እያለን የለንም!

በተለያየ የሙያ መስክ እና የሕይወት ጎዳና ላይ የምንገኝ ሰዎች በሆነ አጋጣሚ ተገናኝተን የተለያዩ ርእሶችን እያነሳን ስንጥል ውስጤ በጣም እየታዘበ ሲያስቸግረኝ እንደድሮ ጮክ ብዬ ከመናገር ይልቅ ዝምታን መርጬ ማዳማጥ ያዝኩ፡፡ ብዙዎቻችን ቤተሰብ የመሰረትን ስለሆንን የእራሳችን፣ የትዳር አጋራችን፣ የልጆቻችን ፣ የወላጆቻችን ጉዳይ ሁሉ ስለተካተተ ይመለከተን ስለነበር ንቁ ተሳትፎዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ አንዷ “የኢትዮጵያ ባሎች ሲባሉ…” ብላ ብሶት የጎላበት መልእክት ስታስተላልፍ ሁሉም በሚባል መልኩ በአዎንታ ያረጋግጡላታል፡፡ ሌላዋ ተነስታ በተቃራኒው “የእኛ ባሎች እኮ ቢያንስ ይሉኝታ ያውቃሉ ነጮቹንና ጥቁሮቹን (እኛ ከጥቁር የተለየን ይመስል) ብታዩ እኮ…” ብላ ስታብራራ የእሷንም ሀሳብ በአዎንታ ያደምቁላታል፡፡ ጭውውቱ ወንዶችም የተሳተፉበት ስለነበረ እነሱም በወንድኛ ያዩትን እና ያመኑበትን ይተቻሉ፤ በባሎች እና በሚስቶች የሚሰጠውን ትንታኔ ግራ እስኪገባኝ ድረስ ተቀባይም ነፋቂም እኩል በእኩል ነበር፡፡ ይህን ርእስ ለምሳሌ አልኩ እንጂ ስለልጆችም፣ ስለነጋዴዎችም፣ ስለሀብታሞችም፣ ስለባለስልጣኖችም ብቻ ስለተነሳው ቡድን የሚሰጠው አስተያየት እና ቅቡልነቱ ግራ እንደገባኝ ቆይታችን ተጠናቀቀ፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥመኝ የመጀመርያዬ ስላይደለ “እያለን የለንም ማለት ነው?” ብዬ እራሴን እንድጠይቅ አድርጎኛል፡፡
እያለን የሌለው ምን ይሆን ብላችሁ ከጠየቃችሁኝ ካለን ነገር ብጀምር በጣም ብዙ ነገር አለን፡፡ ብዙዎቻችን በተወሰነ መልኩ ትምህርት ቤት የሄድን፣ በተለያዩ ስራዎች እና ንግድ ላይ የተሰማራን፣ ከሰዎች ጋር የምንኖር እና የምንሰራ፣ ከሰዎች ልምድም እውቀትም የምንጋራ የምንማማር ሰዎች ነን፡፡ ብዙዎቻችን አእምሮ አለን፤ የምናስብበት፣ የምንተሳሰብበት፣ የምናሰላበት፣ የምንሰላበት፡፡ ከአእምሮ በተጨማሪ የስሜት ሕዋሳቶች አሉን፤ አካባቢያችንን የምናይበት፣ የምናዳምጥበት (ካዳመጥን…በኋላ እመለስበታለሁ)፣ ሚዛን የምንጠብቅበት፣ የምንዳስስበት፣ የምንንቀሳቀስበት፣ የምንቀምስበት እና የምንለይበት፡፡ እነዚህ የግል ንብረቶቻችን ሲሆኑ እንደማህበረሰብ ደግሞ ባህል፣ ኃይማኖት፣ ማህበራዊ ኑሮ፣ ሀገር፣ መንደር፣ ወዘተ አሉን፡፡ አንድ ሰው በዚህ ሁሉ መኖር ውስጥ ታድያ እንዴት ነው አቅም እና አቋም እንደሌለው ሆኖ የሚገኘው!?
ለጭውውቴ መነሻ ወደሆነኝ እና የብዙ ሰዎች ስብጥር ወደነበረው ውይይት ልመልሳችሁ እና አንዷ ለምሳሌ እንደ ሀሳብ ያነሳችው ነገር “እኔ ባል ሳገባ የቤት እመቤት ሆኜ ልጆቼን ማሳደግ ነው የምፈልገው ስለዚህም የማገባው ሰው ቤታችንን በኢኮኖሚ ቀጥ አድርጎ የሚይዝ መሆን አለበት፤ አለበለዝያ ለማን አባቱ ብዬ ነው የማገባው!” ከማለቷ በአብዛኛው (ሴቶችም ወንዶችም) በሳቅ እና በፈገግታ ካጀቧት በኋላ “እውነትሽን እኮ ነው፣ ምን በወጣሽ በቤትም በደጅም የምትፈጊው!…ወዘተ” የሚሉ የሀሳቡ አድናቆት ጎረፈላት፡፡ ቅዱሳን መጽሐፍትም ተጠቀሱ ለማጠናከርያነት እናም ድንቅ ሀሳብ መሆኑ ተረጋገጠ፡፡ ከዚያው ጋር ተያያዘና ሌላዋ ሴት “እኔ በኢኮኖሚ እራስን ሳይችሉ ማግባት እና የወንድ እጅ መጠበቅ ምን እንደሚመስል አይቼዋለሁ፤ ከአስቤዛ ጀምሮ ለእያንዳንዷ ወጪ መጠየቅ ይደክማል፤ ሌላው ቢቀር እራሱ የሚጋብዛቸውን ሰዎች የተሻለ ነገር ሰርቼ ለመጋበዝ ለግብአት መግዣ ስጠይቀው እንኳን ገንዘብ የሚሰጠኝ ከሚሸነቁጥ ንግግር ጋር ነው! ለእራሴ የምፈልጋቸው ነገሮችንማ መጠየቅ ትቻለሁ፤…ወዘተ” ካለች በኋላ ቀጠለችና ሀሳቧን ለማጠናከር “በባል ገቢ ብቻ መኖር እሳት ማለት ነው ይፋጃል፤ እናም ማንንም ጥገኛ መሆንን አልመክርም!” ከማለቷ ቅድም “ምን በወጣኝ እና ምን በወጣሽ!” ሲሉ የነበሩት ሁሉ ግልብጥ ብለው የዚህኛው ሀሳብ ደጋፊ ሆነው ተገኙ፡፡ እኔ ብወያይበት እና ብከራከርበት በምወደው ርእሰጉዳይ ባይተዋር ሆንኩኝ፡፡
በውይይት እና በክርክር አምናለሁ፤ አንድም ለማሳመን አልያም ለማመን የሚደረግ ውይይት እና ክርክር፡፡ እንደዚህ ያለ በደቂቃዎች የሀሳብ መገለባበጥ ያለበት ቡድን ውስጥ ስገኝ ግን ከእድሜዬ ላይ የተሰረቀብኝ ነው የሚመስለኝ፡፡ ከዚህ ቀደም ያመንኩበትን ሀሳብ እና አቋም ይዤ እሳተፍ ነበር፡፡ አቋም ይዘው የሚሞግቱኝ እና የሚያሳምኑኝ ወይንም የሚቀበሉኝ ነበሩ፡፡ አሁን እነዚያ ሰዎች የት ሄደው ነው እንደዚህ የሀሳብ አቋም እና አቅም የሌለው ሰው የበዛው!? ይሉኝታ የሚባለው ነገርስ ወዴት ገባ! አንዳንዴ እኮ “ቀደም ብዬ በዚህኛው ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ስለተስማማሁ የሚቃወሙትን ምክንያታቸውን ለማዳመጥ ዝም ብል ይሻላል!” ብሎ ማሰብም የአባት ነው! (የአባት የሚለው አባባል ግን ምን ማለት ይሆን! አባት አይዋሽም፣ አያወላውልም ወይንም ብቸኛ ተከባሪ ነው ለማለት ነው! እዚያ ውስጥ አልገባም!)
ቆይ ግን ይህንን ነገር እኔ ብቻ ነኝ የታዘብኩት!? አይመስለኝም፤ እናንተም ሳትታዘቡ አትቀሩም፡፡ ቆይ ታድያ እንደማህበረሰብ ምን ይሆን ያጣነው? ትምህርታችን ይሆን? አስተዳደጋችን ይሆን? ባህላችን ይሆን? ማህበራዊ ትውፊቶቻችን ይሆኑ? ኃይማኖቶቻችን ይሆኑ? ድህነታችን ይሆን? ሁሉም ተደማምረው ይሆን? የሀሳብ ወጥነትን የምናዳብርባቸው ብዙ መንገዶች እንዳሉ አንብቢያለሁ፤ በተለያዩ ኮርሶችም ተምሪያለሁ፡፡ ወላጆቻችንም የጠየቁንን ልንመልስላቸው ስንል “አንዱን ምረጪ አታወላውይ!” በሚል መክረውናል፤ ካልተመከርን ቆንጥጠውናል፡፡ ቤተእምነቶችም የራሳቸውን ድርሻ እያስተማሩን አድገናል፡፡ አስተማሪዎችም የዋዛ አልነበሩም፤ ጎረቤቶችስ እንዲህ እንደዛሬ እሩቅ ለሩቅ ሳንሆን “የእከሌ ልጅ” እየተባለ ሁሉም ቀጪአችን ነበሩ! እና ታድያ ይሄ ሁሉ እሴት እያለን አቋም እና አቅም የሌለን ስለምን ይሆን!
እኔ እንደማህበረሰብ ብዙ መሰራት ያለበት ነገር አለ ባይ ነኝ፡፡ እኛ ጎልማሶቹም፣ታላላቆቻችንም፣ ወጣቶቹም እንዴት እንዲህ የሀሰብ መዋዠቅ ሊያጠቃን ቻለ!? ምናልባት ከሰዎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ከቁምነገር ስለማንቆጥረው ይሆን!? እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ለምን ታድያ ውዱን ጊዜአችንን በማናምንበት ግንኙነት ላይ እናባክናለን!? ነገስ የሚተኩን ታዳጊዎች ከእኛ ምን ይማራሉ? ከላይ ስለመስማት እና ስለማዳመጥ ስጽፍ ያቆየሁት ሀሳብ ነበረ፡፡ ማዳመጥ ነው የሚጎድለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ለሁሉም ሀሳብ ደጋፊም ተቃዋሚም ከሆንን እያዳመጥን አይደለም፤ ይልቁንስ እየሰማን እንጂ፡፡ ስናዳምጥ ሚዛናዊ እንሆናለና! በነገራችን ላይ ጆሮ የሰውነታችንን ሚዛን በመጠበቅ ትልቅ ሚና አለው ይባላል፤ ሳይንስ ነው ያለው ደግሞ የሰው ወሬ አይደለም፡፡ እና እያለን የሌለን እና እራሳችንም የሌለነው ከማዳመጥ ይልቅ ስለምንሰማ ነው (በማዳመጥ እና በመስማት ያለውን ልዩነት ስለምታውቁት እንለፈው)፡፡ ይሄ የሆነው ደግሞ ከነባራዊው ሁኔታ ተነስቼ ስገምተው ውስጣችን ሌሎች የሚጮሁ ነገሮች ስላሉብን ይሆን!? ከኑሮ ውድነቱ ሰላም ማጣቱ፣ እድሜ ያለሀይ ባይ ምንም ሳንሰራበት መሮጡ፣… ወዘተ
አቋም እና አቅም ሲኖረን ብዙ ጎዶሏችንን ይሞላልናል፣ በእራስ መተማመናችን ይጨምራል፣ ሰዎችም ወደእኛ ይዘው የሚመጡት መረጃም ሆነ ማንኛውም መወያያና መከራከርያ ሀሳብ ደርዝ ያለው ይሆናል፡፡ እኛም የማንንም ጊዜ አናጠፋም፤ ሰዎችም የእኛን ጊዜ አያጠፉም፡፡ ስለዚህም እያለን የሌለን ሳንሆን እያለን ያለን እና የሚኖረን እንሁን! ለዛሬ ጨርሻለሁ!
Share to your circles!