በጋመ ምጣድ ለመጋገር ወረፋ አንያዝ!

አቤት የድሮ ጉርብትና እኮ ብዙ ደሳስ የሚሉ ትውፊቶች ነበሩት። ማህበራዊ ኑሮው በተለይ ዳግም ላይመለስ የጠፋ እንደ ትርክት ለልጆቻችን የምናወራው ለእኛ ብቻ ትዝታው የሚያስደስተን:፡ ለምሳሌ እንዲህ እንደአሁኑ በከተማችን ብዙ የኤሌክትሪክ ምጣደች በየቤቱ ባልነበሩበት ዘመን የጋራ የሆኑ የጭስ ኩሽናዎች ነበሩ፡፡ ታድያ አንዲት እናት ገና አብሲት ስትጥል ሌላኛዋም እግሯን ተከትላ አብሲቷን ትጥላለች። ለምን መሰላችሁ የመጀመርያዋ ባሰማችው ምጣድ ለመጋገር ሌላኛዋ ወረፋ ይዛ በመጠበቅ ትጋግራለች ማለት ነው፡፡ ደግሞ ሌላኛዋ በመሶቡ ያለው በቀደም የጋገረችው እንጀራ እንዳይሻግትባት በሰማው ምጣድ ላይ በሶስተኝነት ወረፋ ጠብቃ ታሞቃለች። ብቻ ምን አለፋችሁ የጋመው ምጣድ ላይ ለመጋገር የማይበረታ የለም፡፡ ታድያ የመጀመርያው ድካምና ወጪ ያለው ማገዶ ፈልጣ፣ አብዝታ ጨምራ፣ ተጫጭሳ፣ አቀጣጥላ ምጣዱን አስምታ የጋገረችው የመጀመርያዋ ሴት ላይ ነው። ደግሞ እኮ አብሮነቱ እንዳለ ሆኖ ይተማሙ ነበር፤ “ይቺ ደግሞ ሁልጊዜ የእኔን የጋመ ምጣድ ጠብቃ የምትመጣና የምትጋግው ማገዶ ላለመግዛት ነው? እሷ ብቻ ብልጥ የሆነች ይመስላታል? ወዘተ!” ቡናቸውን ሲጠጡም ሸንቆጥ ይደራረጋሉ፡፡ ያው ነጻነትን በጋመ ምጣድ መቀየር በሉት፡፡ አብዝታ ነጻነት የሚኖራት የመጀመርያዋ ናትና!
ታድያ ተባብሮ መኖሩ እንደ ጥሩ ትዝታ አነሳሁት እንጂ ዋናው ለማውራት የፈለግኩት ከትዳር ጋር እንዴት እንደሚነጻፀር ለማሳየት ነው፡፡ ትዳር የሚመሰረተው በሁለቱ ተጋቢዎች ፍቅርን መሰረት በማድረግ ሲሆን ከዚያ በፊት ግን ቅድመ ዝግጅት ይደረጋል፡፡ ታድያ ሁላችንም እንደምናውቀው ማህበረሰቡም ቅድመ ዝግጅቱ የወንዱ እንዲሆን ይጠብቃል፤ ብዙ ሴቶችም የምንመኘውና የምንጠብቀው የተደራጀ ቤት ውስጥ ለመግባት ነው፤ ልክ በጎረቤታችን እንደጋመው ምጣድ፡፡ ከተገኘ ማን ይጠላል! ደግሞስ ወንዱም ቢችል ደስ የሚለው ቤት ሠርቶ፣ ቤቱን በአስፈላጊው ቁሳቁስ አሟልቶ፣ መኪና ገዝቶ ሲጨርስ ሚስቱ ቤቱ ገብታ ሚስት ሚስት እንድትጫወትም አይደል! እሱ ልክ የመጀመርያውን ምጣድ ለማስማት የደከመችውን ባለመብቷን ሴት ይመስላል። “እሱ ከፈለገ ምናለበት?” ካላችሁኝ ክፋት የለበትም። በተለይ ፍቅሩ ከዘለቀ! ቤት እኮ ተሰርቶ አያልቅም፤ ሴቷ ከገባች በኋላም ስራው ይቀጥላል፡፡ ይህ ግን ቀና አስተሰሰብ ይፈልጋል፡፡ በነገራችን ላይ አንዳንድ ወንዶችም “ምን አላት?” ብለው አስልተው የሚወዳጁ አሉ። የጋመ ምጣድ ቢኖራቸውም አቻ የጋመ ምጣድ የሚጠብቁ፤ ግን ቁጥራቸው ብዙ አይደለም፡፡ እነሱን ዛሬ አናነሳቸውም፤ መነሻችንን እንዳይጣረስብን!
እኔ ትዳር ለምትፈልገዋ ሴት የምመክራትም ሆነ የምመኝላት በጋመ ምጣድ ለመጋገር ወረፋ እንዳትጠብቅ ነው፡፡ ይልቁንም በንጹሕ ልባዊ ፍቅር፣ በእውቀት እና በጥበብ የተሞላ፣ ቤትን ማስተዳደር የሚያስችል ገቢ ሁለቱም ተጋቢዎች ቢያስገቡ፣ ከዚያም ከእለት ኑሮ ባሻገር ተቆጥቦ ለሚወለድ/ዱ ልጆች እና ለመኖርያ አስፈላጊውን አብሮ መገንባት የሚያስችል አቅም ይዞ እንጂ። የሞላ ቤት የምትጠብቀዋ እህት የሰማ ምጣድ እየጠበቀች እንደምትጋግረዋ የድሮ ጎረቤት ሴት ትመስለኛለች ማለቴ ነው፡፡ ሁሌ ጠባቂና ተጠባባቂ በእራስ መተማመን የማይኖራት ሆና ትታየኛለች። “ሁሉን ነገር አሟልቼ ነው ሚስቴ ቤቴ የምትገባው” ብለህ የምታምነው ሰውዬም መበለጥህን እያሰብህ የበታችነት ስሜትህን እየታገልህ የበላይነትህን ለማስጠበቅ የምትታትር ትመስለኛለህ። ይሄ የእኔ ግምት ነው፡፡ ልክ ነዋ! አንተ በለፋህበት አዛዥ ናዛዥ ልሁን ብትል የልብ ስብራትህን ታስባለሀ አይደል!? ሲጀመር እሷም ካላበደች አዛዥ ናዛዥ ልሁን የምትል አትሆንም፤ በጋመው ላይ ገብታ! ነገርየው እኮ ውስብስብ ነው! ቀላል አድርገን አየነው እንጂ የጋመ ምጣድ ስትጠብቅ የምትፈልገውን ትሳር ያላገኘች እሱም ምጣዴን ላግም ሲል ጊዜ የሚሄድበት ቤት ይቁጠራቸው! ልግ በሉ ትዳሩን ፈልገው ነው ያልኩት፤ ያልፈለጉትን እና የማይፈልጉትን አይመለከትም፡፡
ለዚህ ሁሉ ስሌት ግን ተጠያቂው ማህበረሰባችን ነው፡፡ ሲወርድ እና ሲወራረድ የመጣውን አባዊ ስርዓት መቀየር አልተቻለም፡፡ ዛሬ ላይ ሴቶች እየተማሩ እና እየሰሩ ከድሮ በተሻለ በኢኮኖሚው ላይ ያላቸውን ድርሻ እያረጋገጡ ነው፤ በተለይ ዋና ከተማዎች፡፡ ነገር ግን አንዳዶቹ ወንዶች እና ሴቶች ከድሮ መንፈስ መላቀቅ ተስኗቸዋል መሰለኝ አሁንም ቁሳቁስ ማሟላትን እንደመብታቸው የሚያዩት አሉ፡፡ ሰዎች ስለትዳር ሲያስቡ ፍቅር እና ትጋትን መሰረት እንዳያደርጉ “ምን አለው፣ ምን አላት የሚሉት ጥያቄዎች የተንሰራፉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ተጋቢዎቹ እኮ ከተጋቡ በኋላ ኑሯቸውን የሚገፉት ለሁለት እየተውተረተሩ እንጂ የውጪው ነፋስ ያን ያህል መሰረት የለውም፡፡ ይህ ማለት ግን የሶስተኛ ወገን “ምን አለው?” እና “ምን አላት?” ምንም ፋይዳ የለውም ማለት አይደለም፡፡ ትዳሩን ከሁለቱ ተጋቢዎች ውጪ ከዳርም ከመሀልም ሆነው የሚያጫውቱ ብዙ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን እራስን ዋና ተዋናይ ማድረጉ ድንቅ እና አዋጭ ነው፡፡ “ለማን ብዬ?” ካላችሁ ለራሳችሁ ብላችሁ እላችኋለሁ፡፡ አዋጭ ስል ቢዝነስ አስመሰልኩት አይደል! ለነገሩ እኮ ትዳር ቢዝነስ የሚመስል ነገር አለው፤ መስጠት፣ መቀበል፣ መደራደር፣ መከራከር፣ መግባባት፣ አለመግባባት ወዘተ!
እና ሳጠቃልለው የትዳር እንጀራ የሚጥመው የጋመ ምጣድ እስኪከሰት ወረፋ ከመጠበቅ ይልቅ የራስን ምጣድ አግመው፣ አስሰው እና አለስልሰው ሲጋግሩ እና ሲበሉ ነው! ከመፋቀሩ ባሻገር የእኔነት ስሜቱ፣ በእራስ መተማመኑ እና መተሳሰቡ ከጭሳጭሱ(ከድካሙ) 100 እጥፍ ቀጥ ያደርጋልና! ያው የአሁኑ ወጣቶች የድሮውን ምጣድ ባታውቁትም ሀሳቡ ግን ይገባችኋል ብዬ አምናለሁ! እደጋግመዋለሁ፡- በሌላ ሰው የጋመ ምጣድ ለመጋገር ወረፋ አንያዝ! ለዛሬ ጨርሻለሁ!