የአበባየሽ ወይ ገራሚ እይታ!

መስከረም አንድ ቀን የሚከበረው የኢትዮጵያ አዲስ አመት የአንድነት አውድአመት ነው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘር እና ኃይማኖት ሳይለይ የሚያከብረው እና በደስታ የሚቀበለው፡፡ ሁላችንም ልጅ አዋቂው እንኳን ለ2018ዓ.ም. በሰላም ደረሰኝ የምንባባልበት ትልቅ ቀን ነው (በዚሁ እንኳን አደረሰን ብያለሁ!)፡፡ እለቱም እንቁጣጣሽ ተብሎ በተለይ ታዳጊ ሴቶች ልጆች “አበባ አየሽ ወይ!” ብለው እየዞሩ ይጨፍራሉ፤ ሳይርቁ በጎረቤቶች እና በሚያውቋቸው ሰዎች ቤቶች፡፡ ታድያ ዛሬ በዚህ ጉዳይ የሚያስወራኝ ገጠመኝ ስለኖረኝ እንጂ አዲስ አመትማ ሁላችንም የምናውቀው እና የምናከብረው ነውና እያስተዋወቅኳችሁ እንዳልሆነ ይሰመርበት፡፡

ምን ሆነ መሰላችሁ፤ በአዲስ አመት ዋዜማ (እኛ ድሮ ልጆች እያለን እንግጫ ለቀማ ይባል ነበር፤ አሁንም ቃሉን ባንጠቀምበትም ስያሜው እንደዚያው መሰለኝ) ታዳጊ ሴቶች እየጨፈሩ እኔና አንዲት የውጭ ዜግነት ያላት ጓደኛዬ ያለንበት መጡ፡፡ በእርግጥ ልጆቹ ያንን ያህል ግጥሙን አጥንተው እያዜሙ ባይሆንም አድምቀውታል፤ ልጆችም ስለሆኑ ደስ ይሉ ነበር፡፡ ታድያ ጓደኛዬ ያየችውን፣ የምትበላውን፣ ብቻ ምናለፋችሁ ለእሷ አዲስ የሆነውን ሁሉ ትጠይቃለች፡፡ ያው እኛም እነሱ ሀገር ብንሄድ መጠየቃችን አይቀርምና! ከዚያ እኔ በልጅነቴ በማውቀው ግጥም የጨዋታው መሪ (ዜማ አውጪ) የምትለውን እየተረጎምኩ ማስረዳት ጀመርኩ፤ “አበባየሽ ወይ ብላ ጀምራ እስክትጨርስ ተቀባዮቿ ለምለም ይላሉ፣ እሷ ትቀጥላለች፤ ባልንጀሮቼ ቁሙ በተራ፣ እንጨት ለቅሜ ቤት እስክሰራ፣ እንኳን ቤት እና የለኝም አጥር፣ እደጅ አድራለሁ ኮከብ ስቆጥር፣ ኮከብ ቆጥሬ ስገባ ቤቴ፣ ትቆጣኛለች የእንጀራ እናቴ…እናቴን ጥሯት መድሀኒቴን፣ እሷን ካጣችሁ መቀነቷን እያለ ይቀጥላል፡፡ ከዚያ ደግሞ ልጅቷ መቼ እንዳገባች ባይታወቅም ለባሏ ንፍሮ ቀቅላለች፡፡ እናም “ንፍሮ ቀቅዬ ብላ ብለው፣ ጉልቻ አንስቶ ጎኔን አለው፣ ከጎኔም ጎኔም ኪላሊቴን.. እያለች ታዜማለች ነው ታንጎራጉራለች የሚባለው! መጨረሻ ላይ ስጦታው (ሽልማቱ) ሲሰጣቸው ሁሉም ልጆች በሕብረት “ከብረው ይቆዩን ከብረው፣ በአመት ወንድ ልጅ ወልደው፣ ሰላሳ ጥገት አስረው” እያሉ ይመርቃሉ፡፡ ሲያጠቃልሉ ይሸታል ዶሮ ይሸታል ጠጅ የእማምዬ ደጅ በማለት የሴትየዋን ሙያ ያሞግሳሉ አልኳት፡፡

በአግራሞት የከፈተችውን አፏን እስክትዘጋ ጠብቄ ስሜቷን እና አስተያየቷን በጉጉት መጠባበቅ ያዝኩ፡፡ በጣም ያደነቀች  መስሎኝ “እኔ አድንቄው የማላውቀውን አበባየሽ ወይ እንዴት አደነቀች?” ብዬ ተገርሜ ነበር፡፡ ለካስ እሷም ከመደነቅ ይልቅ ደንግጣ ኖሯል፡፡ እናም አለች፡- “መጀመርያ ይህን የመሰለ እሮሮ በአዲስ አመት እንዴት እንደዜማ ይቀርባል?” ብላ ዜማ ሳይሆን ሙሾ መሆኑን ነገረችኝ፡፡ እኔ እየሳቅሁ ነበር የምተረጉምላትም የማዳምጣትም፡፡ የአእምሮዬን ደህንነት የተጠራጠረች ሁላ ነበር የምትመስለው፡፡ ለካ ለእነሱ አባባል ሁሉ በቂ ትርጉም ያለው ዘመኑን የሚዋጅ ነው፡፡ እኛ ደግሞ የሆነ ዘመን ላይ ማን ድርሰቱን እንደሰራው የማናውቀውን አበባየሽ ወይ ደስ እያለን እየተጫወትን  ከዘመን ዘመን እየተቀቀባበልነው ነው፡፡ ለነገሩ እኔም የሆነ ዘመን ላይ መጠየቅ ጀምሬ ነበር፤ አትፈላሰፊ ተብዬ ተኮረኮምኩ እንጂ፡፡ አንድ ጊዜ ያነበብኩት (በወንድ የተጠና ጥናት ይመስለኛል ጊዜው እሩቅ ነው) አበባ የሚለው ላይ ትኩረት አድርጎ  “አበባ አየሽ ወይ ማለት የወር አበባ ማለት ነው ምክንያቱም ሴት ልጅ የወር አበባ ካየች ለአቅመ ትዳር ዝግጁ ስለሆነች…” ይላል፡፡ አስቡት የወር አበባ ከ10 እስከ 12 ባለው እድሜ የሚመጣ የተፈጥሮ ስርዓት ሲሆን ሴት ልጅ ግን ለአቅመ ትዳር ደረሰች የምትባለው ልጅ ከሚለው ክልል ማለትን ከ18 እድሜዋ በላይ ስትሆን ነው፤ ይሄ ደግሞ ሀገራችንም በፈረመችው የአለማቀፉ ኮንቬንሽን ቁልጭ ተደርጎ ተቀምጧል፡፡ ብቻ የሴት ልጅ ነገር ገና ተጠንቶ ያላለቀ ስላይደለ እሱን ትተን ወደ ተነሳንበት እንመለስ፡፡ እና ጓደኛዬ በቁጣ “The girls aren’t really celebrating the New Year; they’re reaching out, maybe to elders or even the authorities, to step in about the harassment they’re facing.” ብላኝ እርፍ! እኔም አበባየሽ ወይ የድረሱልኝ ጥሪ መሆኑን የውጭ ዜጋዋ ጓደኛዬ ሲብራራልኝ ዋጥ አድርጌ ዝም!

የምር ግን አበባየሽ ወይ ዜማው እንዳለ ሆኖ ግጥሙ መቀየር አለበት፡፡ የረሳሁት ደግሞ አለላችሁ “እቴ አበባ እቴ አበባዬ፣ እቴ አበባሽ ስትለኝ ከርማ፣ ጥላኝ ሄደች በሐምሌ ጭለማ” የሚል አለበት፡፡ ይሄኛውን ለጓደኛዬ አልተረጎምኩላትም እንጂ ልጅቷ በጓደኛ ወይንም በእህት የተከዳች መሆኑን ያሳያል፡፡ አስባችሁታል ግን ስንት ሰው እንደበደላት? እንጀራ እናቷ፣ ባሏ፣ ጓደኛዋ ወይንም እህቷ፤ ይሄኔ በሌላ ሰፈር እኔ ያልሰማሁት ግጥም ውስጥ ሌላ በዳይም ይኖር/ትኖር ይሆናል፡፡ ከምር ግን “አበባየሽ ሆይ” የሴት ልጅን በደል ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ፌሚኒስት የሆነ ድርሰት ነው፡፡ ለዚህም ነው መፍትሔ ያላገኘው፤ ልክ ሰሞኑን እንደተጫጩባቸው ፌሚኒስቶች ማለት ነው፡፡ ለነገሩ ፌሚኒስቶቹም ብዙ ከባህል እና ማህበራዊ እሴቶቻችን የወጡ ባህርያት እያሳዩ እንቅስቃሴውን ለገዳዮች አሳልፈው ሰጡት እንጂ እኔም እኮ ፌሚኒስት ነበርኩ ማለቴ ነኝ፤ የሴቶች መብት ተሟጋች! አንድ ቀን እለት ይሄንን የእኔና የውጪ ዜጋዋ ጓደኛዬን ወግ በግርድፉ ሶሻል ሚዲያ ላይ ባወራው ፌሚኒስቷ ብለው ተንጫጩብኝ፤ የማፈን ዘመቻ በሉት፡፡ ብቻ ስለሴቶች መብት ድምጽ ማሰማት እየታፈነ ሄዶ ሄዶ መጨረሻው ዝምታ ስለሚሆን በአበባየሽ ሆይ የተገለጸውም፣ አስገድዶ መድፈሩም፣ መግደሉም፣ ብቻ አለ የተባለው ጥቃት ባለበት ይቀጥል ዘንድ ተፈርዶበታል፡፡

አሁን አሁን በተለይ ቤተ እምነቶች በምስጋና እየቀየሩት ይገኛሉ፤ ሙዚቀኞችም እንደዚያው፡፡ እስቲ ሁሉን የሚያካትት፣ ትውልድ የሚቀባበለው፤ ወቅቱን የሚናገር፣ ከክረምት ወደ በጋ፣ ከአበባም ወደ አደይ አበባ፣ ከእረፍት ወደ ትምህርት ቤት፣ ከአሮጌ ወደ አዲስ አመት መሸጋገርያ ብስራት የሆነ ዜማ እንስራ! ስንመርቅም ወንድ ልጅ ብቻ እንዲወለድ አንመርቅ! አስባችሁታል ወንድ ብቻ ተወልዶ የሴት እጥረት ቢከሰት ምን ሊፈጠር እንደሚችል!? ሌላው ቢቀር ትውልድም አይቀጥልም፡፡ ካልሆነ አዲስ ግጥም ላዋጣ እንዴ፡- “አበባየሽ ወይ ለምለም፣ ዛሬ ደረስን፣ አሮጌው አልፎ አዲሱን አየን፣ ፍክትክት አለ አደይ አበባችን፣ ሊከፈትልን ነው ትምህርት ቤታችን…ወዘተ፡፡ በሉ ግጥም እስኪመጣልኝ ለዛሬ ጨርሻለሁ!

Share to your circles!

1 thought on “የአበባየሽ ወይ ገራሚ እይታ!”

  1. Saron G/maryam Mimi

    Fitsum, you are really vital.
    በእውነት አስገራሚ እይታ ነው። ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ የድረሱልኝ ጥሪ ነው። ጥሩ ግጥም እዛ ውስጥ እምዬን ጥሯት መድሀኒቴን እሷን ካታችኋት መቀነቷን አሸተዋለሁ እሷን እሷን የሚለው ብቻ ነው። ይሄ ደሞ ሴት ልጅ ከናቷ በቀር ዘመድ የላትም የሚለውን አባባል ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። ሴት ልጅ ከእናቷ ሳትርቅ ብዙ ልምድና እውቀት እያዳበረች ማደግ አለባት ፈጣሪ ቢፈቅድ በተረፈ ጓደኛም እህትም የ እንጀራ እናትም ባልም ሊከዱን ይችላሉ ብቸኛዋ መድሀኒታችን እናታችን ናት ሀገራችን ናት ማለት ነው ሰቆቃው ሳይሰማልን ዘመናት አለፉ ባል በጉልቻ ከማለት አልፎ ገዳይ ሆነ …

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top