዶች ካገቡ በኋላ የጋብቻ ቀለበታቸውን የማያደርጉት!?” በማለት ያላሰቡትን ጥያቄ ጠየቅኳቸው፡፡ ከርእስ ውጪ (off topic) መሆኔ ዘና ሳያደርጋቸው አልቀረም ተወያየንበት፡፡ ከመነሻዬ እንደነገርኳችሁ እኔ የምጎዳኛቸው ወንዶች በጣም መልካም ስብእና ያላቸው ስለሆኑ ምላሻቸው የመልስ ምታዊ ሳይሆን በገባቸው እና ከእራሳቸው ተሞክሮ በመነሳት ነበር፡፡ ከዚያ በፊትም ሌሎች ወንዶችን ጠይቄ የተሰጠኝ ምላሽ ጋር የተቀራረበ ነው፡፡

ብዙ ወንዶች ቀለበት የማያደርጉበትን ምክንያት ሲገልጹ ወርቅ አልወድም፣ አለርጂ ነኝ፣ ያሳክከኛል፣ ይጨንቀኛል፣ ካገባሁ በኋላ ስወፍር ጣቴን ጨነቀው፣ ቀለበቴን በልቤ አስሬዋለሁ፣ ወዘተ የሚሉ ናቸው፡፡ ከእለታት አንድ ዘመን አበበ ተካ የሚባል ድምጻዊ “ምንድነው ቃልኪዳን ምንድነው ቀለበት፣ ፍቅር ቤት ካልሰራ ማላው ምን ሊረዳ እኛ ከተካዳን፣…” ከዚያም ይቀጥልና “ቀለበት ላይ አስረው ፍቅርን አቻ ላቻ፣ በ80 ላይቆም ጎጆና ጉልቻ፣ …” እያለ ያዜመው ዘመን ተሸጋሪ ዜማ ትዝ አለኝ፡፡ ለማንኛውም ሙሉውን ለማስታወስ አዳምጡት ጋብዣችኋለሁ፡፡ አዎ ቀለበት እና ቃልኪዳን ካልተከበረ ታሰረም አልታሰረ ምንም አይፈይድም፡፡ እናም ወንዶቹም ይህንኑ ነበር ሲያስረዱኝ የነበረው፡፡ ልክም ናቸው፤ ግን ደግሞ ሙሉ በሙሉ ለመቀበል በጣም አዳጋች የሆነብኝ ነገር ነው፡፡ በዛሬ የወርቅ ዋጋ ቀለበት ትርጉም ባይኖረው ስለምን ተገዝቶ በሰርጉ እለት ይታሰራል ዝም ብሎ መጋባት እየተቻለ!? የትዳር ጓደኛዋ ቀለበቱን ማስቀመጡ ምንም የማይመስላት ሴት ትኖራለች፡፡ ግን ደስ ይላት ይሆን!? እኔ ባለትዳር ነኝ፡፡ እናም ባለቤቴ የተለየ ምክንያት ኖሮት ያንን ምክንያት እኔም አውቄው የተስማማሁበት ካልሆነ በስተቀር ቢያወልቀው ደስ አይለኝም፡፡ እስቲ ሁላችንም ሴቶችም ወንዶችም በተለይ ያላገባን ከሆንን እና በሆነ አጋጣሚ የሆነ ተቃራኒ ጾታ ቀልባችንን የሚገዛ ነገር ሲያደርግ/ስታደርግ ብናይ እና “ለእኔ ባደረጋት/ባደረገው!” ብለን ብንማልል አይናችን ወደየት ነው የሚያማትረው!? ወደ ጣት፤ ቀለበት ፍለጋ አይደለምን!? እርግጥ ይሄንን ስታነቡ “ቀለበት ብቸኛው መገለጫ አይደለም!” እንደምትሉኝ አምናለሁ፤ እቀበላለሁም፡፡ ነገር ግን አንዱ መሆኑን እና በደመነፍስ አትኩሮት የሚስብ መሆኑን ደግሞ አንክድም፡፡ ሌላው እይታዬ ደግሞ ወንድ ልጅ ቀለበቱን ማስቀመጡ ማንም ከምንም አይቆጥረውም፡፡ አንዱ ምክንያት ደግሞ ወርቃቸውን የሚያስቀምጡ ቁጥራቸው የትዬለሌ ስለሆነ ነው፡፡ “ታድያ ምን ችግር አለው? ለምን አጀንዳ የመሆን አቅም አገኘ?” ትሉኝ ይሆናል፡፡ ከምንም ተነስቼ አይደለም፤ ብዙ በትዳር ላይ የሚገኙ ታማኝ ያልሆኑ ወንዶች ብዙ ሴቶችን ያላገቡ በመምሰል ቀርበው ጓደኝነት መመስረት ብቻ አይደለም አልፈውም በሚፈጠረው ጾታዊ ግንኙነት ልጅ እንዲወልዱ ካደረጉ በኋላ ትተዋቸው እየተሰወሩ ነጠላ እናቶች (single mothers) ለመብዛታቸው አንዱ ምክንያት ሆኖ እየሰማን እና እያየን ስለሆነ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ለእኛ ለሴቶች የቃልኪዳን ቀለበታችን የሰላምና መረጋጋት ኮሚሽነራችን በሉት፡፡ ጉዳይ ለማስፈጸም የሆነ ቦታ ስንሄድ የሚያስተናግዱን ወንዶች ከሆኑ እና ለማማለል አይን አይናችንን ያዩን ከመሰለን ጣቶቻችንን ለማሳየት ከፍ አድርገን ደመነፍሳዊ ማውለብለብ እናደርጋለን፡፡ በነገራችን ላይ በየሄድንበት የምናገኛቸው ወንዶች ሁሉ ጾታዊ ክጀላ ያደርጋሉ እያልኩ እንዳልሆነ ይሰመርልኝ፡፡ ሌላው በአብዛኛው ሴት ልጆችን በማማለል ሂደት ውስጥ ያሉት ወንዶች (ጓደኛ ፍለጋ ላይ ያሉት በሚል ተረዱልኝ) ቀለበት ያጠለቀች ሴት ላይ ማገዶ አያባክኑም፡፡ ምክንያቱም ትዳሯን ያከብሩላታል፣ አልያም ግብረ መልሷም ምን እንደሚሆን ከወዲሁ ያውቁታል፡፡ እናም ግግም ያሉት ካልሆኑ በስተቀር የሚቀርቧት ሴት ጥያቄአቸውን ልትቀበል የምትችለዋን ነው፡፡ አሁንም ቀለበት የሌላት ሴት ሁሉ ጾታዊ ጥያቄዎችን ትቀበላለች እያልኩኝ አይደለም፡፡ በዚያውም ልክ ቀለበት ያላትን የሚጠይቁ ደፋሮች የሉም እያልኩም አይደለም፡፡ የማወራው ስለ ትክክለኛው (Norm) አካሄድ ነው፡፡ እንጂማ ቀለበት ያለው ሰውዬ ቀለበት ያላደረገችውን በድፍረት የሚጠይቅበት እና “ባለትዳር አይደለህም ወይ!?” ለሚለው ጥያቄ የመሰለውን ድፍረታዊ መልስ የሚሰጥ ሞልቷል፡፡ ቀልብተው ካበቁ በኋላ ጾታዊ ጥያቄ የሚቀበሉ ሴቶችም አሉ ተብያለሁ፤ እንደወንዶቹ ቁጥራቸው በርካታ አይደለም እንጂ፡፡ በሰው የግል ሕይወት በመግባት ከትኩረቴ ወጣሁ መሰለኝ የእኔ ነገር!

መነሻዬ ወንዶች እና የቃል ኪዳን ቀለበት ነውና ሀሳቤን ጠቅለል አድርጌ ወጌን ላሳርገው፡፡ ይሄ ያነሳሁት አጀንዳ የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፡፡ እኛ ሀገር የተጠና ጥናት አላገኘሁም እንጂ በአጠቃላ አለማቀፍ እውነታ ነው፡፡ በአብዛኛው ወንዶች ባገቡ በጥቂት ወራት ወይንም ከጥቂት አመታት በኋላ የቃልኪዳን ቀለበታቸውን ያወልቃሉ፡፡ ሴቶቹ ግን ምናልባትም ሲወልዱ ከወፈሩ ያወልቁ እንደሆነ እንጂ አያወልቁም፡፡ ለእኔ በጣም አስገራሚ እውነት ነው፡፡ በእርግጥ እስከ መጨረሻው የማያወልቁ እንዳሉም እንዳንዘነጋ፡፡ አንጋፋው ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ባለቤታቸው በሞት ከተለዩም በኋላ እስከ እለተ ሞታቸው ቀለበታቸውን እንዳላወለቁ እና ድርሰታቸውን ፍቅር እስከመቃብርን ኖረው እንዳሳዩ ይነገርላቸዋል፡፡ ይህንን የምናነብ ባለትዳር እንስቶችም በየቤታችን ቀለበታቸውን ያላወለቁትን ባለቤቶቻችንን እያስታወስን “እዚህም እንደዚያ!” ያልን በርካታ ነን፡፡ ግን ለእኔ ሁሌም ጥያቄ ስለሚጭርብኝ ነው፡፡ ቀለበትን ለማውለቅ መጀመርያውንስ ማሰር ለምን አስፈለገ!? በተለይ በዚህ ፍቺ እንደ አሸን በፈላበት፣ ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች ባለቡት ዘመን ቀለበትን ከማውለቅ ማጥለቅ አይሻልም ይሆን!? ሕይወት እኮ በተለያየ አቅጣጫ ስትጓዝ ሕሊና ሸንቋጭ ነገር ያስፈልጋታል! የቃልኪዳን ቀለበት አንዱ ነው የምል ነኝ! በነገራችን ላይ ቀለበታችሁን በአሳማኝ ምክንያት ብታወልቁም ለትዳራችሁ ታማኝ የሆናችሁ እልፍ ወንድሞቻችን አላችሁ እና አሁንም እደጋግመዋለሁ፤ ይህ ጽሑፍ እናንተን አይመለከትም! ለዛሬ ጨረስኩ!

በፍፁም አጥናፈወርቅ ኪ/ማርያም

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top